ዘፀአት 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እስራኤል ቀይ ባሕርን መሻገራቸው 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “ተመልሰው በመግደሎና በባሕር መካከል፥ በብኤልሴፎን ፊት ለፊት ባለው ገላጣ መንደር አንጻር እንዲሰፍሩ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ ከእርሱም አጠገብ በባሕር ዳር ትሰፍራላችሁ። 3 ፈርዖንም ለሕዝቡ ስለ እስራኤል ልጆች፦ ‘በምድር ይቅበዘበዛሉ፤ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው’ ይላል። 4 እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፤ እርሱም ከኋላቸው ይከተላቸዋል፤ እኔም በፈርዖንና በሠራዊቱ ሁሉ ላይ እከብራለሁ፤ ግብፃውያንም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። 5 ሕዝቡም እንደ ኰበለሉ ለግብፅ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የሹሞቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና፥ “እንዳይገዙልን የእስራኤልን ልጆች የለቀቅነው ምን ማድረጋችን ነው?” አሉ። 6 ፈርዖንም ሰረገላውን አሰናዳ፤ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ሰበሰበ። 7 ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችንም፥ የግብፅንም ፈረሶች ሁሉ ወስዶ ሁሉንም ከሦስት ከፈላቸው። 8 እግዚአብሔርም የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንንና የሹሞቹን ልብ አጸና፤ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ። 9 ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶች፥ ሰረገሎቹም፥ ፈረሰኞቹም፥ ሠራዊቱም ሁሉ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ ዳር በብኤልሴፎን ፊት ለፊት ባለው ገላጣ መንደር አንጻርም ሰፍረው አገኙአቸው። 10 ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዐይናቸውን አነሡ፤ እነሆም፥ ግብፃውያን ሲከተሉአቸው አዩ፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 11 ሙሴንም አሉት፥ “በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድን ነው? 12 በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻለናልና፦ ‘ተወን፤ ለግብፃውያን እንገዛ’ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን?” 13 ሙሴም ለሕዝቡ፥ “አትፍሩ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና ቁሙ፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። 14 እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተም ዝም ትላላችሁ” አላቸው። 15 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ለምን ትጮኽብኛለህ? ከብቶቻቸውን እንዲነዱ ለእስራኤል ልጆች ንገር። 16 አንተም በትርህን አንሣ፤ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። 17 እነሆም፥ እኔ የፈርዖንንና የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ፥ በሰረገሎቹም፥ በፈረሰኞቹም ላይ እከብራለሁ። 18 ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ፥ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር በአገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” 19 በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዐምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፤ 20 በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ጭጋግና ጨለማ ነበረ፤ ሌሊቱም አለፈ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። 21 ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የአዜብ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፤ ባሕሩንም አደረቀው፤ ውኃውም ተከፈለ። 22 የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። 23 ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች፥ ፈረሰኞቹም ሁሉ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። 24 ንጋትም በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዐምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠራዊት ተመለከተ፤ የግብፃውያንንም ሠራዊት አወከ። 25 የሰረገሎቹንም መንኰራኵር አሰረ፤ ወደ ጭንቅም አገባቸው፤ ግብፃውያንም፥ “እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ” አሉ። ግብፃውያን እንደ ሰጠሙ 26 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ውኃውም በግብፃውያን፥ በሰረገሎቻቸውም፥ በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ፤ ይሸፍናቸውም።” 27 ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፤ እግዚአብሔርም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው። 28 ውኃውም ተመልሶ በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን፥ ፈረሰኞችንም፥ የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደነ፤ ከመጡትም ሁሉ አንድ ስንኳ የቀረ የለም። 29 የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ሄዱ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። 30 እግዚአብሔርም በዚያ ቀን እስራኤልን ከግብፃውያን እጅ አዳናቸው፤ እስራኤልም ግብፃውያን እንደ ሞቱ በባሕር ዳር አዩ። 31 እስራኤልም እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርም አመኑ፤ ባሪያውንም ሙሴን አከበሩ። |