ዘፀአት 32 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የወርቅ ጥጃው ምስል ( ዘዳ. 9፥6-29 ) 1 ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው፥ “ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን” አሉት። 2 አሮንም፥ “በሚስቶቻችሁና በሴቶች ልጆቻችሁ ጆሮ ያሉትን የወርቅ ጌጦች አምጡልኝ” አላቸው። 3 ሕዝቡም ሁሉ በጆሮዎቻቸው ያሉትን የወርቅ ጌጦች ወደ አሮን አመጡለት። 4 ከእጃቸውም ተቀብሎ በመቅረጫ ቀረጸው፤ ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፤ እርሱም፥ “እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው” አላቸው። 5 አሮንም በአየው ጊዜ መሠዊያውን በፊቱ ሠራ፤ አሮንም፥ “ነገ የእግዚአብሔር በዓል ነው” ሲል አወጀ። 6 አሮንም በነጋው ማልዶ ተነሣ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ሠዋ፤ የደኅንነት መሥዋዕትንም አቀረበ ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ። 7 እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው እንዲህም አለው፥ “ከግብፅ ምድር ያወጣኻቸው ሕዝብህ በድለዋልና ሂድ፤ ፈጥነህ ውረድ። 8 ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስል ለራሳቸው አደረጉ፤ ሰገዱለትም፤ ሠዉለትም፤ 9 ‘እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው’ አሉ። 10 አሁንም ተቈጥቼ አጠፋቸው ዘንድ ተወኝ፤ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።” 11 ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፤ አለም፥ “አቤቱ፥ በታላቅ ኀይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር በአወጣኸው በሕዝብህ ላይ ለምን ተቈጣህ? 12 ግብፃውያንስ፦ ‘በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው’ ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፤ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ። 13 ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፤ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፤ ለዘለዓለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸው ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም ዐስብ።” 14 እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ይቅር አለ። 15 ሙሴም ተመለሰ፤ ሁለቱንም የምስክር ጽላት በእጁ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ የድንጋይ ጽላቱም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር። 16 ጽላቱ የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቱ ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ። 17 ኢያሱም ሲጮሁ የሕዝቡን ድምፅ ሰምቶ ሙሴን፥ “የሰልፍ ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ አለ” አለው። 18 ሙሴም፥ “ይህ የድል ነሺዎች ወይም የድል ተነሺዎች ድምፅ አይደለም፤ ነገር ግን የወይን ስካር ድምፅ እሰማለሁ” አለው። 19 እንዲህም ሆነ፤ ወደ ሰፈሩ ሲቀርብ ጥጃውንም ዘፈኑንም አየ፤ የሙሴም ቍጣ ተቃጠለ፤ እነዚያንም ሁለቱን ጽላት ከእጁ ጥሎ ከተራራው በታች ሰበራቸው። 20 የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፤ ፈጨው፤ አደቀቀውም፤ በውኃም ላይ በተነው፤ ለእስራኤልም ልጆች አጠጣቸው። 21 ሙሴም አሮንን፥ “ይህን ታላቅ ኀጢአት ታመጣበት ዘንድ ይህ ሕዝብ ምን አደረገህ?” አለው። 22 አሮንም እንዲህ አለ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በእኔ ላይ አትቈጣ፤ የዚህን ሕዝብ ጠባይ አንተ ታውቃለህ። 23 እነርሱም ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉኝ። 24 እኔም ከእናንተ ወርቅ ያለው ሰው ያምጣልኝ አልኋቸው፤ ሰጡኝም፤ በእሳትም ላይ ጣልሁት፤ ይህም ጥጃ ወጣ።” 25 ሙሴም በጠላቶቻቸው ፊት እንዲነወሩ አሮን ስድ ለቅቆአቸዋልና ሕዝቡ ስድ እንደ ተለቀቀ በአየ ጊዜ፥ 26 ሙሴ በሰፈሩ ደጅ ቆሞ፥ “የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ወደ እኔ ይምጣ” አለ፤ የሌዊ ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። 27 እርሱም፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ላይ ይታጠቅ፤ ሂዱና በሰፈሩ ውስጥ ከበር እስከ በር ተመላለሱ፤ እያንዳንዱም ወንድሙን፥ እያንዳንዱም ጎረቤቱን፥ እያንዳንዱም የቅርቡን ይግደል” አላቸው። 28 የሌዊም ልጆች ሙሴ እንዳለ አደረጉ፤ በዚያም ቀን ከሕዝቡ ሦስት ሺህ ሰዎች ሞቱ። 29 ሙሴም፥ “ዛሬ በረከትን እንዲያወርድላችሁ ከእናንተ እያንዳንዱ ከልጁና፥ ከወንድሙ የተነሣ እግዚአብሔርን በእጃችሁ ደስ አሰኛችሁት” አላቸው። 30 በነጋውም ሙሴ ለሕዝቡ፥ “እናንተ ታላቅ በደል ሠርታችኋል፤ አሁንም አስተሰርይላችሁ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እወጣለሁ፤” አላቸው። 31 ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኀጢአት ሠርተዋል፤ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤ 32 አሁንም ይህን ኀጢአታቸውን ይቅር ትላቸው እንደሆነ ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ ደምስሰኝ” አለ። 33 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “በፊቴ የበደለውን እርሱን ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ። 34 አሁንም ሂድ፤ ይህንም ሕዝብ ወደ ነገርሁህ ቦታ ምራ፤ እነሆ፥ መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ ነገር ግን በምጐበኝበት ቀን ኀጢአታቸውን አመጣባቸዋለሁ” አለው። 35 አሮን የሠራውን ጥጃ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ቀሠፈ። |