Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ሆሴዕ 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእስራኤል ሕዝብ ጣዖት በማምለካቸው እንደ ተገሠጹ

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ቃል ኪዳኔን ስላፈረሱና ሕጌን ስለ ተላለፉ በቤቴ ላይ ጠላት እንደ ጆፌ አሞራ ያንዣበበ ስለ ሆነ የማስጠንቀቂያ መለከት ንፉ!”

2 እነርሱም፥ “አምላክ ሆይ! እኛ ሕዝብህ እናውቅሃለን” እያሉ ወደ እኔ ይጮኻሉ፤

3 ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በጎ ነገርን ስለ ጠሉ ጠላት ያሳድዳቸዋል።

4 “ያለ እኔ ፈቃድ ነገሥታትን አነገሡ፤ እኔን ሳይጠይቁ መሳፍንትን መርጠው ሾሙ፤ ከብራቸውና ከወርቃቸው ለገዛ ራሳቸው መጥፊያ የሆኑትን ጣዖቶችን ሠሩ።

5 የሰማርያ ሕዝብ ሆይ! በጥጃ ምስል የተሠራ ጣዖታችሁን ተጸይፌአለሁ፤ ቊጣዬ በእናንተ ላይ እንደ እሳት ይነዳል፤ ከበደል የማትነጹት እስከ መቼ ነው?

6 ይህ በጥጃ ምስል የተሠራ ጣዖት በአናጢ እጅ የተሠራ ስለ ሆነ አምላክ ሊሆን አይችልም፤ ስለዚህ በጥጃ ምስል የተሠራው የሰማርያ ጣዖት ተሰባብሮ ይወድቃል።

7 እነርሱ ነፋስን ዘርቶ ዐውሎ ነፋስን እንደሚያጭድ ይሆናሉ፤ ዛላ የሌለው የእህል አገዳ ምግብ ሊሆን አይችልም፤ ፍሬ ቢኖረውም እንኳ የሚበሉት ባዕዳን በሆኑ ነበር።

8 የእስራኤል ሕዝብ በአሕዛብ መካከል ተውጠው ቀርተዋል፤ ዋጋ እንደሌለው ዕቃም ሆነዋል።

9 ብቻውን እንደሚንከራተት የምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ሄዱ፤ እንዲጠብቁአቸውም ዋጋ በመክፈል መንግሥታትን ተለማመጡ፤

10 መንግሥታትን ለመለማመጥ ዋጋ ቢከፍሉም እንኳ እኔ በአንድነት እሰበስበዋለሁ፤ ነገሥታትና መሳፍንት በሚያደርጉባቸው ጭቈና እየመነመኑ ይሄዳሉ።

11 “የእስራኤል ሕዝብ ብዙ መሠዊያዎችን ለኃጢአት ማስተስረያ ብለው ሠርተዋል፤ ነገር ግን እነዚያ መሠዊያዎች የኃጢአት መሥሪያ ቦታዎች ሆኑ።

12 እኔ ለእነርሱ ከሕጌ ብዙ መመሪያዎችን ጽፌ ሰጠኋቸው፤ እነርሱ ግን እንደ እንግዳ ነገር ቈጠሩት።

13 እነርሱ ለእኔ ምርጥ መሥዋዕት ቢያቀርቡ፥ የመሥዋዕቱንም ሥጋ ቢበሉ እኔ እግዚአብሔር አልቀበላቸውም። አሁን በደላቸውን አስቤ በኃጢአታቸው እቀጣቸዋለሁ፤ ወደ ግብጽም ይመለሳሉ።

14 “የእስራኤል ሕዝብ ለራሳቸው ታላላቅ ቤተ መንግሥቶች ሠርተዋል፤ እኔን ፈጣሪአቸውን ግን ረስተዋል፤ የይሁዳም ሕዝብ ብዙ የተመሸጉ ከተሞችን ሠርተዋል፤ ስለዚህ ከተሞቻቸውንና ምሽጎቻቸውን የሚያቃጥል እሳት እልክባቸዋለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos