ሆሴዕ 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሆሴዕ በእስራኤል የሚደርሰውን ቅጣት እንደ ተነበየ 1 እስራኤል ሆይ! ከአምላክህ ርቀህ አመንዝረሃልና እንደ አሕዛብ ደስ አይበልህ፤ ሐሴትንም አታድርግ፤ ከእህሉና ከወይኑ አውድማ ሁሉ ይልቅ የግልሙትና ዋጋን ወድደሃል። 2 የእህሉ አውድማና የወይኑ መጭመቂያ አላወቃቸውም፤ ወይኑም ጐደለባቸው። 3 በእግዚአብሔር ምድር ላይ አይቀመጡም፤ ኤፍሬምም በግብፅ ይቀመጣል፤ በአሦርም ርኩስ ነገርን ይበላሉ። 4 ለእግዚአብሔርም የወይን ጠጅን ቍርባን አያቀርቡም፤ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘውም፤ እንደ ኀዘንም እንጀራ ይሆንባቸዋል፤ የሚበላውም ሁሉ ይረክሳል፤ እንጀራቸውም ለሰውነታቸው ይሆናል እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይገባም። 5 በዓመት በዓል ቀንና በእግዚአብሔር በዓል ቀን ምን ታደርጋላችሁ? 6 ስለዚህ እነሆ ከግብፅ ጕስቍልና የተነሣ ሸሽተው ይሄዳሉ፤ ሜምፎስም ትቀበላቸዋለች፤ በማከማስም ይቀብሩአቸዋል፤ ጥፋትም ወርቃቸውን ይወርሳል፥ እሾህም በድንኳኖቻቸው ውስጥ ይበቅላል። 7 የበቀል ወራት መጥቶአል፤ የፍዳም ወራት ደርሶአል፤ እስራኤልም እንደ አበደ ነቢይና ርኩስ መንፈስ እንደ አለበት ሰው ይታመማል፤ ከኀጢአትህና ከጠላትነትህ ብዛት የተነሣም ቍጣህን አበዛህ። 8 ኤፍሬም ከእግዚአብሔር ጋር ጉበኛ ነበረ፤ አሁን ግን ነቢዩ በመንገዱ ሁሉ ላይ ክፉ ወጥመድ ሆነ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ርኵሰትን አደረጉ። 9 በጊብዓ ዘመን እንደ ነበረ እጅግ ረከሱ፤ እርሱም በደላቸውን ያስባል፤ ኀጢአታቸውንም ይበቀላል። 10 እስራኤልን በምድረ በዳ እንደ አለ ወይን ሆኖ አገኘሁት፤ አባቶቻችሁንም በመጀመሪያዋ ዓመት እንደ በለስ በኵራት ሆነው አየኋቸው፤ እነርሱ ግን ወደ ብዔልፌጎር መጡ፤ ለነውርም ተለዩ፤ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ። 11 ኤፍሬምም እንደ ወፍ በረረ፤ ክብራቸው ከመፅነስና ከመውለድ፥ ከማማጥም ነበር። 12 ልጆቻቸውንም ቢያሳድጉ ከሰው ለይች ልጅ አልባ አደርጋቸዋለሁ፤ ሥጋዬ ከእነርሱ ነውና ወዮላቸው! 13 እኔ እንደ አየሁ የኤፍሬም ልጆች ለወጥመድ ተሰጥተዋል፤ ኤፍሬምም ልጆቹን ወደ ገዳዮች አወጣ። 14 አቤቱ! ስጣቸው፤ ምን ትሰጣቸዋለህ? መካን ማኅፀንን፥ የደረቁትንም ጡቶች ስጣቸው። 15 ክፋታቸውም ሁሉ በጌልገላ አለ፤ በዚያ ጠልቻቸዋለሁ፤ ስለ ሠሩት ክፋት ከቤቴ አሳድዳቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ አልወድዳቸውም፤ አለቆቻቸው ሁሉ ዐመፀኞች ናቸውና። 16 ኤፍሬም ታመመ፤ ሥሩም ደረቀ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ፍሬ አያፈራም፤ ደግሞም ቢወልዱ የተወደደውን የማኅፀናቸውን ፍሬ እገድላለሁ። 17 አልሰሙትምና እግዚአብሔር ይጥላቸዋል፤ በአሕዛብም መካከል ተቅበዝባዦች ይሆናሉ። |