ዘፍጥረት 28 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ይስሐቅም ያዕቆብን ጠራው፤ ባረከውም፥ እንዲህም ብሎ አዘዘው፥ “ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ፤ 2 ተነሣና ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሂድ፤ ከዚያም ከእናትህ ከርብቃ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች ሚስትን አግባ። 3 አምላኬ ከአንተ ጋር ይሂድ፤ ከፍ ከፍም ያድርግህ፤ ይባርክህ፤ ያብዛህ፤ ብዙ ሕዝብም ሁን ፤ 4 ስደተኛ ሆነህ የተቀመጥህባትን፥ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጣትን ምድር ትወርስ ዘንድ የአባቴን የአብርሃምን በረከት ለአንተ ይስጥህ፤ ከአንተም በኋላ ለዘርህ።” 5 ይስሐቅም ልጁ ያዕቆብን ላከው፤ እርሱም የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም የሚሆን የሶርያዊው ባቱኤል ልጅ ላባ ወዳለበት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሄደ። ዔሳው ሌላ ሚስት ማግባቱ 6 ዔሳውም ይስሐቅ ያዕቆብን እንደ ባረከው በአየ ጊዜ ከዚያም ሚስትን ያገባ ዘንድ ወደ ሁለቱ የሶርያ ወንዞች መካከል እንደ ላከው፥ በባረከውም ጊዜ፥ “ከከነዓን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ” ብሎ እንዳዘዘው፥ 7 ያዕቆብም የአባቱንና የእናቱን ቃል ሰምቶ ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል እንደ ሄደ፥ 8 የከነዓናውያንም ሴቶች ልጆች በአባቱ በይስሐቅ ፊት የተጠሉ እንደ ሆኑ ዔሳው በአየ ጊዜ፥ 9 ዔሳው ወደ ይስማኤል ሄደ፤ ቤሴሞትንም በፊት ካሉ ሚስቶቹ ጋር ሚስት ትሆነው ዘንድ ወሰዳት፤ እርስዋም የናኮር ወንድም የአብርሃም ልጅ የሆነው የይስማኤል ልጅና የናቡዓት እኅት ናት። ያዕቆብ በቤቴል ያየው ሕልም 10 ያዕቆብም ከአዘቅተ መሐላ ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ። 11 ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፤ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና በዚያ አደረ፤ ከዚያም ስፍራ ድንጋዮች አንድ ድንጋይ አነሣ፤ ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ። 12 ሕልምም አለመ፤ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበትና ይወርዱበት ነበር። 13 እነሆም፥ እግዚአብሔር በላዩ ቆሞበት ነበር፥ እንዲህም አለ፥ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ አትፍራ፥ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፤ 14 ዘርህም እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፤ እስከ ባሕርና እስከ አዜብ እስከ መስዕና እስከ ምሥራቅ ይበዛል፤ ይሞላልም፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በአንተ፥ በዘርህም ይባረካሉ። 15 እነሆም፥ እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚያችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።” 16 ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነሥቶ፥ “በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ አላወቅሁም ነበር” አለ። 17 ፈራ፤ እንዲህም አለ፥ “ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ፤ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህችም የሰማይ ደጅ ናት።” 18 ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ፤ ተንተርሷት የነበረችውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆማት፥ በላይዋም ዘይትን አፈሰሰባት። 19 ያዕቆብም ያን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው፤ አስቀድሞ ግን የዚያ ከተማ ስም ሎዛ ነበረ። 20 ያዕቆብም እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ፥ “እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን፥ በምሄድባትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ፥ የምበላውንም እንጀራ፥ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ፥ 21 ወደ አባቴም ቤት በጤና ቢመልሰኝ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፤ 22 ለሐውልት ያቆምኋት ይህችም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ትሆንልኛለች፤ ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከዐሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ።” |