ዘፍጥረት 26:24 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፥ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ አትፍራ፤ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አባትህ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛዋለሁ።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለትና፣ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አገልጋዬም ስለ አብርሃም ስል ዘርህን አበዛለሁ” አለው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በዚያችም ሌሊት ጌታ ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው፦ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፥ አትፍራ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፥ እባርክሃለሁ፥ ስለ ባርያዬ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛለሁ።” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለትና “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ እኔ ከአንተ ጋር ስለ ሆንኩ አትፍራ፤ ለአገልጋዬ ለአብርሃም በገባሁት ቃል ኪዳን መሠረት እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም አበዛዋለሁ” አለው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው፦ እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ አትፍራ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና እባርክሃለሁ ስለ ባሪያዬ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛለሁ። |
ከዚህም ነገር በኋላ የእግዚአብሔር ቃል በራእይ ወደ አብራም መጣ፤ እንዲህ ሲል፥ “አብራም ሆይ፥ አትፍራ፤ እኔ ጋሻ እሆንሃለሁ፤ ዋጋህም በእኔ ዘንድ እጅግ ብዙ ነው።”
ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል በትውልዳቸው ለዘለዓለም ኪዳን አቆማለሁ፤ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ።
በውስጥዋ የምትኖርባትን ይህችን ምድር፥ የከነዓንን ምድር ሁሉ፥ ለዘለዓለም ይገዙአት ዘንድ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ አምላክም እሆናቸዋለሁ።”
እግዚአብሔርም የሕፃኑን ጩኸት ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፥ “አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የልጅሽን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ።
ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ፈጽሞ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላት ሀገሮችን ይወርሳሉ፤
አብርሃምም ወደ ብላቴኖቹ ተመለሰ፤ ተነሥተውም ወደ ዐዘቅተ መሐላ አብረው ሄዱ፤ አብርሃምም በዐዘቅተ መሐላ ተቀመጠ።
እንዲህም አለ፥ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፤ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ።
እነሆም፥ እግዚአብሔር በላዩ ቆሞበት ነበር፥ እንዲህም አለ፥ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ አትፍራ፥ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፤
እነሆም፥ እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚያችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።”
ላባም፥ “በዐይንህ ፊት ሞገስን የማገኝ ብሆንስ ከዚሁ ተቀመጥ፤ እግዚአብሔር በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ ተመልክቼአለሁና።
እንዲህም አላቸው፥ “እነሆ፥ የአባታችሁ ፊት እንደ ዱሮ ከእኔ ጋር እንዳልሆነ አያለሁ፤ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር ነው።
ጌታውም እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር እንዳለ፥ እርሱ የሚሠራውንም ሁሉ እግዚአብሔር በእጁ እንዲያከናውንለት አየ።
እስራኤልም ለእርሱ ያለውን ሁሉ ይዞ ተነሣ፤ ወደ ዐዘቅተ መሐላም መጣ፤ መሥዋዕትንም ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ ሠዋ።
ኤልያስም አላት፥ “በእግዚአብሔር እመኚ፤ አትፍሪ፤ ሄደሽም እንዳልሽው አድርጊ፤ አስቀድመሽ ግን ከዱቄቱ ለእኔ ታናሽ እንጎቻ አድርገሽ አምጭልኝ፥ ከዚያም በኋላ ለአንቺና ለልጅሽ አድርጊ፤
ሙሴም ለሕዝቡ፥ “አትፍሩ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና ቁሙ፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ።
ደግሞም፥ “እኔ የአባቶችህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ” አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን መለሰ።
እነሆ፥ አምላኬ መድኀኒቴ ነው፤ ጌታ እግዚአብሔር ክብሬና ዝማሬዬ ነው፤ መድኀኒቴም ሆኖአልና በእርሱ ታምኜአለሁ፤ አልፈራምም።”
እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፤ እረዳህማለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።
የፈጠረህ ከማኅፀንም የሠራህ የሚረዳህም እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፥ “ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም ወዳጄ እስራኤል ሆይ፥ አትፍራ።
እኔ ነኝ፤ የማጽናናሽ እኔ ነኝ፤ አንቺ እንግዲህ ዕወቂ፤ ማንን ፈራሽ? የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ነውን?
ያን ጊዜ እኔ ከያዕቆብ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ደግሞም ከይስሐቅ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን፥ ከአብርሃምም ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ምድሪቱንም አስባለሁ።
እኔ አምላካቸው እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብፅ ምድር ከግዞት ቤት እንዳወጣኋቸው የቀድሞ ቃል ኪዳናቸውን ስለ እነርሱ አስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝና።”
‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤’ ሙሴም ተንቀጠቀጠ፤ መረዳትም አልቻለም።
የእግዚአብሔር የመቅሠፍቱ ቍጣ ይመለስ ዘንድ፥ ለአባቶችህም እንደ ማለላቸው ይምርህ ዘንድ፥ ይራራልህም ዘንድ፥ ያበዛህም ዘንድ፥ ርጉም ከሆነው አንዳች ነገር በእጅህ አትንካ።
ጽና፤ በርታ፤ አትፍራ፤ ከፊታቸውም አትደንግጥ፤ አትድከም፤ አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ አይጥልህም፤ አይተውህምም።
አሁን ግን፥ በሰማያት ያለችውን የምትበልጠውን ሀገር ተስፋ ያደርጉ እንደ ነበር ታወቀ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ይጠራ ዘንድ በእነርሱ አያፍርም፤ ተስፋ ያደረጉአትን ሀገር አዘጋጅቶላቸዋልና።