አሞጽ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእስራኤል በደልና ቅጣት 1 የእስራኤል ቤት ሆይ! እኔ እግዚአብሔር በእናንተና ከግብፅ ምድር በአወጣሁት ወገን ሁሉ ላይ የተናገርሁትን ይህን ቃል ስሙ፤ እንዲህም አልሁ፦ 2 “እኔ ከምድር አሕዛብ ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ፤ ስለዚህ ስለ ኀጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ።” 3 በውኑ ሁለት ሰዎች ሳይተያዩ በአንድነት ይሄዳሉን? 4 ወይስ አንበሳ የሚነጥቀው ነገር ሳያገኝ በጫካው ውስጥ በከንቱ ያገሣልን? ወይስ የአንበሳ ደቦል አንዳች ሳይዝ በመደቡ ሆኖ በከንቱ ይጮኻልን? 5 ወይስ ወፍ፥ አጥማጅ ከሌለው፥ በምድር ላይ በወጥመድ ይያዛልን? ወይስ ወስፈንጠር አንዳች ሳይዝ ከምድር በከንቱ ይፈናጠራልን? 6 ወይስ በከተማ ውስጥ መለከት ሲነፋ ሕዝቡ አይደነግጡምን? ወይስ እግዚአብሔር ያላዘዘው ክፉ ነገር በከተማ ላይ ይመጣልን? 7 ጌታ እግዚአብሔር ለባሪያዎቹ ለነቢያት ያልገለጠውንና ያልነገረውን ምንም አያደርግምና። 8 አንበሳው አገሣ፤ የማይፈራ ማን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ትንቢት የማይናገር ማን ነው? የሰማርያ ውድቀት 9 በፋርስ ሀገሮችና በግብፅ ሀገሮች ዐውጁና፥ “በሰማርያ ተራሮች ላይ ተሰብሰቡ፤ በውስጥዋም የሆነውን ታላቁን ተአምር፥ በመካካልዋም ያለውን ግፍ ተመልከቱ” በሉ። 10 “በፊቷ የሚመጣባትን አላወቀችም፤ ይላል እግዚአብሔር፤ በሀገራቸው ቅሚያንና ግፍን የሚያከማቹ ናቸው።” 11 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እስከ ጢሮስ በአለው ዙሪያሽ ድረስ ምድርሽ ይጠፋል፥ ብርታትሽንም ከአንቺ ያወርዳል፤ ሀገሮችሽም ይበዘበዛሉ።” 12 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እረኛ ከአንበሳ አፍ ሁለት እግርን ወይም የጆሮን ጫፍ እንደሚያድን፥ እንዲሁ በሰማርያ በአሕዛብ ፊትና በደማስቆ የተቀመጡት የእስራኤል ልጆች ይድናሉ። 13 “ካህናት ሆይ! ስሙ፤ በያዕቆብም ቤት ላይ መስክሩ፥ ይላል ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሔር። 14 እስራኤልን ስለ ኀጢአቱ በምበቀልበት ቀን የቤቴልን መሠዊያዎች ደግሞ እበቀላለሁ፤ የመሠዊያው ቀንዶች ይሰበራሉ፤ ወደ ምድርም ይወድቃሉ። 15 የክረምቱንና የበጋዉን ቤት እመታለሁ፤ በዝሆንም ጥርስ የተለበጡት ቤቶች ይጠፋሉ፤ ሌሎችም ታላላቆች ቤቶች ይፈርሳሉ” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |