ሆሴዕ 8:13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) መሥዋዕትንም ቢሠዉ፥ ሥጋንም ቢበሉ፤ እግዚአብሔር አይቀበላቸውም፤ አሁንም በደላቸውን ያስባል፤ በኀጢአታቸውም ይበቀላቸዋል፤ እነርሱም ወደ ግብፅ ይመለሳሉ፤ በአሦርም ርኩስ ነገርን ይበላሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ለእኔ የሚገባውን መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ሥጋውንም ይበላሉ፤ እግዚአብሔር ግን በእነርሱ አልተደሰተም፤ ስለዚህ ክፋታቸውን ያስታውሳል፤ ኀጢአታቸውን ይቀጣል፤ ወደ ግብጽም ይመለሳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የተመረጠውን መሥዋዕቴን ያቀርባሉ፥ ሥጋንም ያርዳሉ፥ ይበላሉም፤ ጌታ ግን በእነርሱ ደስ አይሰኝም፤ በደላቸውን አሁን ያስታውሳል፥ ስለ ኃጢአታቸውም ይቀጣቸዋል፤ እነርሱም ወደ ግብጽ ይመለሳሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እነርሱ ለእኔ ምርጥ መሥዋዕት ቢያቀርቡ፥ የመሥዋዕቱንም ሥጋ ቢበሉ እኔ እግዚአብሔር አልቀበላቸውም። አሁን በደላቸውን አስቤ በኃጢአታቸው እቀጣቸዋለሁ፤ ወደ ግብጽም ይመለሳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) መሥዋዕቴን ያቀርባሉ፥ ሥጋንም ያርዳሉ፥ ይበላሉም፥ እግዚአብሔር ግን አይቀበላቸውም፥ በደላቸውንም ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይቀጣል፥ እነርሱም ወደ ግብጽ ይመለሳሉ። |
አሁንም ሂድ፤ ይህንም ሕዝብ ወደ ነገርሁህ ቦታ ምራ፤ እነሆ፥ መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ ነገር ግን በምጐበኝበት ቀን ኀጢአታቸውን አመጣባቸዋለሁ” አለው።
“የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምንድን ነው?” ይላል እግዚአብሔር፤ “የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤአለሁ፤ የበሬና የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም።
እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፥ “መቅበዝበዝን ወድደዋል፤ እግራቸውንም አልከለከሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም፤ በደላቸውንም አሁን ያስባል፤ ኀጢአታቸውንም ይጐበኛል።”
ስለ ምንስ ከሳባ ዕጣንን፥ ከሩቅም ሀገር ቀረፋን ታቀርቡልኛላችሁ? የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን አልቀበለውም፤ ቍርባናችሁም ደስ አያሰኘኝም።
የእስራኤል ቤት እነርሱን በተከተሉ ጊዜ እርስዋ በደልን ታሳስባለች፤ ከእንግዲህም ወዲያ መታመኛ አትሆንላቸውም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
እግዚአብሔርንም ለመሻት ከበጎቻቸውና ከላሞቻቸው ጋር ይሄዳሉ፤ ነገር ግን እርሱ ከእነርሱ ተለይቶአልና አያገኙትም።
ወደ ከንቱ ነገር ተመለሱ፤ እንደ ጠማማ ቀስትም ሆኑ፤ አለቆቻቸውም ከምላሳቸው ስንፍና የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ይህም በግብፅ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል።
ወንጀላቸውን አንድ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው እንደ አሰቡ ክፋታቸውን ሁሉ ዐሰብሁ፤ አሁንም ክፋታቸው ከብባቸዋለች፤ በደላቸውም በፊቴ አለች።
ስለዚህ እነሆ ከግብፅ ጕስቍልና የተነሣ ሸሽተው ይሄዳሉ፤ ሜምፎስም ትቀበላቸዋለች፤ በማከማስም ይቀብሩአቸዋል፤ ጥፋትም ወርቃቸውን ይወርሳል፥ እሾህም በድንኳኖቻቸው ውስጥ ይበቅላል።
የበቀል ወራት መጥቶአል፤ የፍዳም ወራት ደርሶአል፤ እስራኤልም እንደ አበደ ነቢይና ርኩስ መንፈስ እንደ አለበት ሰው ይታመማል፤ ከኀጢአትህና ከጠላትነትህ ብዛት የተነሣም ቍጣህን አበዛህ።
“እኔ ከምድር አሕዛብ ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ፤ ስለዚህ ስለ ኀጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ።”
የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁንና የእህሉን ቍርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ የድኅነት መሥዋዕታችሁንም አልመለከትም።
ሳይገባው፥ የጌታችን ሥጋም እንደ ሆነ ሳያውቅ፥ ሰውነቱንም ሳያነጻ፥ የሚበላና የሚጠጣ ለራሱ ፍርዱንና መቅሠፍቱን ይበላል፤ ይጠጣልም።
ጊዜው ሳይደርስ ዛሬ ለምን ትመረምራላቸሁ? በጨለማ ውስጥ የተሰወረውንም የሚያበራ፥ የልብን አሳብም የሚገልጥ ጌታችን ይመጣል፤ ያንጊዜ ሁሉም ዋጋውን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል።
ከእንግዲህ ወዲህ ተመልሰህ አታያትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር በመርከብ ወደ ግብፅ ይመልስሃል፤ በዚያም ለጠላቶቻችሁ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮች ትሆናላችሁ፤ የሚራራላችሁም አይኖርም።”
ታላቂቱም ከተማ በሦስት ተከፋፈለች፤ የአሕዛብም ከተማዎች ወደቁ። ታላቂቱም ባቢሎን የብርቱ ቍጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሔር ፊት ታሰበች።
ሳሙኤልም ሳኦልን፥ “በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።