ዘዳግም 28 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በታዛዥነት የሚገኝ በረከት ( ዘሌ. 26፥3-13 ፤ ዘዳ. 7፥12-24 ) 1 “እንዲህም ይሆናል፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽመህ ብትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ትእዛዙን ሁሉ ብታደርግ፥ ብትጠብቅም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከምድር አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል። 2 የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል፤ ያገኙህማል። 3 አንተ በከተማ ቡሩክ ትሆናለህ፤ በእርሻም ቡሩክ ትሆናለህ። 4 የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የከብትህም ፍሬ፥ የላምህም መንጋ፥ የበግህም መንጋ ቡሩክ ይሆናል። 5 መዛግብትህና የቀረውም ሁሉ ቡሩክ ይሆናል። 6 አንተም በመግባትህ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ቡሩክ ትሆናለህ። 7 “እግዚአብሔርም ከእግርህ በታች ይወድቁ ዘንድ የሚቃወሙህን ጠላቶችህን በእጅህ ይጥላቸዋል፤ በአንድ መንገድ ይመጡብሃል፤ በሰባትም መንገድ ከፊትህ ይሸሻሉ። 8 እግዚአብሔር በረከቱን በአንተ ላይ፥ በጎተራህ፥ በእህልህም ሥራ ሁሉ እንዲወርድ ይልካል፤ አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህም ምድር ይባርክሃል። 9 የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትሰማ፥ በመንገዱም ብትሄድ፥ እግዚአብሔር ለአባቶችህ እንደ ማለ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል። 10 የምድር አሕዛብም ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር ስም በአንተ ላይ እንደ ተጠራ አይተው ይፈሩሃል። 11 አምላክህ እግዚአብሔርም እርስዋን ይሰጥህ ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው በምድርህ ላይ፥ በሆድህ ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ፥ ከብቶችህን በማብዛት እግዚአብሔር በጎነቱን ያበዛልሃል። 12 እግዚአብሔርም ለምድርህ በወራቱ ዝናብን ይሰጥ ዘንድ፥ የእጅህንም ሥራ ሁሉ ይባርክ ዘንድ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ ለብዙ አሕዛብም ታበድራለህ፥ አንተ ግን ከማንም አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብን ትገዛለህ፥ አንተን ግን እነርሱ አይገዙህም። 13 ዛሬም ያዘዝሁህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሰምተህ ብትጠብቃት፥ ብታደርጋትም፥ እግዚአብሔር ራስ ያደርግሃል እንጂ ጅራት አያደርግህም፤ ሁልጊዜም በላይ እንጂ በታች አትሆንም። 14 ዛሬም ካዘዝሁህ ከእነዚህ ቃሎች ወደ ቀኝ፥ ወደ ግራም ፈቀቅ ባትል፥ ታመልካቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት ባትከተል። በማይታዘዙ ላይ የሚደርስ ርግማን ( ዘሌ. 26፥14-46 ) 15 “ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዐቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ፥ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል፤ ያገኙህማል። 16 በከተማ ርጉም ትሆናለህ፤ በእርሻም ርጉም ትሆናለህ። 17 መዛግብትህና የቀረውም ርጉማን ይሆናሉ። 18 የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የላምህም መንጋ፥ የበግህም መንጋ ርጉማን ይሆናሉ። 19 አንተ በመግባትህና በመውጣትህም ርጉም ትሆናለህ። 20 እኔን ስለተውኸኝ፥ ስለ ሥራህ ክፋት፥ እስክትጠፋ፥ ፈጥነህም እስክታልቅ ድረስ በምትሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር ችግርን፥ ረኃብን፦ ቸነፈርንም ይልክብሃል። 21 እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ከምትገባባት ምድር እስኪያጠፋህ ድረስ ሞትን ያመጣብሃል። 22 እግዚአብሔር በክሳት፥ በንዳድም፥ በጥብሳትም፥ በትኵሳትም፥ በድርቅም፥ በዋግም፥ በአረማሞም ይመታሃል፤ እስክትጠፋም ድረስ ያሳድዱሃል። 23 በራስህም ላይ ሰማይ ናስ ይሆንብሃል፤ ከእግርህም በታች ምድሪቱ ብረት ትሆንብሃለች። 24 እግዚአብሔር የምድርህን ዝናብ ጭጋግ ያደርጋል፤ እስክትጠፋም ድረስ ከሰማይ አፈር ይወርድብሃል። 25 “እግዚአብሔር ከጠላቶችህ ፊት የተመታህ ያደርግሃል፤ በአንድ መንገድ ትወጣባቸዋለህ፤ በሰባት መንገድም ከእነርሱ ትሸሻለህ፤ በምድርም መንግሥታት ሁሉ የተበተንህ ትሆናለህ። 26 ሬሳህ ለሰማይ ወፎች ሁሉ፥ ለምድርም አራዊት መብል ይሆናል፤ የሚቀብርህም አታገኝም። 27 እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በግብፅ ቍስል፥ በእባጭም፥ በቋቁቻም፥ በችፌም ይመታሃል። 28 እግዚአብሔር በዕብደት፥ በዕውርነት፥ በልብ ድንጋጤም ይመታሃል። 29 ዕውር በጨለማ እንደሚዳብስ በቀትር ጊዜ ትዳብሳለህ፤ መንገድህም የቀና አይሆንም፤ በዘመንህም ሁሉ የተገፋህ፥ የተዘረፍህም ትሆናለህ፤ የሚረዳህም የለም። 30 ሚስት ታገባለህ፤ ሌላም ሰው ይነጥቅሃል፤ ቤት ትሠራለህ፤ በእርሱም አትቀመጥበትም፤ ወይን ትተክላለህ፤ ከእርሱም አትለቅምም። 31 በሬህ በፊትህ ይታረዳል፤ ከእርሱም አትበላም። አህያህ ከእጅህ በግድ ይወሰዳል፤ ወደ አንተም አይመለስም፤ በጎችህ ለጠላቶችህ ይሰጣሉ፤ የሚረዳህም አታገኝም። 32 ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለሌላ ሕዝብ ይሰጣሉ፤ ራሳቸውንም ሲመቱአቸው በዐይኖችህ ታያለህ፤ ልታደርገውም የምትችለው የለም። 33 የምድርህን ፍሬ፥ ድካምህንም ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ አንተም ሁልጊዜ የተጨነቅህ፥ የተገፋህም ትሆናለህ። 34 ዐይኖችህም ከሚያዩት የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ። 35 እግዚአብሔር ልትድን በማትችልበት በክፉ ቍስል ጕልበትህንና ጭንህን ከእግርህ ጫማ እስከ አናትህ ድረስ ይመታሃል። 36 “እግዚአብሔርም አንተን፥ በአንተም ላይ የምትሾማቸውን አለቆችህን አንተና አባቶችህ ወዳላወቃችኋቸው ሕዝብ ይወስድሃል፤ በዚያም ሌሎችን የእንጨትና የድንጋይ አማልክትን ታመልካለህ። 37 እግዚአብሔርም ወደ እነርሱ በሚወስድህ አሕዛብ መካከል ሁሉ የደነገጥህ፥ ለምሳሌና ለተረትም ትሆናለህ። 38 ብዙ ዘርም ወደ እርሻ ታወጣለህ፤ አንበጣም ይበላዋልና ጥቂት ትሰበስባለህ። 39 ወይን ትተክላለህ፤ ታበጀውማለህ፤ ከወይኑም አትጠጣም፤ ክፉ ትልም ይበላዋልና በእርሱ ደስ አይልህም። 40 የወይራ ዛፍ በሀገርህ ሁሉ ይሆንልሃል፤ ፍሬውም ይረግፋልና ዘይቱን አትቀባም። 41 ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ትወልዳለህ፤ ማርከው ይወስዷቸዋልና አይቀሩልህም። 42 ዛፍህን ሁሉ፤ የምድርህንም ፍሬ ሁሉ ኩብኩባ ያጠፋዋል። 43 በአንተ መካከል ያለ መጻተኛ በአንተ ላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አንተ ግን ዝቅ ዝቅ ትላለህ። 44 እርሱ ያበድርሃል፤ አንተ ግን አታበድረውም፤ እርሱ ራስ ይሆናል፤ አንተም ጅራት ትሆናለህ። 45 የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ስላልሰማህ፥ ያዘዘህንም ትእዛዙንና ሥርዐቱን ስላልጠበቅህ፥ እስክትጠፋ ድረስ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይወርዱብሃል፤ ያሳድዱህማል፤ ያገኙህማል። 46 በአንተም በልጅ ልጅህም ላይ ለዘለዓለም ለምልክትና ለድንቅ ይሆናሉ። 47 “ሁሉን አብዝቶ ስለ ሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍሥሓና በቀና ልብ አላመለክኸውምና፥ 48 በራብና በጥማት፥ በዕራቁትነትም፥ ሁሉንም በማጣት እግዚአብሔር ለሚልክብህ ለጠላቶችህ ትገዛለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በአንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭናል። 49 እግዚአብሔርም ንስር እንደሚበርር ከሩቅ ሀገር፥ ከምድር ዳር ቋንቋቸውን የማትሰማውን ሕዝብ፥ 50 ፊቱ የሚያስፈራውን፥ የሽማግሌውንም ፊት የማያፍረውን፥ ሕፃኑንም የማይምረውን ሕዝብ ያመጣብሃል። 51 እስክትጠፋም ድረስ የከብትህን ፍሬ፥ የምድርህንም ፍሬ ይበላል፤ እስኪያጠፋህም ድረስ እህልህን፥ ወይንህንም፥ ዘይትህንም፥ የላምህንና የበግህንም መንጋ አይተውልህም። 52 በሀገርህ ሁሉ ያሉ፥ ትታመንባቸው የነበሩ፥ የረዘሙ፥ የጸኑም ቅጥሮች እስኪፈርሱ ድረስ፥ በከተሞችህ ሁሉ ያጠፋሃል፤ አምላክህም እግዚአብሔር በሰጠህ ምድር ሁሉ፥ በደጆች ሁሉ ያስጨንቅሃል። 53 ጠላቶችህም በሀገርህ ውስጥ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር የሚሰጥህን የሆድህን ፍሬ፥ የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ። 54 በአንተ ዘንድ የተደላደለና የተቀማጠለ ሰው በወንድሙ፥ አብራውም በምትተኛ በሚስቱ፥ በቀሩትም ልጆቹ ይቀናል፤ 55 በከተሞችህ ሁሉ ውስጥ ጠላቶችህ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሌላ ነገር የቀረው የለምና ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ለአንዱ አይሰጥም። 56 በአንተ ዘንድ የተለሳለሰችና የተቀማጠለች፥ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ የእግር ጫማዋን በምድር ላይ ያላደረገችው ሴት፥ አቅፋ በተኛችው ባልዋ፥ በወንድና በሴት ልጅዋም ትቀናለች፥ 57 ከአካልዋ የሚወጣውን የእንግዴ ልጅ፥ የምትወልዳቸውንም ልጆች፤ በደጆችህ ውስጥ ጠላቶችህ፤ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሁሉን ስላጣች በስውር ትበላቸዋለች። 58 “በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ታደርግ ዘንድ፥ ይህንም ክቡርና ምስጉን ስም እግዚአብሔር አምላክህን ትፈራ ዘንድ ባትሰማ፥ 59 እግዚአብሔር መቅሠፍትህን፥ የዘርህንም መቅሠፍት፥ ታላቅና የሚያስፈራ መቅሠፍትን፥ ለብዙ ጊዜ የሚኖር ክፉ ደዌና ሕማምን ሁሉ ያመጣብሃል። 60 የፈራኸውንም የግብፅ ደዌ ሁሉ እንደገና ያመጣብሃል፤ ያጣብቅብህማል። 61 ደግሞም ይህ ሕግ ባለበት መጽሐፍ ውስጥ ያልተጻፈውን ደዌ ሁሉ፥ መቅሠፍትንም ሁሉ እስክትጠፋ ድረስ እግዚአብሔር ያመጣብሃል። 62 የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁምና ከብዛታችሁ የተነሣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የነበረው ቍጥራችሁ ጥቂት ሆኖ ይቀራል። 63 እግዚአብሔርም በጎ ያደርግልህ ዘንድ፥ ያበዛህም ዘንድ ደስ ይለው እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ሲያጠፋህ፥ ሲያፈርስህም ደስ ይለዋል፤ ትወርሳትም ዘንድ ከምትገባባት ምድር ትነቀላለህ ። 64 እግዚአብሔርም ከምድር ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ወደ አሉ አሕዛብ ሁሉ ይበትንሃል፤ በዚያም አንተና አባቶችህ ያላወቃችኋቸውን ሌሎችን አማልክት፥ እንጨትንና ድንጋይን ታመልካለህ። 65 በእነዚያም አሕዛብ መካከል ዕረፍት አታገኝም፤ ለእግርህም ጫማ ማረፊያ አይሆንም፤ በዚያም እግዚአብሔር ተንቀጥቃጭ ልብ ፥ ፈዛዛ ዐይን፥ ደካማም ነፍስ ያመጣብሃል። 66 ሕይወትህ በዐይኖችህ ፊት የተሰቀለች ትሆናለች፤ ሌሊትና ቀንም ትደነግጣለህ፤ በሕይወትህም አትታመንም፤ 67 ከፈራህበት ከልብህ ፍርሀት የተነሣ፥ በዐይንህም ካየኸው የተነሣ፥ ሲነጋ እንዴት ይመሽ ይሆን? ትላለህ፤ ሲመሽም እንዴት ይነጋ ይሆን? ትላለህ። 68 ከእንግዲህ ወዲህ ተመልሰህ አታያትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር በመርከብ ወደ ግብፅ ይመልስሃል፤ በዚያም ለጠላቶቻችሁ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮች ትሆናላችሁ፤ የሚራራላችሁም አይኖርም።” |