ዘፍጥረት 46 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ያዕቆብ ከቤተ ሰቡ ጋር ወደ ግብፅ መሄዱ 1 እስራኤልም ለእርሱ ያለውን ሁሉ ይዞ ተነሣ፤ ወደ ዐዘቅተ መሐላም መጣ፤ መሥዋዕትንም ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ ሠዋ። 2 እግዚአብሔርም በሌሊት ራእይ፥ “ያዕቆብ ያዕቆብ” ብሎ ለእስራኤል ተናገረው። እርሱም “ምንድን ነው?” አለ። 3 አለውም፥ “የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ወደ ግብፅ መውረድን አትፍራ፤ በዚያ ትልቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና። 4 እኔ ወደ ግብፅ አብሬህ እወርዳለሁ፤ ከዚያም ደግሞ እኔ አወጣሃለሁ፤ ልጅህ ዮሴፍም እጁን በዐይንህ ላይ ያኖራል።” 5 ያዕቆብም ከዐዘቅተ መሐላ ተነሣ፤ የእስራኤልም ልጆች አባታቸውን፥ ገንዘባቸውን፥ ሚስቶቻቸውንም እነርሱን ያመጡባቸው ዘንድ ዮሴፍ በላካቸው ሰረገሎች ጭነው ወሰዱ። 6 ጓዛቸውን፥ በከነዓን ሀገርም ያገኙትን ጥሪታቸውን ሁሉ ይዘው ያዕቆብና ዘሩ ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ መጡ፤ 7 ወንዶች ልጆቹንና የወንዶች ልጆቹን ወንዶች ልጆች፥ ሴቶች ልጆቹንና የሴቶች ልጆቹን ሴቶች ልጆች፥ ዘሩንም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ አስገባቸው። 8 ከአባታቸው ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት የእስራኤል ልጆች ስም ይህ ነው፤ ያዕቆብና ልጆቹ፤ የያዕቆብ በኵር ሮቤል። 9 የሮቤልም ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፍሉስ፥ አስሮን፥ ከርሜ። 10 የስምዖን ልጆች፤ ይሙኤል፥ ያሚን፥ አኡድ፥ ያኪን፥ ሱሐር፥ የከነዓናዊት ልጅ ሳዑል። 11 የሌዊም ልጆች፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ። 12 የይሁዳም ልጆች፤ ዔር፥ አውናን፥ ሴሎም፥ ፋሬስ፥ ዛራ፤ ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ። የፋሬስም ልጆች እኒህ ናቸው፤ ኤስሮም፥ ይሞሔል፤ 13 የይሳኮርም ልጆች፤ ቶላዕ፥ ፎሓ፥ ያሱብ፥ ስምራ። 14 የዛብሎንም ልጆች፤ ሳሬድ፥ አሎን፥ አሌል። 15 ልያ በመስጴጦምያ በሶርያ ለያዕቆብ የወለደቻቸው ልጆችና ሴቲቱ ልጅዋ ዲና እነዚህ ናቸው፤ ወንዶችም ሴቶችም ልጆችዋ ሁሉ ሠላሳ አራት ነፍስ ናቸው። 16 የጋድም ልጆች፤ ስፎን፥ ሐጊ፥ ሱኒ፥ አዜን፥ አድ፥ አሮሐድ፥ አርሔል። 17 የአሴርም ልጆች፤ ኢያምን፥ ኢያሱ፥ኢዩል፥ በሪዓ፥ እኅታቸው ሳራ፤ የበሪዓ ልጆችም፤ ኮቦር፥ መልኪኤል። 18 ላባ ለልጁ ለልያ የሰጣት የዘለፋ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ እርስዋም እነዚህን ዐሥራ ስድስቱን ነፍስ ለያዕቆብ ወለደች። 19 የያዕቆብ ሚስት የራሔል ልጆች ዮሴፍና ብንያም ናቸው። 20 ለዮሴፍም በግብፅ ምድር ልጆች ተወለዱለት፤ እነርሱም የሄልዮቱ ከተማ ካህን የጴጤፌራ ልጅ አስኔት የወለደችለት ምናሴና ኤፍሬም ናቸው። ሶርያዊት ዕቅብቱ የወለደችለት የምናሴም ልጅ ማኪር ነው። ማኪርም ገለዓድን ወለደ፤ የምናሴም ወንድም የኤፍሬም ልጆች ሱታላና ጠኀን ናቸው። የሱታላ ልጅም ኤዴን ነው። 21 የብንያምም ልጆች፤ ቤላ፥ ቦኮር፥ አስቤር፤ የቤላ ልጆችም፤ ጌራ፥ ኖሔማን፥ አሒ፥ ሮስ፥ ማንፌን፥ ሑፈም፤ ጌራም አራድን ወለደ። 22 ለያዕቆብ የተወለዱለት የራሔል ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ሁሉም ዐሥራ አራት ነፍስ ናቸው። 23 የዳንም ልጅ አሳ ነው። 24 የንፍታሌምም ልጆች፤ አሴሔል፥ ጎሂን፥ ዮሴር ሴሌም። 25 ላባ ለልጁ ለራሔል የሰጣት የባላ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህንም ለያዕቆብ ወለደችለት፤ ባላ የወለደቻቸው ሁሉም ሰባት ነፍስ ናቸው። 26 ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት ሰዎች ሁሉ ከጕልበቱ የወጡት፥ ከልጆቹ ሚስቶች ሌላ፥ ሁላቸው ስድሳ ሰባት ናቸው። 27 በግብፅ ምድር የተወለዱለት የዮሴፍም ልጆች ሁለት ናቸው፤ ወደ ግብፅ የገቡት የያዕቆብ ቤተ ሰዎች ሁሉ ሰባ ናቸው። ያዕቆብና ቤተ ሰቡ በግብፅ 28 ይሁዳንም ኤሮስ በምትባል በራምሴ ከተማ እንዲቀበለው በፊቱ ወደ ዮሴፍ ላከው፤ 29 ዮሴፍም ሰረገላውን አዘጋጀ፤ አባቱንም እስራኤልን ሊገናኘው ወደ ኤሮስ ከተማ ወጣ፤ በአየውም ጊዜ አንገቱን አቀፈው፤ ረዥም ጊዜም አለቀሰ። 30 እስራኤልም ዮሴፍን፥ “አንተ ገና በሕይወት ሳለህ ፊትህን አይችአለሁና አሁን ልሙት” አለው። 31 ዮሴፍም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፥ “እኔ ሄጄ ለፈርዖን እንዲህ ብዬ እነግረዋለሁ፦ በከነዓን ምድር የነበሩት ወንድሞችና የአባቴ ቤተ ሰዎች ወደ እኔ መጥተዋል፤ 32 እነርሱም ከብት ጠባቂዎች፥ መንጋ አርቢዎች ናቸው፤ በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን፥ ያላቸውንም ሁሉ አመጡ። 33 ፈርዖንም ቢጠራችሁ ተግባራችሁስ ምንድን ነው? ቢላችሁ፥ 34 በግ ጠባቂ ሁሉ ለግብፅ ሰዎች ርኩስ ነውና በዐረብ በኩል በጌሤም እንድትቀመጡ እኛ አገልጋዮችህ ከብላቴንነታችን ጀምረን እስከ አሁን ድረስ እኛም አባቶቻችንም እንስሳ አርቢዎች ነን” በሉት። |