ምሳሌ 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የንጉሥ ልብ እንደ ውኃ ፈሳሽ በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ ወደ ወደደውም ይመልሳታል፥ በዚያም ትቈያለች። 2 ሰው ሁሉ ለራሱ ጻድቅ መስሎ ይታያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያቀናል። 3 ጽድቅንና ቅን ፍርድን ማድረግ መሥዋዕት ከመሠዋት ይልቅ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነው። 4 ለስድብ በልብ አለመቸኮል ታላቅ ዕውቀት ነው የኃጥኣንም ብርሃናቸው ኀጢአት ነው። 5 የትጉህ ዐሳብ ወደ ጥጋብ ያደርሳል፥ ችኩል ሰው ሁሉ ግን ለመጕደል ይቸኩላል። 6 በሐሰተኛ ምላስ ሀብትን የሚያከማች ከንቱ ነገርን ይከተላል፥ ወደ ሞት ወጥመድም ያደርሰዋል። 7 ጽድቅን ያደርጉ ዘንድ አይወድዱምና የኃጥኣን ጥፋት ከሩቅ ይመጣል። 8 እግዚአብሔር ለጠማሞች ጠማማ ሥራን ይልክባቸዋል፤ ሥራው የቀናና ንጹሕ ነውና። 9 ከነዝናዛ ሴት ጋር በተለሰነ ቤት ከመቀመጥ ይልቅ፥ ከቤት ውጭ በማዕዘን ላይ መቀመጥ ይሻላል። 10 የኀጢአተኛ ነፍስ በአንድ ሰው እንኳ ይቅር አትባልም። 11 ክፉ ሰው ሲዋረድ የዋህ ሰው ዐዋቂ ይሆናል፤ ጥበብን የሚረዳ ሰውም ዕውቀትን ይቀበላል። 12 የክፉዎች ልብ ጽድቅን አያውቅም፥ ክፋትም ኃጥአንን ያከፋቸዋል። 13 ድሃን እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው፥ እርሱ ራሱ ይጣራል፥ የሚሰማውም የለም። 14 በስውር ያለ ስጦታ ቍጣን ይመልሳል፥ ስጦታን የሚሸልግ ግን ጽኑ ቍጣን ያስነሣል። 15 ፍርድን ማድረግ ለጻድቃን ደስታ ነው፤ ጻድቅ ሰው ግን ክፉ በሚሠሩ ዘንድ የረከሰ ነው። 16 ከጽድቅ መንገድ የሚሳሳት ሰው፥ በረዐይት ጉባኤ ያርፋል። 17 ደስታን የሚወድድ ድሃን ይሆናል፥ የወይን ጠጅንና ዘይትን የሚወድድም ባለጠጋ አይሆንም። 18 ኃጥእ በጻድቅ ዘንድ የተናቀ ነው፥ ኃጥእም የጻድቅ ቤዛ ነው። 19 ከቍጡ፥ ከነዝናዛና ከነገረኛ ሴት ጋር ከመቀመጥ ይልቅ በምድረ በዳ መቀመጥ ይሻላል። 20 የተወደደ መዝገብ በጠቢባን አፍ ያርፋል፤ አላዋቂዎች ግን ያጡታል። 21 ጽድቅንና ምሕረትን የሚከተል ሕይወትንና ክብርን ያገኛል። 22 ጠቢብ የጸናች ከተማን ይገባባታል፥ ክፉዎች የሚተማመኑበትንም ኀይል ያፈርሳል። 23 አፉንና ምላሱን የሚጠብቅ ነፍሱን ከመከራ ይጠብቃል። 24 የችኩል፥ የነዝናዛና የነገረኛ ሰው ስሙ ቸነፈር ነው፥ ክፉን የሚያስብም ኃጥእ ነው። 25 ታካችን ምኞቱ ትገድለዋለች፥ እጆቹ ምንም ይሠሩ ዘንድ አይፈቅዱምና። 26 ኃጥእ ቀኑን ሁሉ ክፉ ምኞትን ይመኛል፥ ጻድቅ ግን ዐውቆ ይራራል፥ ይመጸውታልም። 27 የኃጥኣን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ በክፋት ያቀርቡታልና። 28 ሐሰተኛ ምስክር ይጠፋል፤ የሚሰማ ሰው ግን ተጠንቅቆ ይናገራል። 29 ኃጥእ ሰው ያለ ኀፍረት ፊት ለፊት ይቃወማል፤ ቅን ሰው ግን መንገዱን ይረዳል። 30 ጥበብና ብርታት፥ ምክርም፥ በኃጥእ ዘንድ የሉም። 31 ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤ ረድኤት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። |