ዘፍጥረት 24 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይስሐቅና ርብቃ ጋብቻ 1 አብርሃምም ሸመገለ፤ ዘመኑም አለፈ፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሁሉ ባረከው። 2 አብርሃምም ሎሌውን፥ የቤቱን ሽማግሌ፥ የከብቱን ሁሉ አዛዥ አለው፦ 3 “እጅህን በእጄ ላይ አድርግ፤ እኔም አብሬ ከምኖራቸው ከከነዓን ሴቶች ልጆች ለልጄ ለይስሐቅ ሚስት እንዳትወስድለት በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ 4 ነገር ግን ወደ ተወለድሁበት ወደ ሀገሬና ወደ ተወላጆች ሂድ፤ ለልጄ ለይስሐቅም ከዚያ ሚስትን አምጣለት።” 5 ሎሌውም፥ “ሴቲቱ ምናልባት ወደዚህ ሀገር ከእኔ ጋር ለመምጣት ባትወድድስ ልጅህን ወደ መጣህበት ሀገር ልመልሰውን?” አለው። 6 አብርሃምም አለው፥ “ልጄን ወደዚያ እንዳትመልስ ተጠንቀቅ፤ 7 ከአባቴ ቤት፥ ከተወለድሁባት ምድር ያወጣኝ፦ ‘ይህችንም ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጥሃለሁ’ ብሎ የነገረኝና የማለልኝ የሰማይና የምድር አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ መልአኩን በፊትህ ይሰድዳል፤ ከዚያም ለልጄ ሚስትን ትወስዳለህ። 8 ሴቲቱም ከአንተ ጋር ወደዚች ምድር ለመምጣት ባትፈቅድ አንተ ከዚህ መሐላ ንጹሕ ነህ፤ ልጄን ግን ወደዚያ እንዳትመልሰው ተጠንቀቅ።” 9 ሎሌውም በጌታው በአብርሃም እጅ ላይ እጁን አደረገ፤ ስለዚሁም ነገር ማለለት። 10 ሎሌውም ከጌታው ግመሎች መካከል ዐሥር ግመሎችን ወስዶ፥ ከጌታውም ዕቃ መልካም መልካሙን ይዞ ተነሣ፤ ተነሥቶም ወደ ሦርያ ወንዞች መካከል ወደ ናኮር ከተማ ሄደ። 11 ሲመሽም ውኃ ቀጂዎች ውኃ ሊቀዱ በሚመጡበት ጊዜ ከከተማዪቱ ውጪ በውኃ ጕድጓድ አጠገብ ግመሎቹን አሳረፈ። 12 እንዲህም አለ፥ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፤ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። 13 እነሆ፥ በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዋ ሰዎች ሴቶች ልጆችም ውኃውን ሊቀዱ ይወጣሉ፤ 14 እንስራሽን አዘንብለሽ ውኃ አጠጭኝ የምላት እርስዋም፦ ‘አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ እስኪረኩ አጠጣለሁ’ የምትለኝ ድንግል፥ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ለአብርሃም ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ።” 15 እንደዚህ በልቡ ያሰበውን መናገሩን ሳይፈጽም እንዲህ ሆነ፦ የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት የሚልካ ልጅ የባቱኤል ሴት ልጅ ርብቃ እነሆ፥ መጣች፥ እንስራዋንም በጫንቃዋ ተሸክማ ነበር። 16 ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማታውቅ ድንግል ነበረች። ወደ ውኃው ጕድጓድም ወረደች፤ ውኃም ቀዳች፤ እንስራዋንም ሞልታ ወጣች። 17 ያም ሰው ሊገናኛት ሮጠና፥ “ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ አጠጪኝ” አላት። 18 እርስዋም፥ “ጌታዬ ሆይ፥ ጠጣ” አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ከጫንቃዋ በእጅዋ አውርዳ እስኪረካ አጠጣችው። 19 እርሱንም ከአጠጣች በኋላ፦ “ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ” አለችው። 20 ፈጥናም ውኃውን ከእንስራዋ በማጠጫው ውስጥ ገለበጠችው፤ ደግሞም ልትቀዳ ወደ ጕድጓዱ ሮጠች፤ ለግመሎቹም ሁሉ ውኃ ቀዳች። 21 ሰውየውም ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር፤ እግዚአብሔር መንገዱን አቅንቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅም ዝም አለ። 22 ግመሎቹም ከጠጡ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ሰውዬው አንድ አንድ ወቄት የሚመዝን የወርቅ ጉትቻ፥ ለእጆችዋም ዐሥር ወቄት የሚመዝን ጥንድ የወርቅ አምባር አወጣ፤ 23 ጠርቶም እንዲህ አላት፥ “አንቺ የማን ልጅ ነሽ? በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ እንዳለ እስኪ ንገሪኝ፤” 24 አለችውም፥ “እኔ ሚልካ ለናኮር የወለደችለት የባቱኤል ልጅ ነኝ። 25 በእኛ ዘንድ ለግመሎችህ ሣርና ገለባ የሚበቃ ያህል አለ፤ ማደሪያም አለን።” 26 ሰውየውም ደስ አለው፤ ለእግዚአብሔርም ሰገደ። 27 እንዲህም አለ፥ “ቸርነቱንና እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ለእኔም ወደ ጌታዬ ወደ አብርሃም ወንድም ቤት መንገዴን አቀናልኝ።” 28 ብላቴናዪቱም ሮጠች፥ ለእናቷም ቤት ይህን ሁሉ ነገር ተናገረች። 29 ለርብቃም ስሙ ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ ላባም ወደ ውጪ ወደ ውኃው ጕድጓድ ወደ ሰውዬው ሮጠ። 30 ጉትቻውንና አምባሮቹን በእኅቱ እጅ ባየ ጊዜ፥ የእኅቱንም የርብቃን ነገር፦ ያ ሰው እንዲህ አለኝ ያለችውን በሰማ ጊዜ፥ እርሱ ወደዚያ ሰው መጣ፤ እነሆም በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ከግመሎቹ ዘንድ ቆሞ ነበር። 31 እርሱም አለው፥ “አንተ የእግዚአብሔር ቡሩክ፥ ግባ ስለምን አንተ በውጪ ቆመሃል? እኛም ቤትን፥ ለግመሎችህም ማደሪያን አዘጋጅተናል።” 32 ሰውዬውም ወደ ቤት ገባ፤ ግመሎቹንም አራገፈ፤ ለግመሎቹም ሣርና ገለባ አቀረቡላቸው፤ እግሩን ይታጠብ ዘንድ ውኃ አመጡለት፤ ከእርሱ ጋር ላሉ ሰዎችም አመጡላቸው። 33 ይበላም ዘንድ እንጀራን አቀረቡለት፤ እርሱ ግን “ነገሬን እስክናገር ደረስ አልበላም” አለ። እነርሱም “ተናገር” አሉት። 34 እርሱም አለ፥ “እኔ የአብርሃም ሎሌ ነኝ። 35 እግዚአብሔርም ጌታዬን እጅግ ባረከው፤ አገነነውም፤ ላሞችንና በጎችን፥ ወርቅንና ብርን፥ ወንዶች ባሪያዎችንና ሴቶች ባሪያዎችን፥ ግመሎችንና አህዮችንም ሰጠው። 36 የጌታዬ የአብርሃም ሚስት ሣራም በእርጅናዋ ለጌታዬ ወንድ ልጅን ወለደች፤ የነበረውንም ሁሉ ሰጠው።” 37 ጌታዬ እንዲህ ሲል አማለኝ፥ “እኔ ካለሁበት ሀገር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስትን አትውሰድ፤ 38 ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት ወደ ወገኔም ሂድ፤ ለልጄም ከዚያ ሚስትን ውሰድለት። 39 ጌታዬንም ሴቲቱ ምናልባት ከእኔ ጋር መምጣትን ባትፈቅድስ አልሁት። 40 እርሱም አለኝ፦ አካሄዴን በፊቱ ያደረግሁለት እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል። መንገድህንም ያቀናል፤ ለልጄም ከወገኖች ከአባቴም ቤት ሚስትን ትወስዳለህ፤ 41 የዚያን ጊዜ ከመሐላዬ ንጹሕ ትሆናለህ፤ ወደ ዘመዶች ሄደህ እነርሱ ባይሰጡህ ካማልሁህ መሐላ ንጹሕ ትሆናለህ።” 42 ዛሬም ወደ ውኃው ጕድጓድ መጣሁ፤ እንዲህም አልሁ፥ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዛሬ የምሄድበትን መንገዴን ብታቀናልኝ፥ 43 እነሆ፥ እኔ በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዋ ሰዎች ሴቶች ልጆችም ውኃን ሊቀዱ ይወጣሉ፤ ጥቂት ውኃ ከእንስራሽ አጠጪኝ ስላት፥ 44 እርስዋም ፦ ‘አንተ ጠጣ፤ ደግሞም ለግመሎችህ እቀዳለሁ’ የምትለኝ ድንግል፥ እግዚአብሔር ለጌታዬ ልጅ ለባሪያዉ ለይስሐቅ ያዘጋጃት ሚስት እርስዋ ትሁን። በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ።” 45 እኔም በልቤ ያሰብሁትን ሳልፈጽም እንዲህ ሆነ፤ ያን ጊዜ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ወጣች፥ ወደ ምንጭም ወርዳ ውኃ ቀዳች፤ እኔም “እስቲ ውኃ አጠጪኝ” አልኋት። 46 ፈጥናም እንስራዋን ከትከሻዋ አወረደችና፥ “አንተ ጠጣ፤ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ” አለችኝ፤ እኔም ጠጣሁ፤ ግመሎችንም ደግሞ አጠጣች። 47 እኔም “አንቺ የማን ልጅ ነሽ? ንገሪኝ” ብዬ ጠየቅኋት። እርስዋም፥ “ሚልካ የወለደችለት የናኮር ልጅ የባቱኤል ልጅ ነኝ” አለችኝ፤ 48 ይህንም ነገር ከአንደበቷ በሰማሁ ጊዜ እጅግ ደስ አሰኘችኝ። ለጆሮዎችዋም ጉትቻዎችን ለእጆችዋም አምባሮችን አድርጌ አስጌጥኋት። ደስ ባሰኘችኝም ጊዜ፥ ለእግዚአብሔር ሰገድሁ፤ የጌታዬን የወንድሙን ልጅ ለልጁ እወስድ ዘንድ በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። 49 አሁንም ቸርነትንና እውነትን ለጌታዬ ትሠሩ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ ይህም ባይሆን ንገሩኝ፤ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ እመለስ ዘንድ። 50 ባቱኤልና ላባም መለሱ፤ እንዲህም አሉ፥ “ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶአል፤ ክፉ ወይም በጎ ልንመልስልህ አንችልም። 51 ርብቃ እንኋት፤ በፊትህ ናት፤ ይዘሃት ሂድ፥ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁን።” 52 የአብርሃምም ሎሌ ነገራቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ምድር ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ። 53 ሎሌውም የብርና የወርቅ ጌጥ፥ ልብስም አወጣ፤ ለርብቃም ሰጣት፤ ዳግመኛም ለአባቷና ለእናቷ እጅ መንሻ ሰጣቸው። 54 ከዚህም ሁሉ በኋላ እርሱ፥ ከእርሱ ጋር ያሉትም በሉ፤ ጠጡም፤ በዚያም አደሩ፤ በማለዳም ተነሥቶ፥ “ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ” አላቸው። 55 አባቷ እናቷና ወንድምዋ፦ “ብላቴናዪቱ ዐሥር ቀን ያህል እንኳ በእኛ ዘንድ ትቀመጥ፤ ከዚያም በኋላ ትሄዳለች” አሉ። 56 እርሱም፥ “እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኝ ሳለ አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ” አላቸው። 57 እነርሱም፥ “ብላቴናዪቱን እንጥራና ከአፍዋ እንጠይቅ” አሉ። 58 ርብቃንም ጠርተው፥ “ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን?” አሉአት። እርስዋም፥ “አዎን እሄዳለሁ” አለች። 59 እኅታቸውንም ርብቃን ሞግዚቷንም ከገንዘብ ጋር፥ የአብርሃምን ሎሌና ሰዎቹንም አሰናበቱአቸው። 60 እኅታቸው ርብቃንም መረቁአትና፥ “አንቺ እኅታችን፥ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽም የጠላት ሀገሮችን ይውረስ” አሉአት። 61 ርብቃም ተነሣች፤ ደንገጥሮችዋም፥ በግመሎችዋ ላይ ተቀምጠው ከሰውዬው ጋር አብረው ሄዱ፤ ሎሌውም ርብቃን ተቀብሎ ሄደ። 62 ይስሐቅም በዐዘቅተ ራእይ በኩል ወደ ምድረ በዳ ይመለከት ነበር፤ በአዜብ በኩል ባለው ምድር ተቀምጦ ነበርና። 63 ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር፤ ዓይኖቹንም አቀና፤ እነሆም ግመሎች ሲመጡ አየ። 64 ርብቃም ዓይኖችዋን አቀናች፤ ይስሐቅንም አየች፤ ከግመልም ወረደች። 65 ሎሌውንም፥ “ሊቀበለን በሜዳ የሚመጣ ይህ ሰው ማነው?” አለችው። ሎሌውም፥ “እርሱ ጌታዬ ነው” አላት፤ እርስዋም ቀጸላዋን ወስዳ ተከናነበች። 66 ሎሌውም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። 67 ይስሐቅም ወደ እናቱ ቤት ገባ፤ ርብቃንም ወሰዳት፤ ሚስትም ሆነችው፤ ወደዳት፤ ይስሐቅም ስለ እናቱ ስለ ሣራ ተጽናና። |