ኢሳይያስ 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የምስጋና መዝሙር 1 በዚያም ቀን እንዲህ ትላለህ፥ “አቤቱ፥ ተቈጥተኸኛልና፥ ቍጣህንም ከእኔ መልሰሃልና፥ ዳግመኛም ይቅር ብለኸኛልና አመሰግንሃለሁ። 2 እነሆ፥ አምላኬ መድኀኒቴ ነው፤ ጌታ እግዚአብሔር ክብሬና ዝማሬዬ ነው፤ መድኀኒቴም ሆኖአልና በእርሱ ታምኜአለሁ፤ አልፈራምም።” 3 ውኃውንም ከሕይወት ምንጮች በደስታ ትቀዳላችሁ። 4 በዚያም ቀን እንዲህ ትላላችሁ፥ “እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ክብሩን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደ ሆነ አስታውሱ። 5 ታላቅ ሥራ ሠርቶአልና ለእግዚአብሔር ስም ዘምሩ፤ ይህንም በምድር ሁሉ ላይ አስታውቁ። 6 አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ፤ የእስራኤል ቅዱስ በመካከልሽ ከፍ ከፍ ብሎአልና።” |