ኤርምያስ 25 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ባቢሎን ምርኮ የተነገረ ትንቢት 1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት፥ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በመጀመሪያው ዓመት፥ ስለ ይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2 ይህንም ቃል ነቢዩ ኤርምያስ ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉና በኢየሩሳሌም ለተቀመጡ ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ 3 “ከይሁዳ ንጉሥ ከአሞጽ ልጅ ከኢዮስያስ ከዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባሉት በእነዚህ በሃያ ሦስቱ ዓመታት፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፤ እኔም ማልጄ ተነሥቼ ተናገርኋችሁ፤ ነገር ግን አልሰማችሁኝም።” 4 እግዚአብሔርም ባሪያዎቹን ነቢያትን ወደ እናንተ ላከ፤ እነርሱም ማልደው ገሠገሡ፤ እናንተም አልሰማችኋቸውም፤ ለመስማትም ጆሮአችሁን አላዘነበላችሁም። 5 እርሱም፥ “ሁላችሁ እናንተ ከክፉ መንገዳችሁና ከሥራችሁ ክፋት ተመለሱ፤ እግዚአብሔርም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጣችሁ ምድር ትቀመጣላችሁ አለ። 6 ትገዙላቸውና ትሰግዱላቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፤ ክፉም እንዳላደርግባችሁ በእጃችሁ ሥራ አታስቈጡኝ። 7 ለእናንተ ጕዳት እንዲሆን በእጃችሁ ሥራ ታስቈጡኝ ዘንድ አልሰማችሁኝም፥” ይላል እግዚአብሔር። 8 ስለዚህ ኀያል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ቃሌን አልሰማችሁምና፤ 9 እነሆ ልኬ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ፤ ባሪያዬንም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እወስዳለሁ፤ በዚችም ምድርና በሚቀመጡባትም ሰዎች ላይ፥ በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፤ ለጥፋትና ለፉጨት ለዘለዓለምም ዕፍረት ባድማ አደርጋቸዋለሁ። 10 ከእነርሱም የሐሤትን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራን ድምጽና የሴት ሙሽራን ድምፅ፥ የወፍጮንም ድምፅ የመብራትንም ብርሃን አስቀራለሁ። 11 ይህችም ምድር ሁሉ ትጠፋለች፤ ለእነዚህም አሕዛብና ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ። 12 “ሰባው ዓመትም በተፈጸመ ጊዜ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ያን ሕዝብ ስለ ኀጢአታቸው እቀጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ የከለዳውያንንም ምድር ለዘለዓለም አጠፋቸዋለሁ። 13 በእርስዋም ላይ የተናገርሁትን ቃሌን ሁሉ፥ ኤርምያስ በአሕዛብ ሁሉ ላይ በትንቢት የተናገረውን በዚች መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ፥ በዚያች ምድር ላይ አመጣለሁ። 14 ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት እነርሱን ይገዙአቸዋል፤ እኔም እንደ አደራረጋቸውና እንደ እጃቸው ሥራ እከፍላቸዋለሁ።” የእግዚአብሔር ፍርድ በአሕዛብ ላይ 15 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል፥ “ያልተበረዘ የዚህን ቍጣ የወይን ጠጅ ጽዋ ከእጄ ውሰድ፤ አንተን የምሰድድባቸውን አሕዛብን ሁሉ አጠጣቸው። 16 ከምሰድድባቸውም ሰይፍ የተነሣ ይጠጣሉ፤ ይወላገዳሉ፤ ያብዳሉም።” 17 ከእግዚአብሔርም እጅ ጽዋውን ወሰድሁ፤ እግዚአብሔርም እኔን የላከባቸውን አሕዛብ ሁሉ አጠጣኋቸው። 18 ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ፈጽሞ ምድረ በዳ ይሆኑ ዘንድ፥ ለርግማንም አደርጋቸው ዘንድ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች፥ ነገሥታቷንም፥ አለቆችዋንም አጠጣኋቸው። 19 የግብፅንም ንጉሥ ፈርዖንን፥ አገልጋዮቹንም፥ መሳፍንቱንና መኳንንቱን፤ ሕዝቡንም ሁሉ፥ 20 የተደባለቀውንም ሕዝብ ሁሉ፥ የዖፅ ምድር ነገሥታትንም ሁሉ፥ የፍልስጥኤም ምድር ነገሥታትንም ሁሉ፤ አስቀሎናንም፥ ጋዛንም፥ አቃሮንንም፥ የአዛጦንንም ቅሬታ፤ 21 ኤዶምያስንም፥ ሞዓብንም፥ የአሞንንም ልጆች፤ 22 የጢሮስንም ነገሥታት ሁሉ፥ የሲዶናንም ነገሥታት ሁሉ፥ በባሕር ማዶ ያሉ የደሴት ነገሥታትንም፤ 23 ድዳንንም፥ ቴማንንም፥ ሮስንም፥ ፊታቸውን የሚከተቡትን ሁሉ፤ 24 የዓረብ ነገሥታትንም ሁሉ፥ በምድረ በዳ የሚቀመጡ የድብልቅ ሕዝብ ነገሥታትንም ሁሉ፤ 25 የዘምሪ ነገሥታትንም ሁሉ፥ የኤላም ነገሥታትንም ሁሉ፥ የሜዶን ነገሥታትንም ሁሉ፤ 26 የቀረቡና የራቁ፥ አንዱ ከሌላው ጋር ያሉ የሰሜን ነገሥታትንም ሁሉ፥ በምድር ፊት ላይ ያሉ የዓለም መንግሥታትንም ሁሉ አጠጣኋቸው፤ የሲሳርም ንጉሥ ከእነርሱ በኋላ ይጠጣል። 27 አንተም፥ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመካከላችሁ ከምሰድደው ሰይፍ የተነሣ ጠጡ፤ ስከሩም፤ ተፍገምገሙ፤ ውደቁም፤ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሡም በላቸው። 28 ይጠጡም ዘንድ ጽዋውን ከእጅህ ለመቀበል እንቢ ቢሉ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፈጽማችሁ ትጠጣላችሁ” በላቸው። 29 እነሆ ስሜ የተጠራባትን ከተማ አስጨንቃት ዘንድ እጀምራለሁ፤ በውኑ እናንተ መንጻትን ትነጻላችሁን? በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁና አትነጹም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 30 “ስለዚህም ይህን ቃል ሁሉ ትንቢት ትናገርባቸዋለህ፤ እንዲህም ትላቸዋለህ፦ እግዚአብሔር በላይ ሆኖ እንደ አንበሳ ያገሣል፤ በቅዱስ ማደሪያውም ሆኖ ድምፁን ያሰማል፤ በበረቱ ላይ እጅግ ያገሣል፤ ወይንም እንደሚጠምቁ በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይጮኻል። 31 እግዚአብሔር ከአሕዛብ ጋር ክርክር አለውና ጥፋት እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይደርሳል፤ ከሥጋ ለባሽ ሁሉም ጋር ይፋረዳል፤ ኀጢአተኞችንም ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።” 32 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ ክፉ ነገር ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ይወጣል፤ ጽኑም ዐውሎ ነፋስ ከምድር ዳርቻ ይነሣል። 33 በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ግዳዮች ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይሆናሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ በምድር ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ እንጂ አይሰበሰቡም፤ አይቀበሩምም። 34 ትታረዱና ትበተኑ ዘንድ ቀናችሁ ደርሶአልና፥ እንደ ተወደደ የሸክላ ዕቃ ትወድቃላችሁና እናንተ እረኞች! አልቅሱ፤ እናንተም የበጎች አውራዎች! ጩኹ። 35 ከእረኞች የማይጠፋ የለም፤ የበጎች አውራዎችም አይድኑም። 36 እግዚአብሔር ማሰማርያቸውን አጥፍቶአልና የእረኞች ጩኸት ድምፅ፥ የበጎች አውራዎችም ልቅሶ ሆኖአል። 37 ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ የተነሣ የሰላም ውበት ፈርሶአል። 38 እንደ አንበሳ መደቡን ለቅቆአል፤ ከአረማውያን ሰልፍና ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ የተነሣ ምድራቸው ምድረ በዳ ሆናለችና።” |