ኤርምያስ 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢየሩሳሌም በጠላት መከበብ 1 እናንተ የብንያም ልጆች፥ ክፉ ነገር፥ ታላቅም ጥፋት ከመስዕ ይጐበኛልና ከኢየሩሳሌም ውስጥ ለመሸሽ ጽኑ፤ በቴቁሔ መለከቱን ንፉ፤ በቤትካሪም ላይ ምልክትን አንሡ። 2 ቅምጥል የጽዮን ልጅ ሆይ! ውበትሽ ይጐሳቈላል። 3 እረኞችና መንጎቻቸው ወደ እርስዋ ይመጣሉ፤ በዙሪያዋም ድንኳኖቻቸውን ይተክሉባታል፤ በእጃቸውም መንጋቸውን ያሰማራሉ። 4 በእርስዋ ላይ ሰልፍ አዘጋጁ፤ ተነሡ፥ በቀትርም እንውጣ። ቀኑ መሽቶአልና፥ የቀኑም ጥላ አልፎአልና ወዮልን። 5 ተነሡ በሌሊትም እንውጣ፤ መሠረቶችዋንም እናፍርስ። 6 ኀያል እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ዛፎችዋን ቍረጡ፤ በኢየሩሳሌምም ላይ ኀይልን አፍስሱ ይህች ከተማ የሐሰት ከተማ ናት፤ መካከልዋ ሁሉ ግፍ ብቻ ነው። 7 በጕድጓድ ውኃ እንደሚፈልቅ፥ እንዲሁ ክፋቷ ከእርስዋ ዘንድ ይፈልቃል፤ ግፍና ቅሚያ በእርስዋ ዘንድ ይሰማል፤ ደዌና ቍስልም ሁልጊዜ በፊቷ አለ። 8 ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ነፍሴ ከአንቺ እንዳትለይ፥ አንቺንም ባድማና ወና እንዳላደርግሽ፥ ተግሣጽን ተቀበዪ። የእስራኤል ዐመፀኛነት 9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሰው ወይንን እንደሚቃርም፥ እንዲሁ ከእስራኤል የቀሩትን ይቃርሙአቸዋል፤ እጅህን እንደ ወይን ለቃሚ ወደ እንቅብ ዘርጋ። 10 ይሰሙኝስ ዘንድ ለማን እናገራለሁ? ለማንስ አዳኛለሁ? እነሆ፥ ጆሮአቸው ያልተገረዘች ናት፤ ለመስማትም አይችሉም፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቃል ለስድብ ሆኖባቸዋል፥ ይሰሙት ዘንድ አልፈቀዱምና። 11 ስለዚህ ቍጣዬን መላሁባቸው፤ ታገሥሁ፤ ፈጽሜም አላጠፋኋቸውም፤ በሜዳ በሕፃናት ላይ በጐልማሶችም ጉባኤ ላይ መዓቴን በአንድነት አፈስስባቸዋለሁ፤ ባል ከሚስቱ ጋር ሽማግሌውም ከጎበዙ ጋር ይያያዛልና። 12 እጄን በዚች ምድር በሚኖሩ ላይ እዘረጋለሁና ቤቶቻቸዉ፥ እርሻዎቻቸውም፥ ሴቶቻቸውም በአንድነት ለሌሎች ይሰጣሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ 13 ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ኀጢአትን አድርገዋልና፥ ከሐሳዊ ነቢይ ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉም ሐሰትን አደረጉ። 14 የሕዝቤንም ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን፦ ሰላም ሰላም ይላሉ። 15 ርኩስ ነገርን ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፤ ውርደትንም አላወቁም፤ ስለዚህም ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፤ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥” ይላል እግዚአብሔር። 16 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፤ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች ዕወቁ፤ በእርስዋም ላይ ሂዱ፤ ለነፍሳችሁም መድኀኒትን ታገኛላችሁ፤” እነርሱ ግን፥ “አንሄድባትም” አሉ። 17 እኔም፥ “የመለከቱን ድምፅ አድምጡ” ብዬ ጠባቂዎችን ሾምሁባቸው፤ እነርሱ ግን፥ “አናዳምጥም” አሉ። 18 አሕዛብና የመንጋው ጠባቂዎች ሆይ፥ ስለዚህ ስሙ። 19 ምድር ሆይ፥ ስሚ! እነሆ ቃሌን ስላልሰሙ፥ ሕጌንም ስለ ጣሉ፥ እኔንም ስለ ናቁ በዚህ ሕዝብ ላይ እንደ ሥራቸው ፍሬ፥ ክፉን ነገር አመጣባቸዋለሁ። 20 ስለ ምንስ ከሳባ ዕጣንን፥ ከሩቅም ሀገር ቀረፋን ታቀርቡልኛላችሁ? የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን አልቀበለውም፤ ቍርባናችሁም ደስ አያሰኘኝም። 21 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በዚህ ሕዝብ ላይ ደዌን አሳድራለሁ፤ አባቶችና ልጆችም በአንድነት ይታመማሉ፤ ጎረቤትና ባልንጀራም ይጠፋሉ። ከወደ ሰሜን የሚመጣ ወራሪ 22 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ሕዝብ ከሰሜን ሀገር ይመጣል፤ ታላቅ ሕዝብም ከምድር ዳርቻ ይነሣል። 23 ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፤ ጨካኞች ናቸው፤ ምሕረትም አያደርጉም፤ ድምፃቸው እንደ ባሕር ሞገድ ይተምማል፤ በሰረገላና በፈረሶችም ላይ ይቀመጣሉ፤ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ! እንደ እሳት ያጠፉሻል። 24 ጩኸታቸውን ሰምተን፥ እጃችን ደክማለች፤ ወላድን ሴት ምጥ እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞናል። 25 የጠላት ሰይፍ ከብበዋችኋልና ወደ ሜዳ አትውጡ፤ በመንገድም ላይ አትሂዱ። 26 የሕዝቤ ልጅ ሆይ፥ ማቅ ልበሺ፤ በራስሺም ላይ አመድ ነስንሺ፥ አጥፊ በላያችን በድንገት ይመጣብናልና ለተወዳጅ ልጅ እንደሚደረግ ልቅሶ መራራ ልቅሶ አልቅሺ። 27 በተፈታኝ ሕዝቤ መካከል ፈታኝ አድርጌሃለሁ፤ መንገዳቸውንም በፈተንሁ ጊዜ ታውቀኛለህ። 28 እነርሱ ሁሉ እጅግ ደንቆሮዎች ናቸው፤ በጠማማነት ይሄዳሉ፤ ሁሉም እንደ ናስና ብረት የዛጉ ናቸው። 29 ወናፉን የሚአናፋው ደከመ፤ እርሳሱም በእሳት ቀለጠ፤ አንጥረኛውም መልሶ በከንቱ ያቀልጠዋል፤ ኀጢአታቸውም አልተወገደም። 30 እግዚአብሔር ንቆአቸዋልና የተናቀ ብር ብላችሁ ጥሩአቸው። |