ሆሴዕ 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በውጭም ወንበዴዎች ቀምተዋልና እስራኤልን እፈውስ ዘንድ በወደድሁ ጊዜ የኤፍሬም ኀጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ። 2 ወንጀላቸውን አንድ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው እንደ አሰቡ ክፋታቸውን ሁሉ ዐሰብሁ፤ አሁንም ክፋታቸው ከብባቸዋለች፤ በደላቸውም በፊቴ አለች። 3 ነገሥታቱ በክፋታቸው፥ አለቆቹም በሐሰታቸው ደስ ተሰኙ። 4 ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፤ ጋጋሪ እንደሚያነድድበት እንደ ምድጃ ናቸው፤ ሁሉም እስኪቦካ ድረስ እሳትን መቈስቈስና እርሾን መለወስ ይቈያል። 5 በንጉሦቻችን ቀን አለቆች ከወይን ጠጅ ሙቀት የተነሣ ታመሙ፤ እነርሱም ከዋዘኞች ጋር እጆቻቸውን ዘረጉ። 6 እያደቡ ልባቸውን እንደ ምድጃ አዘጋጅተዋል፤ ጋጋሪያቸውም ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፤ በጠባም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ይነድዳል። 7 ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፤ ፈራጆቻቸውንም በሉ፤ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወደቁ፤ ከእነርሱም መካከል የሚጠራኝ የለም። 8 ኤፍሬም ከሕዝቡ ጋር ተደባለቀ፤ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ነው። 9 ጠላት ጕልበቱን በላው፤ እርሱ ግን አላወቀም፤ ሽበትም ወጣበት፤ እርሱም ገና አላስተዋለም። 10 የእስራኤልም ውርደቱና ስድቡ በፊቱ ነው፤ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ግን አልተመለሱም፤ በዚህም ሁሉ እግዚአብሔርን አልፈለጉትም። 11 ኤፍሬምም ልብ እንደሌላት እንደ ሰነፍ ርግብ ነው፤ ግብፅን ጠሩ፤ ወደ አሦርም ሄዱ። 12 ሲሄዱም አሽክላዬን እዘረጋባቸዋለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎችም አወርዳቸዋለሁ፤ መከራቸውን ሲሰሙ እገሥጻቸዋለሁ። 13 ከእኔ ፈቀቅ ብለዋልና ወዮላቸው! እኔንም ስለ በደሉ ደንግጠዋል! እኔ ታደግኋቸው፤ እነርሱ ግን በሐሰት ተናገሩብኝ። 14 በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፤ ስለ እህልና ስለ ወይን ይገዳደሉ ነበር፤ 15 በእኔም ዘንድ ተገሠጹ፤ እኔም ክንዳቸውን አጸናሁ፤ እነርሱ ግን ክፉ ነገርን መከሩብኝ። 16 ወደ ከንቱ ነገር ተመለሱ፤ እንደ ጠማማ ቀስትም ሆኑ፤ አለቆቻቸውም ከምላሳቸው ስንፍና የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ይህም በግብፅ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል። |