ሆሴዕ 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የንስሓ ጥሪ 1 በመከራቸው ጊዜ በማለዳ ወደ እኔ ይገሰግሳሉ፤ እንዲህም ይላሉ፥ “ኑ፤ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናልና፥ እርሱም ይጠግነናል። 2 ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፤ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን። 3 እንወቀው፤ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል፤ እንደ ወገግታም ተዘጋጅቶ እናገኘዋለን፤ በምድርም ላይ እንደ መጀመሪያውና እንደ ኋለኛው ዝናብ ወደ እኛ ይመጣል። 4 “ምሕረታችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና ኤፍሬም ሆይ! ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ! ምን ላድርግልህ? 5 ስለዚህ ነቢያቶቻችሁን አጨድኋቸው፤ በአፌም ቃል ገደልኋቸው፤ ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል። 6 ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለሁና። 7 እነርሱ ግን ቃል ኪዳንን እንደሚያፈርስ ሰው ሆኑ፤ በዚያም ላይ ከዱኝ። 8 ገለዓድ ከንቱን የምትሠራና በደም የተቀባች ከተማ ናት፥ 9 ሰውን እንደሚያደቡ ወንበዴዎች፥ እንዲሁ ካህናት በሴኬም መንገድ ላይ አድብተው ይገድላሉ፤ ዐመፅንም ያደርጋሉ። 10 በእስራኤል ቤት የሚያሰፈራን ነገር አይቻለሁ፤ በዚያ የኤፍሬምንም ዝሙት አየሁ፤ እስራኤልም ረክሶአል። 11 ይሁዳ ሆይ! የሕዝቤን ምርኮ በምመልስበት ጊዜ ለአንተ ደግሞ መከር ተወስኖልሃል።” |