1 ነገሥት 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኤልያስ ዝናብ እንዳይዘንብ ስለ መከልከሉ 1 በገለዓድ ቴስባን የነበረው ቴስብያዊው ነቢዩ ኤልያስ አክዓብን፥ “በፊቱ የቆምሁት የኀያላን አምላክ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! ከአፌ ቃል በቀር በእነዚህ ዓመታት ዝናብም ጠልም አይወርድም” አለው። 2 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 3 “ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፤ በዮርዳኖስም ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተሸሸግ። 4 ከፈፋው ትጠጣለህ፤ ቁራዎችም በዚያ ይመግቡህ ዘንድ አዝዣለሁ።” ሄደም፥ እግዚአብሔርም እንዳዘዘው አደረገ። 5 ሄዶም በዮርዳኖስ ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ተቀመጠ። 6 ቁራዎችም በየጥዋቱና በየማታው እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ ከፈፋውም ይጠጣ ነበር። 7 ከብዙ ቀንም በኋላ በምድር ላይ ዝናብ አልነበረምና ፈፋው ደረቀ። ኤልያስ ወደ ሰራፕታዪቱ መበለት እንደ ሄደና የመበለቲቱን ልጅ ከሞት እንዳስነሣ 8 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤልያስ መጣ እንዲህም አለው፦ 9 “ተነሥተህ በሲዶና አጠገብ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሂድ፤ በዚያም ተቀመጥ፤ እነሆም፥ ትመግብህ ዘንድ አንዲት መበለት አዝዣለሁ።” 10 ተነሥቶም ወደ ሰራፕታ ሄደ፤ ወደ ከተማዪቱም በር በደረሰ ጊዜ አንዲት መበለት በዚያ እንጨት ትለቅም ነበር፤ ኤልያስም ጠርቶ፥ “የምጠጣው ጥቂት ውኃ በጽዋ ታመጭልኝ ዘንድ እለምንሻለሁ” አላት። 11 ውኃም ልታመጣለት በሄደች ጊዜ ወደ እርስዋ ጠርቶ፥ “እግረ መንገድሽን ቍራሽ እንጀራ በእጅሽ አምጭልኝ” አላት። 12 ሴትየዋም፥ “አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! በማድጋ ካለው ከእፍኝ ዱቄት በማሰሮም ካለው ከጥቂት ዘይት በቀር እንጀራ የለኝም፤ እነሆም፥ ጥቂት እንጨት እሰበስባለሁ፤ ሄጄም ለእኔና ለልጄ እጋግረዋለሁ፤ በልተነውም እንሞታለን” አለችው። 13 ኤልያስም አላት፥ “በእግዚአብሔር እመኚ፤ አትፍሪ፤ ሄደሽም እንዳልሽው አድርጊ፤ አስቀድመሽ ግን ከዱቄቱ ለእኔ ታናሽ እንጎቻ አድርገሽ አምጭልኝ፥ ከዚያም በኋላ ለአንቺና ለልጅሽ አድርጊ፤ 14 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በምድር ላይ እግዚአብሔር ዝናብ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ፥ ዱቄቱ ከማድጋው አይጨረስም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አይጐድልም።” 15 እርስዋም ሄዳ እንዲሁ አደረገች፤ እርስዋና እርሱ ልጆችዋም በሉ። 16 በአገልጋዩ በኤልያስም ቃል እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዱቄቱ ከማድጋው አልተጨረሰም፤ ዘይቱም ከማሰሮው አልጐደለም። 17 ከዚያም በኋላ የባለቤቲቱ የዚያች ሴት ልጅ ታመመ፤ ትንፋሹም እስኪታጣ ድረስ ደዌው እጅግ ከባድ ነበረ። 18 እርስዋም ኤልያስን፥ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? አንተስ ከእኔ ጋር ምን አለህ? ኀጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን?” አለችው። 19 ኤልያስም፥ “ልጅሽን ስጪኝ” አላት፥ ከብብቷም ወስዶ ተቀምጦበት ወደ ነበረው ሰገነት አወጣው፤ በአልጋውም ላይ አስተኛው። 20 ኤልያስም፥ “እኔ በቤቷ ያደርሁ የዚች መበለት ምስክርዋ ጌታዬ ሆይ፥ ልጅዋን በመግደልህ ክፉ አድርገህባታልና ወዮልኝ!” ብሎ ጮኸ። 21 በብላቴናውም ላይ ሦስት ጊዜ እፍ አለበት፤ ወደ እግዚአብሔርም፥ “አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ የዚህ ብላቴና ነፍስ ወደ እርሱ ትመለስ ዘንድ እለምንሃለሁ” ብሎ እግዚአብሔርን ጠራው። 22 እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ፤ የሕፃኑም ነፍስ ተመለሰች፥ ዳነም፤ 23 ኤልያስም ብላቴናውን ይዞ ከሰገነቱ ወደ ቤት አወረደው፥ ለእናቱም ሰጣት፥ “እነሆ፥ ተመልከች ልጅሽ ድኖአል” አለ። 24 ሴቲቱም ኤልያስን፥ “የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንህ፥ የእግዚአብሔርም ቃል በአፍህ እውነት እንደ ሆነ አሁን ዐወቅሁ” አለችው። |