ዘፀአት 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ፋሲካ 1 እግዚአብሔርም በግብፅ ሀገር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 2 “ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁናችሁ። 3 ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ተናገሩ፤ በሉአቸውም፦ በዚህ ወር በዐሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤተ ሰቦች ቤቶች አንድ አንድ ጠቦት፥ እያንዳንዱ ሰውም ለራሱ ቤተ ሰብእ አንድ ጠቦት ይውሰድ። 4 በቤት ያሉት ሰዎች ጥቂት ቢሆኑ፥ አንድ በግም የማይጨርሱ ቢሆኑ በጉን ሊጨርሱ በሚበቁ በሰዎች ቍጥር እያንዳንዱ በአጠገቡ የሚኖረውን ጎረቤቱን ይውሰድ። 5 ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለእናንተ ይሁን፤ ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰዱ። 6 በዚህም ወር እስከ ዐሥራ አራተኛ ቀን ድረስ ጠብቁት፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሲመሽ ይረዱት። 7 ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቅቡት። 8 በእሳትም የተጠበሰውን ሥጋውን በዚያች ሌሊት ይብሉ፤ ቂጣውን እንጀራም ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት። 9 ጥሬውንም፥ በውኃም የበሰለውን አትብሉ፤ ነገር ግን በእሳት የተጠበሰውን ራሱን፥ እግሩንና ሆድ ዕቃውን ብሉት። 10 ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፤ አጥንቱንም ከእርሱ አትስበሩ፤ ከእርሱም እስከ ጥዋት የተረፈ ቢኖር በእሳት አቃጥሉት። 11 ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ ተጫምታችሁ፥ በትራችሁንም በእጃችሁ ይዛችሁ እንዲህ ብሉት፦ እየቸኰላችሁም ትበሉታላችሁ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነውና። 12 እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ ሀገር አልፋለሁ፤ በግብፅም ሀገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ በቀልን አደርግባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 13 ደሙም ባላችሁባቸው ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም አያለሁ፤ እናንተንም እሰውራችኋለሁ፤ እኔም የግብፅን ሀገር በመታሁ ጊዜ የጥፋት መቅሠፍት አይመጣባችሁም። 14 ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፤ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፤ ለልጅ ልጃችሁም ሥርዐት ሆኖ ለዘለዓለም ታደርጉታላችሁ። የቂጣ በዓል 15 “ሰባት ቀን ቂጣ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያም ቀን እርሾውን ከቤታችሁ ታወጣላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ። 16 የመጀመሪያዪቱ ቀን ቅድስት ትባላላች፤ እንዲሁም ሰባተኛዋ ቀን ቅድስት ትሁንላችሁ፤ ለነፍስ ከሚሠራው ሥራ ሁሉ በቀር ማናቸውንም ሥራ ሁሉ አትሥሩ 17 በዚህም ቀን ሠራዊታችሁን ከግብፅ ሀገር አወጣዋለሁና ይህን ትእዛዝ ጠብቁት፤ እንግዲህ ይህን ቀን ለልጅ ልጃችሁ ለዘለዓለም ሥርዐት አድርጋችሁ ትጠብቃላችሁ። 18 ከመጀመሪያውም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ሠርክ ጀምራችሁ እስከዚሁ ወር ሃያ አንደኛ ቀን ሠርክ ድረስ ቂጣ ትበላላችሁ። 19 ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፤ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ሁሉ ያ ሰው ከመጻተኛው ጀምሮ እስከ ሀገር ልጁ ድረስ፥ ከእስራኤል ማኅበር ተለይቶ ይጥፋ። 20 እርሾ ያለበትን ምንም አትብሉ፤ በቤቶቻችሁም ሁሉ ውስጥ ቂጣ ብሉ።” የመጀመሪያው ፋሲካ 21 ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎች ጠርቶ አላቸው፥ “ሂዱና በየወገናችሁ ጠቦት ውሰዱ፤ ለፋሲካም እረዱት። 22 ከሂሶጵ ቅጠልም ጭብጥ ውሰዱ፤ በዕቃ ውስጥ ባለውም ደም ንከሩት፤ በዕቃውም ውስጥ ከአለው ደም ሁለቱን መቃኖችና ጉበኑን እርጩ፤ ከእናንተም አንድ ሰው እስኪነጋ ድረስ ከቤቱ ደጅ አይውጣ። 23 እግዚአብሔር ግብፃውያንን ይመታ ዘንድ ያልፋልና፤ ደሙንም በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ በአየ ጊዜ እግዚአብሔር በሩን ያልፋል፤ አጥፊውም ይመታችሁ ዘንድ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይተወውም። 24 ለእናንተ ለልጆቻችሁም ለዘለዓለም ይሆናችሁ ዘንድ ይህን ሕግ ጠብቁ። 25 እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ወደሚሰጣችሁ ሀገር በገባችሁ ጊዜ ይህን አምልኮ ጠብቁት። 26 ልጆቻችሁ፦ ‘ይህ ሥርዐት ለእናንተ ምንድር ነው?’ ባሉአችሁ ጊዜ እናንተ፦ 27 ‘ይህ በግብፅ ሀገር የእስራኤልን ልጆች ቤቶች ሰውሮ ግብፃውያንን በመታ ጊዜ፥ ቤቶቻችንን የአዳነ የእግዚአብሔር የፋሲካው መሥዋዕት ነው’ ትሉአቸዋላችሁ።” ሕዝቡም ተጐነበሱ፤ ሰገዱም። 28 የእስራኤልም ልጆች ሄዱ፤ እንዲህም አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንደ አዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ። 10፥ የግብፃውያን የበኵር ልጆች ሞት 29 እንዲህም ሆነ፤ እኩለ ሌሊት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በዙፋን ከተቀመጠው ከፈርዖን በኵር ጀምሮ እስከ ውኃ ቀጅዋ ምርኮኛ በኵር ድረስ፥ በግብፅ ምድር በኵሩን ሁሉ፥ የእንስሳውንም በኵር ሁሉ መታ። 30 ፈርዖንም፥ ሹሞቹም ሁሉ፥ ግብፃውያንም ሁሉ በሌሊት ተነሡ፤ የሞተ የሌለበት ቤት አልነበረምና በግብፅ ምድር ሁሉ ታላቅ ልቅሶ ሆነ። 31 ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ አላቸው፥ “እናንተ የእስራኤልም ልጆች ተነሡ፤ ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱም፤ እንዳላችሁም እግዚአብሔርን አምልኩት፤ 32 በጎቻችሁንም፥ ላሞቻችሁንም ውሰዱ፤ ሂዱም፤ እኔንም ደግሞ ባርኩኝ።” 33 ግብፃውያንም ፈጥነው ከምድሩ ይወጡ ዘንድ ሕዝቡን ያስቸኩሉአቸው ነበር፥ “ሁላችንም እንሞታለን” ብለዋልና። 34 ሕዝቡም ሊጡን ሳይቦካ ተሸከሙ፤ ቡሃቃውንም በልብሳቸው ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙት። 35 የእስራኤልም ልጆች ሙሴ እንዳዘዘ አደረጉ። ከግብፃውያንም የብርንና የወርቅን ዕቃ፥ ልብስንም ተዋሱ። 36 እግዚአብሔርም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት ሞገስን ሰጠ፤ እነርሱም አዋሱአቸው። እነርሱም ግብፃውያንን በዘበዙአቸው። እስራኤላውያን ከግብፅ እንደ ወጡ 37 የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ፤ ከጓዝ ጋር ካሉት ሌላ ስድስት መቶ ሺህ ሰው የሚያህል እግረኛ ነበረ። 38 ደግሞም ሌላ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ፥ መንጎችና ላሞችም እጅግ ብዙም ከብቶች ከእነርሱ ጋር ወጡ። 39 ከግብፅም ከእነርሱ ጋር ያወጡትን ሊጥ ቂጣ እንጎቻ አድርገው ጋገሩት። አልቦካም ነበርና፤ ግብፃውያንም ስለ አስወጡአቸው ይቈዩ ዘንድ አልተቻላቸውምና፤ ለመንገድም ስንቅ አላሰናዱም ነበርና። 40 የእስራኤልም ልጆች በግብፅ ምድርና በከነዓን ምድር እነርሱና አባቶቻቸው የተቀመጡት ዘመን አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነው። 41 እንዲህም ሆነ፤ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ የእግዚአብሔር ሠራዊት ሁሉ በሌሊት ከግብፅ ምድር ወጣ። 42 ይህች ሌሊት ከግብፅ ምድር ስላወጣቸው ለእግዚአብሔር የተጠበቀች ናት፤ ይህች ሌሊት በእስራኤል ልጆች ሁሉ ዘንድ እስከ ልጅ ልጃቸው ድረስ ለእግዚአብሔር የተጠበቀች ናት። የፋሲካ ሕግ 43 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን አላቸው፥ “ይህ የፋሲካ ሕግ ነው፤ ከእርሱ ባዕድ ሰው አይብላ። 44 አገልጋይ ወይም በብር የተገዛ ቢኖር ከተገረዘ በኋላ ያን ጊዜ ከእርሱ ይብላ። 45 ጥገኛና ሞያተኛ ግን ከእርሱ አይብሉ። 46 በአንድ ቤትም ይበላ፤ ከሥጋውም አንዳች ከቤት ወደ ሜዳ አታውጡ፤ አጥንቱንም አትስበሩ። 47 የእስራኤልም ማኅበር ሁሉ ያድርጉት። 48 የእግዚአብሔርን ፋሲካ ያደርግ ዘንድ ወደ እናንተ የመጣ መጻተኛ ቢኖር ወንዱን ሁሉ ትገርዛለህ፤ ያን ጊዜም ፋሲካ ያደርግ ዘንድ ይገባል፤ እንደ ሀገር ልጅም ይሆንላችኋል፤ ያልተገረዘ ሁሉ ግን ከእርሱ አይብላ። 49 ለሀገር ልጅ፥ በእናንተ መካከልም ለሚቀመጡ መጻተኞች አንድ ሥርዐት ይሆናል።” 50 የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንደ አዘዘ እንዲሁ አደረጉ። 51 በዚያም ቀን እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ከሠራዊታቸው ጋር ከግብፅ ምድር አወጣቸው። |