ዘፍጥረት 31 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ያዕቆብ ከላባ መሸሹ 1 ያዕቆብም የላባ ልጆች ያሉትን ነገር፥ “ያዕቆብ ለአባታችን የሆነውን ሁሉ ወሰደ፤ ይህንም ሁሉ ክብር ከአባታችን ከብት አገኘ” ሲሉ ሰማ። 2 ያዕቆብም የላባን ፊት አየ፤ እነሆም፥ ከእርሱ ጋር እንደ ዱሮው አልሆነም። 3 እግዚአብሔርም ያዕቆብን፥ “ወደ አባትህና ወደ ዘመዶችህ ሀገር ተመለስ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” አለው። 4 ያዕቆብም ልኮ ራሔልንና ልያን ወደ በጎቹ መሰማሪያ ወደ ሜዳ ጠራቸው፤ 5 እንዲህም አላቸው፥ “እነሆ፥ የአባታችሁ ፊት እንደ ዱሮ ከእኔ ጋር እንዳልሆነ አያለሁ፤ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር ነው። 6 እኔ ባለኝ ጕልበቴ ሁሉ አባታችሁን እንዳገለገልሁ ታውቃላችሁ። 7 አባታችሁ ግን አሳዘነኝ፥ ደመወዜንም ዐሥር ጊዜ ለወጠ፤ እግዚአብሔር ግን ክፉን ያደርግብኝ ዘንድ አልፈቀደለትም። 8 ደመወዝህ ዝንጕርጕሮቹ ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ዝንጕርጕሮችን ወለዱ፤ ነጫጮቹ ደመወዝህ ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ነጫጮችን ወለዱ። 9 እግዚአብሔርም የአባታችሁን በጎች ሁሉ ነሥቶ ለእኔ ሰጠኝ። 10 እንዲህም ሆነ፤ በጎቹ በሚፀንሱ ጊዜ ዐይኔን አንሥቼ በሕልም አየሁ፤ እነሆም፥ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ነጭ፥ ዝንጕርጕሮችና ሐመደ ክቦ ነበሩ። 11 እግዚአብሔርም በሕልም፦ ‘ያዕቆብ ያዕቆብ’ አለኝ፤ እኔም፦ ‘እነሆኝ ምንድን ነው?’ አልሁት። 12 እንዲህም አለኝ፦ ዐይንህን አቅንተህ እይ፤ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ነጭ፥ ሐመደ ክቦና ዝንጕርጕሮች ናቸው፤ ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን አይቻለሁና። 13 ሐውልቱን ዘይት በቀባህባት፥ በዚያች ለእኔ ስእለት በተሳልህባት ሀገር የተገለጥሁልህ ፈጣሪህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። አሁንም ተነሥተህ ከዚህ ሀገር ውጣ፤ ወደ ተወለድህባትም ምድር ተመለስ፤ እኔም ከአንተ ጋር እኖራለሁ።” 14 ራሔልና ልያም መልሰው እንዲህ አሉት፥ “በአባታችን ቤት ለእኛ ድርሻ ወይም ርስት በውኑ አለን? 15 እኛ በእርሱ ዘንድ እንደ ባዕድ የተቈጠርን አይደለምን? እርሱ እኛን ሽጦ ዋጋችንን በልቶአልና። 16 ስለዚህም እግዚአብሔር ከአባታችን የነሣው ይህ ሁሉ ሀብትና ክብር ለእኛና ለልጆቻችን ነው፤ አሁንም እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ አድርግ።” 17 ያዕቆብም ተነሣ፤ ልጆቹንና ሚስቶቹንም በግመሎች ላይ አስቀመጠ። 18 መንጎቹንም ሁሉ፥ የቤቱንም ዕቃ ሁሉ፥ በሁለቱ ወንዞች መካከል ሳለ ያገኛቸውን ከብቶች ሁሉ ይዞ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ ከነዓን ምድር ሄደ። 19 ላባ ግን በጎቹን ለመሸለት ሄዶ ነበር፤ ራሔልም የአባቷን ጣዖቶች ሰረቀች። 20 ያዕቆብም ነገሩን ከሶርያዊው ከላባ ሰወረ፤ እንደሚሄድም አልነገረውም። 21 እርሱም ያለውን ሁሉ ይዞ ኰበለለ፤ ተነሥቶም ወንዙን ተሻገረ፤ በገለዓድ ተራራም አደረ። ላባ ያዕቆብን መከታተሉ 22 ለሶርያዊው ላባም ያዕቆብ እንደ ኰበለለ ነገሩት። 23 ላባም ወንድሞቹን ሁሉ ይዞ የሦስት ቀን መንገድ ተከተላቸው፤ በገለዓድ ተራራም ላይ አገኛቸው። 24 እግዚአብሔርም ወደ ሶርያዊው ወደ ላባ በሌሊት በሕልም መጥቶ፥ “በባሪያዬ በያዕቆብ ላይ ክፉ ነገር እንዳትናገር ተጠንቀቅ” አለው። 25 ላባም ያዕቆብን አገኘው፤ ያዕቆብም ድንኳኑን በተራራው ላይ ተክሎ ነበር፤ ላባም ወንድሞቹን በገለዓድ ተራራ አስቀመጣቸው። 26 ላባም ያዕቆብን አለው፥ “ለምን እንዲህ አደረግህ? ከእኔ በስውር የኰበለልህ? ልጆችንስ ሰርቀህ በሰይፍ እንደማረከ የወሰድኻቸው? 27 ብትነግረኝ ኑሮ በደስታና በሐሴት፥ በዘፈን፥ በከበሮና በበገና በሸኘሁህ ነበር። 28 ወይስ ወንዶቹንና ሴቶቹን ልጆችን እስም ዘንድ አይገባኝምን? አሁንም ይህን እንደ አላዋቂ አደረግህ። 29 አሁንም በአንተ ላይ ክፉ ማድረግ በቻልሁ ነበር፤ ነገር ግን የአባትህ አምላክ ትናንት፦ በያዕቆብ ላይ ክፉ እንዳታደርግ ተጠንቀቅ ብሎ ነገረኝ። 30 አሁንም የአባትህን ቤት ከናፈቅህ ሂድ፤ ነገር ግን አምላኮቼን ለምን ሰረቅህ?” 31 ያዕቆብም መለሰ፤ ላባንም እንዲህ አለው፥ “ልጆችህንና ገንዘቤን ሁሉ ከእኔ የምትቀማኝ ስለመሰለኝና ስለፈራሁ ይህን አደረግሁ።” 32 ያዕቆብም አለ፥ “አምላኮችህን የምታገኝበት ሰው ግን እርሱ ይሙት፤ ገንዘብህም በእኔ ዘንድ ካለ በወንድሞቻችን ፊት እይ፤ ለአንተም ውሰደው” አለ። ያዕቆብ ሚስቱ ራሔል እንደ ሰረቀቻቸው አያውቅም ነበርና። 33 ላባም ወደ ያዕቆብ ድንኳንና ወደ ልያም ድንኳን ገባና በረበረ፤ አላገኘምም፤ ከዚያም ወጣና ወደ ሁለቱ ዕቁባቶቹ ድንኳን ገባ፤ ነገር ግን አላገኘም። ወደ ራሔልም ድንኳን ገባ። 34 ራሔልም የአባቷን ጣዖቶች ወስዳ ከግመል ኮርቻ በታች ሸሸገች፤ በላዩም ተቀመጠችበት። ላባም ድንኳኑን ሁሉ ፈለገ፤ አንዳችም አላገኘም። 35 እርስዋም አባቷን፥ “ጌታዬ በፊትህ ለመቆም ስላልቻልሁ የአቀለልሁህ አይምሰልህ፤ በሴቶች የሚደርስ ግዳጅ ደርሶብኛልና” አለችው። ላባም የራሔልን ድንኳን በረበረ፤ ነገር ግን ጣዖቶቹን አላገኘም። 36 ያዕቆብም ተቈጣ፤ ላባንም ወቀሰው፤ ያዕቆብም መለሰ፤ ላባንም እንዲህ አለው፥ “የበደልሁህ በደል ምንድን ነው? ኀጢአቴስ ምንድን ነው? ይህን ያህል ያሳደድኸኝ? 37 አሁንም ዕቃዬን ሁሉ በረበርህ፤ ከቤትህስ ዕቃ ሁሉ ምን አገኘህ? እነርሱ በእኛ በሁለታችን መካከል ይፈርዱ ዘንድ በወንድሞችና በወንድሞችህ ፊት አቅርበው። 38 ሃያ አንድ ዓመት በጎችህንና ፍየሎችህን ስጠብቅ ኖርሁ፥ ከበጎችህም ጠቦቶችን አልበላሁም፤ 39 አውሬ የሰበረውንም አላመጣሁልህም ነበር፤ በቀንም ሆነ በሌሊት የተሰረቀ ቢኖር ከእኔ እከፍልህ ነበር። 40 የቀን ሐሩር፥ የሌሊት ቍር ይበላኝ ነበር፤ ዕንቅልፍም ከዐይኔ ጠፋ። 41 ለአንተ ቤት የተገዛሁልህ ዛሬ ሃያ አንድ ዓመት ነው፤ ዐሥራ አራት ዓመት ስለ ሁለቱ ሴቶች ልጆችህ፥ ሰባት ዓመት ስለ በጎችህ ተገዛሁልህ፤ ደመወዜንም ዐሥር ጊዜ ለዋወጥኸው። 42 የአባቴ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም ፍርሀት ከእኔ ጋር ባይሆንስ ዛሬ ባዶ እጄን በሰደድኸኝ ነበር፤ እግዚአብሔር መዋረዴንና የእጆችን ድካም አየ፤ ትናንትም ገሠጸህ።” የያዕቆብና የላባ ስምምነት 43 ላባም ለያዕቆብ እንዲህ ብሎ መለሰለት፥ “ሴቶቹ ልጆች ልጆች ናቸው፤ ወንዶቹም ልጆች ልጆች ናቸው፤ መንጎቹም ከብቶች ናቸው፤ ይህ የምታየው ሁሉ የእኔ ነው፤ የልጆችም ሀብት ነው፤ ዛሬም በእነዚህ በሴቶች ልጆችና በወለዱአቸው ልጆቻቸው ላይ ምን አደርጋለሁ? 44 አሁንም ና፤ አንተና እኔ ቃል ኪዳን እንጋባ፤ በእኔና በአንተ መካከል ምስክር ይሁን።” 45 ያዕቆብም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አቆመ። 46 ያዕቆብም ወንድሞቹን፥ “ድንጋይ ሰብስቡ” አላቸው፤ እነርሱም ድንጋይ ሰብስበው ከመሩ፤ በድንጋዩም ክምር ላይ በሉ። 47 ላባም፥ “ይህች የድንጋይ ክምር በእኔና በአንተ መካከል ምስክር ትሁን” አለው። ላባም “ወግረ ስምዕ” ብሎ ጠራት፤ ያዕቆብም እንዲሁ አላት። 48 ላባም፥ “ይህች ያቆምኋት የድንጋይ ክምር በእኔና በአንተ መካከል ዛሬ ምስክር ናት” አለ። ስለዚህም ስምዋ ወግረ ስምዕ ተባለ። 49 ላባም አለው፥ “እኛ አንዳችን ከሌላው እንለያያለንና ራእይን የገለጠልኝ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ሆኖ ይመልከት። 50 ልጆችን ብትበድላቸው ወይም በላያቸው ላይ ሚስቶችን ብታገባባቸው እነሆ፥ ከእኛ ጋር ያለ ሰው እንደሌለ አስተውል፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ምስክር ነው።” 51 ላባም ያዕቆብን አለው፥ “እነሆ፥ ይህች የድንጋይ ክምርና ይህችም ሐውልት ምስክሮች ናቸው። 52 እኔ ወደ አንተ በክፋት ባልፍ ይህች የድንጋይ ክምር፥ ይህችም ሐውልት በክፉ ነገር ትከተለኝ። 53 አንተም ወደ እኔ ብታልፍ የአብርሃም አምላክ የናኮርም አምላክ በእኛ መካከል ይፍረድ።” ያዕቆብም በአባቱ በይስሐቅ አምላክ ማለ። 54 ያዕቆብም በተራራው ላይ መሥዋዕትን ሠዋ፤ ወንድሞቹንም ጠራ፤ እነርሱም በሉ፤ ጠጡም፤ በዚያም በተራራው አደሩ። 55 ላባም ማልዶ ተነሥቶ ወንዶችንና ሴቶችን ልጆቹን ሳመ፤ ባረካቸውም፤ ላባም ተመልሶ ወደ ስፍራው ሄደ። |