ዘዳግም 31 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኢያሱ በሙሴ ፋንታ እንደ ተተካ 1 ሙሴም ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናግሮ ጨረሰ። 2 አላቸውም፥ “እኔ ዛሬ መቶ ሃያ ዓመት ሆኖኛል፤ ከዚህ በኋላ እወጣና እገባ ዘንድ አልችልም፤ እግዚአብሔርም፦ ‘ይህን ዮርዳኖስን አትሻገርም’ ብሎኛል። 3 አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ በፊትህ ያልፋል፤ እርሱ እነዚህን አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል፤ ትወርሳቸውማለህ፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ኢያሱ በፊትህ ይሄዳል። 4 እግዚአብሔር አምላክም ባጠፋቸው በዮርዳኖስ ማዶ በሚኖሩ በሁለቱ በአሞሬዎናውያን ነገሥታት በሴዎንና በዐግ፥ በምድራቸውም እንዳደረገ እንዲሁ ያደርግባቸዋል። 5 እግዚአብሔርም በፊታችሁ አሳልፎ ይጥላቸዋል፤ እንዳዘዝኋችሁም ሁሉ ታደርጉባቸዋላችሁ። 6 ጽና፤ በርታ፤ አትፍራ፤ ከፊታቸውም አትደንግጥ፤ አትድከም፤ አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ አይጥልህም፤ አይተውህምም። 7 ሙሴም ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት፦ ‘አንተ ከዚህ ሕዝብ ጋር እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው እንዲሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ትገባለህና፥ እርስዋንም ለእነርሱ ታወርሳለህና ጽና፤ በርታ። 8 በፊትህም የሚሄድ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አይጥልህም፤ አይተውህም፤ አትፍራ፤ አትደንግጥ’ ” አለው። ሕጉ በየሰባት ዓመት መነበብ እንደሚገባው 9 ሙሴም ይህችን ሕግ ጻፈ፤ የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳኑን ታቦት ይሸከሙ ለነበሩት ለሌዊ ልጆች ለካህናቱ፥ ለእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰጣት። 10 ሙሴም በዚያች ቀን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፥ “በሰባተኛው ዓመት መጨረሻ በምሕረት ዓመት በዳስ በዓል፥ 11 እስራኤል ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ እርሱ በመረጠው ቦታ በአንድነት በሚሄድበት ጊዜ፥ ይህን ሕግ በእስራኤል ሁሉ ፊት በጆሮው አንብበው። 12 ይሰሙና ይማሩ ዘንድ፥ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ይፈሩ ዘንድ፥ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ሰምተው ያደርጉ ዘንድ ሕዝቡን ወንዶችና ሴቶችን፥ ሕፃኖቻችሁንም፥ በሀገራችሁ ደጅ ያለውንም መጻተኛ ሰብስብ። 13 የማያውቁ ልጆቻቸውም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት በምትሄዱባት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይስሙ፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርንም መፍራት ይማሩ።” ሙሴና ኢያሱ ከእግዚአብሔር መመሪያ መቀበላቸው 14 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “የምትሞትበት ቀን እነሆ ቀረበ፤ ኢያሱን ጠርተህ እርሱን አዝዘው ዘንድ በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ከእርሱ ጋር ቁም” አለው። ሙሴና ኢያሱም ሄደው በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ቆሙ። 15 እግዚአብሔርም በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በደመና ዐምድ ወረደ፤ የደመናውም ዐምድ በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ላይ ቆመ። 16 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እነሆ፥ ከአባቶችህ ጋር ታንቀላፋለህ፤ ይህም ሕዝብ ይነሣል፤ ይቀመጥባትም ዘንድ በሚሄድባት ምድር መካከል ያሉትን ሌሎችን አማልክት ተከትሎ ያመነዝራል፤ እኔንም ይተወኛል፤ ከእነርሱም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ያፈርሳሉ። 17 በዚያም ቀን ቍጣዬ ይነድድባቸዋል፤ እተዋቸውማለሁ፤ ፊቴንም ከእነርሱ እመልሳለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም መብል ይሆናሉ፤ በዚያም ቀን፦ በእውነት አምላካችን እግዚአብሔር ትቶናልና፥ በእኛም መካከል የለምና ይህ ክፉ ነገር ሁሉ አገኘን እስኪሉ ድረስ ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት ይደርስባቸዋል። 18 ሌሎችን አማልክት ተከትለዋልና ስላደረጉት ክፋት ሁሉ እኔ በዚያ ቀን ፈጽሜ ፊቴን እሰውራለሁ። 19 አሁንም ይህችን መዝሙር ለእናንተ ጻፉ፤ ለእስራኤልም ልጆች አስተምሩአቸው፤ ይህችም መዝሙር በእስራኤል ላይ ምስክር ትሆንልኝ ዘንድ በአፋቸው አድርጓት። 20 ለአባቶቻቸው ወደ ማልሁላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ምድር ካገባኋቸው በኋላ፥ ከበሉም፥ ከጠገቡም በኋላ ይስታሉ፤ ሌሎችን አማልክትም ወደ ማምለክ ይመለሳሉ፤ እኔንም ያስቈጡኛል፤ ቃል ኪዳኔንም ያፈርሳሉ። 21 ዛሬ ወደ ማልሁላቸው ምድር ገና ሳላገባቸው ክፋታቸውን አውቃለሁና፥ ከአፋቸውና ከልጆቻቸውም አፍ አትረሳምና ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት በደረሰባቸው ጊዜ ይህች መዝሙር ምስክር ሆና በፊታቸው ትቆማለች።” 22 ሙሴም በዚያ ቀን ይህችን መዝሙር ጻፈ፤ ለእስራኤልም ልጆች አስተማራት። 23 የነዌንም ልጅ ኢያሱን፥ “የእስራኤልን ልጆች እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው ወደ ማለላቸው ምድር ታገባለህና ጽና፤ በርታ፤ እርሱም ከአንተ ጋር ይሆናል” ብሎ አዘዘው። 24 እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ የዚህን ሕግ ቃሎች እስከ መጨረሻ በመጽሐፍ ጽፎ ከፈጸመ በኋላ፥ 25 የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያንን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ 26 “ይህን የሕግ መጽሐፍ ውሰዱ፤ በዚያም በእናንተ ላይ ምስክር እንዲሆን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት አጠገብ አኑሩት። 27 እኔ ዐመፃችሁንና የአንገታችሁን ድንዳኔ አውቃለሁና፤ እኔም ዛሬ ከእናንተ ጋር ገና በሕይወት ሳለሁ እናንተ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችኋል፤ ይልቁንስ ከሞትሁ በኋላ እንዴት ይሆናል? 28 ይህን ቃል በጆሮአቸው እነግር ዘንድ፥ ሰማይንና ምድርንም አስመሰክርባቸው ዘንድ የነገዶቻችሁን አለቆች፥ ሽማግሌዎቻችሁን ሁሉ፥ ሹሞቻችሁንም፥ ጻፎቻችሁንም ሰብስቡልኝ፤ 29 ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንድትረክሱ፥ ካዘዝኋችሁም መንገድ ፈቀቅ እንድትሉ አውቃለሁና። በእጃችሁም ሥራ ታስቈጡት ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ስላደረጋችሁ፥ በኋለኛው ዘመን ክፉ ነገር ያገኛችኋል።” የሙሴ መዝሙር 30 ሙሴም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ ጆሮ የዚህችን መዝሙር ቃሎች እስከ መጨረሻው ድረስ ተናገረ። |