ሆሴዕ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእስራኤል ሕዝብ ጣዖት በማምለካቸው መገሠጻቸው 1 በብብታቸው እንደ መሬት፤ በእግዚአብሔርም ቤት እንደ ንስር ይመጣል። ቃል ኪዳኔን ተላልፈዋልና፥ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና። 2 አምላክ ሆይ! እኛ እስራኤል ዐወቅንህ ብለው ወደ እኔ ይጮኻሉ። 3 እስራኤል ደግነቱን ጥሎአልና፤ ጠላትም ያሳድደዋልና። 4 ራሳቸውን አነገሡ፤ ከእኔም ዘንድ አይደለም፤ አለቆችንም አደረጉ፤ እኔም አላወቅሁም፤ ለጥፋታቸውም ከብራቸውና ከወርቃቸው ጣዖታትን ለራሳቸው አደረጉ። 5 ሰማርያ ሆይ! እምቦሳሽን መልሺ፤ ቍጣዬም በላያቸው ነድዶአል፤ እስከ መቼም ድረስ ንጹሕ ሊሆኑ አይችሉም። 6 ይህ ደግሞ በእስራኤል ዘንድ ነው፤ ሠራተኛ ሠራው፤ እርሱም አምላክ አይደለም፤ ሰማርያ ሆይ! እንቦሳሽ ተቅበዝብዞአልና። 7 ነፋስን ዘርተዋልና ዐውሎ ነፋስን አጨዱ፤ ለነዶአቸውም ኀይል የለውም፤ ከፍሬውም ዱቄት አይገኝም፤ ቢገኝም ጠላት ይበላዋል። 8 እስራኤል ተውጦአል፤ በአሕዛብም መካከል ዛሬ እንደ ግትቻ ዕቃ ሆኖአል። 9 ለብቻውም እንደሚቀመጥ እንደ ምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ወጥተዋል፤ ኤፍሬምም እንደ ገና ለመለመ፤ እጅ መንሻንም ወደደ። 10 ስለዚህ ለአሕዛብ አልፈው ይሰጣሉ፤ እኔም አሁን እቀበላቸዋለሁ፤ ንጉሥንና አለቆችንም ይቀቡ ዘንድ ፈጽመው ያንሣሉ። 11 ኤፍሬም መሠዊያን አብዝቶአልና የወደደው መሠዊያ ለኀጢአት ሆነበት። 12 ብዙ ሕጎችን እጽፍለታለሁ፤ ነገር ግን ሥርዐቱና የተወደደው መሠዊያው እንደ እንግዳ ነገር ተቈጠሩ። 13 መሥዋዕትንም ቢሠዉ፥ ሥጋንም ቢበሉ፤ እግዚአብሔር አይቀበላቸውም፤ አሁንም በደላቸውን ያስባል፤ በኀጢአታቸውም ይበቀላቸዋል፤ እነርሱም ወደ ግብፅ ይመለሳሉ፤ በአሦርም ርኩስ ነገርን ይበላሉ። 14 እስራኤል ፈጣሪውን ረስቶአል፤ መስገጃዎችንም ሠርቶአል፤ ይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች አብዝቶአል፤ እኔ ግን በከተሞች ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ መሠረቶቻቸውንም ትበላለች። |