1 ቆሮንቶስ 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የመምህራንን ፍለጋ መከተል 1 እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው እኔን ምሰሉ። 2 ወንድሞች ሆይ፥ አመሰግናችኋለሁ፤ ዘወትር ታስቡኛላችሁና፤ ያስተማርኋችሁንም ትምህርት ጠብቃችኋልና። 3 ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራሱ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስዋ ወንድ፤ የክርስቶስም ራሱ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወድዳለሁ። የጸሎት ሥርዐት 4 ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም የሚያስተምር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል። 5 ራስዋን ሳትከናነብ የምትጸልይ ወይም የምታስተምር ሴት ሁላ ራስዋን ታዋርዳለች፤ ራስዋን እንደ ተላጨች መሆንዋ ነውና። 6 ሴት ካልተከናነበች ትላጭ ወይም ጠጕርዋን ትቈረጥ፤ ለሴት ጠጕርዋን መቈረጥ ወይም መላጨት ውርደት ከሆነ ትከናነብ። 7 ወንድ በሚጸልይበት ጊዜ ሊከናነብ አይገባውም፤ የእግዚአብሔር አርአያውና አምሳሉ ነውና፤ ሴትም ለባልዋ ክብር ናት። 8 ሴት ከወንድ ተገኝታለችና፤ ወንድ ግን ከሴት የተገኘ አይደለም። 9 ወንድ ስለ ሴት አልተፈጠረም፤ ሴት ስለ ወንድ ተፈጠረች እንጂ። 10 ስለዚህም ሴት ስለ መላእክት፥ ሥልጣን ለራስዋ ሊሆን ይገባል፤ 11 ነገር ግን አሁን ሴት ከባሏ አትለይ፤ ወንድም ከሚስቱ አይለይ፤ ሁላችሁም በጌታችን ኑሩ። 12 ሴት ከወንድ እንደ ተገኘች እንዲሁ ወንድ ከሴት ተገኘ፤ ነገር ግን ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው። 13 እስኪ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ፤ ሴት ወደ እግዚአብሔር በምትጸልይበት ጊዜ ልትከናነብ አይገባምን? 14 ተፈጥሮዋስ አያስረዳችሁምን? ወንድ ግን ጠጕሩን ቢያሳድግ ነውር ነው። 15 ለሴት ግን ጠጕርዋን ብታሳድግ ክብርዋ ነው፤ ለሴት ጠጕርዋ እንደ ቀጸላ ሆኖ ተሰጥቶአታልና። 16 ነገር ግን የሚጠራጠር ቢኖር እኛ ወይም የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ልማድ የለንም። ጸብና ክርክር እንደማይገባ 17 ይህንም የነገርኋችሁ ላመሰግናችሁ አይደለም፤ በምትሰበሰቡበት ጊዜ ወደ ዝቅተኛ እንጂ ወደሚሻል ግብር አትሄዱምና። 18 ከሁሉ አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያን በምትሰበሰቡ ጊዜ እንደምትጣሉና እንደምትከራከሩ ሰምቻለሁ፤ የማምነውም አለኝ። 19 ከእናንተ የተመረጡት ወንድሞች ተለይተው እንዲታወቁ ትለያዩ ዘንድ ግድ ነው። 20 እንግዲህ እናንተም በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምትበሉና የምትጠጡ ለጌታችን ቀን እንደሚገባ አይደለም። 21 ወደ ምግብ ትሽቀዳደማላችሁ፤ የተራቡ በአጠገባችሁ እያሉ እናንተ ትበላላችሁ፤ ትጠግባላችሁ፤ ትሰክራላችሁም። 22 በውኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ታስነቅፋላችሁን? ነዳያንንስ ታሳፍሩአቸዋላችሁን? ምን እላለሁ? በዚህ አመሰግናችኋለሁን? አላመሰግናችሁም። ስለ ጌታችን ሥጋና ደም 23 ከእግዚአብሔር እንደ ተማርሁ አስተምሬአችኋለሁና፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ራሱን በያዙባት በዚያች ሌሊት ኅብስቱን አነሣ። 24 አመሰገነ፤ ባረከ፤ ፈተተ፤ እንዲህም አላቸው፥ “እንኩ ብሉ፤ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ መታሰቢያዬንም እንዲሁ አድርጉ።” 25 እንዲሁም ኅብስቱን ከተቀበሉ በኋላ ጽዋውን አንሥቶ፥ “አዲስ ሥርዐት የሚጸናበት ይህ ጽዋ ደሜ ነው እንዲህ አድርጉ፤ በምትጠጡበትም ጊዜ አስቡኝ” አላቸው። 26 ይህን ኅብስት በምትበሉበት፥ ይህንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታችን እስከሚመጣበት ቀን ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ። 27 አሁንም ሳይገባው ይህን ኅብስት የበላ፥ ይህንም ጽዋ የጠጣ የጌታችን ሥጋውና ደሙ ስለሆነ ዕዳ አለበት። 28 አሁንም ሰው ራሱን መርምሮና አንጽቶ ከዚህ ኅብስት ይብላ፤ ከዚህም ጽዋ ይጠጣ። 29 ሳይገባው፥ የጌታችን ሥጋም እንደ ሆነ ሳያውቅ፥ ሰውነቱንም ሳያነጻ፥ የሚበላና የሚጠጣ ለራሱ ፍርዱንና መቅሠፍቱን ይበላል፤ ይጠጣልም። 30 ስለዚህ ከመካከላችሁ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች ናቸው፤ ብዙዎችም በድንገት አንቀላፍተዋል። 31 እኛ በራሳችን ብንፈርድ ኖሮ ባልተፈረደብንም ነበር። 32 ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኰነን በጌታ እንገሠጻለን። 33 አሁንም ወንሞቻችን ሆይ፥ ለምሳ በምትሰበሰቡበት ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ፤ 34 መሰብሰባችሁ ለፍዳ እንዳይሆን፥ የተራበ ቢኖር በቤቱ ይብላ፤ አትነቃቀፉም፤ ሌላውን ሥርዐት ግን መጥቼ እሠራላችኋለሁ። |