ዘሌዋውያን 26 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በመታዘዝ የሚገኝ በረከት ( ዘዳ. 7፥12-24 ፤ 28፥1-14 ) 1 “ለእናንተ በእጅ የተሠራ ጣዖት አታድርጉ፤ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና። 2 ሰንበታቴንም ጠብቁ፤ የቀደስኋቸውንም ፍሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝና። 3 “በሥርዐቴ ብትሄዱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ፥ ብታደርጉትም፥ 4 ዝናሙን በወቅቱ አዘንማለሁ፤ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች፤ የሜዳው ዛፎችም ፍሬያቸውን ይሰጣሉ። 5 የእህሉም ማበራየት በእናንተ ዘንድ እስከ ወይኑ መቈረጥ ይደርሳል፤ የወይኑም መቈረጥ እስከ እህሉ መዝራት ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፤ በምድራችሁም ላይ ተዘልላችሁ ትኖራላችሁ። 6 በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፤ ትተኛላችሁ፤ የሚያስፈራችሁም የለም፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ። 7 ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፤ በፊታችሁም በሰይፍ ይወድቃሉ። 8 ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፤ መቶውም ዐሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 9 ወደ እናንተም እመለከታለሁ፤ አባዛችኋለሁ፤ ከፍ ከፍም አደርጋችኋለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። 10 ብዙ ጊዜ የተቀመጠውን፥ የከረመውንም እህል ትበላላችሁ፤ አዲሱንም ታስገቡ ዘንድ የከረመውን ታወጣላችሁ። 11 ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። 12 በመካከላችሁም እመላለሳለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። 13 ባሪያዎች ከነበራችሁበት ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነታችሁን ቀንበር ሰብሬአለሁ፤ በግልጽም አወጣኋችሁ። ባለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣት ( ዘዳ. 28፥15-68 ) 14 “ነገር ግን ባትሰሙኝ፥ እነዚህንም ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ 15 ሥርዐቴንም ብትንቁ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ እንዳታደርጉ፥ ቃል ኪዳኔንም እንድታፈርሱ ሰውነታችሁ ፍርዴን ብትሰለች፥ 16 እኔም እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሀትን፥ ክሳትንም፥ ዐይናችሁንም የሚያፈዝዝ፥ ሰውነታችሁንም የሚያጠፋ ትኩሳት አወርድባችኋለሁ፤ ዘራችሁንም በከንቱ ትዘራላችሁ፤ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና። 17 ፊቴንም አከብድባችኋለሁ፤ በጠላቶቻችሁም ፊት ትወድቃላችሁ፤ የሚጠሏችሁም ያሸንፉአችኋል። ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። 18 እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኀጢአታችሁ በቅጣታችሁ ላይ ሰባት እጥፍ መቅሠፍትን እጨምራለሁ። 19 የትዕቢታችሁን ስድብ አጠፋለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። 20 ጕልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም እህልዋን አትሰጥም፤ የዱር ዛፎችም ፍሬያቸውን አይሰጡም። 21 “ከዚያም በኋላ በእንቢተኝነት ብትሄዱብኝ፥ ልትሰሙኝም ባትፈቅዱ እንደ ኀጢአታችሁ መጠን በመቅሠፍት ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ። 22 በእናንተ ላይ ክፉዎች የምድርን አራዊት እሰድዳለሁ፤ ይበሉአችኋል፤ እንስሶቻችሁንም ያጠፋሉ፤ እናንተንም ያሳንሳሉ፤ መንገዶቻችሁም በረሃ ይሆናሉ። 23 “እስከዚህም ድረስ ባትቀጡ፥ አግድማችሁም ብትሄዱ፥ 24 እኔ ደግሞ አግድሜ በቍጣ እሄድባችኋለሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እበቀላችኋለሁ። 25 የቃል ኪዳኔንም በቀል ይበቀልባችሁ ዘንድ ሰይፍ አመጣባችኋለሁ፤ ወደ ከተማችሁም ትሸሻላችሁ፤ ቸነፈርንም እሰድድባችኋለሁ። በጠላቶቻችሁም እጅ ተላልፋችሁ ትሰጣላችሁ፤ 26 በእህል ረሃብ ባስጨነክኋችሁ ጊዜ ዐሥር ሴቶች እንጀራ በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፤ በሚዛንም መዝነው እንጀራችሁን ይመልሱላችኋል፤ በበላችሁም ጊዜ አትጠግቡም። 27 እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ አግድማችሁም ብትሄዱብኝ፥ 28 እኔ ደግሞ አግድሜ በቍጣ እሄድባችኋለሁ፤ እንደ ኀጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። 29 የወንዶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ፤ የሴቶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ። 30 የኮረብታ መስገጃዎቻችሁን አፈርሳለሁ፤ በእጅ የተሠሩ የዕንጨት ምስሎቻችሁንም አጠፋለሁ፤ ሬሳችሁንም በጣዖቶቻችሁ ሬሳዎች ላይ እጥላለሁ፤ ነፍሴም ትጸየፋችኋለች። 31 ከተሞቻችሁንም ባድማ አደርጋለሁ፤ መቅደሶቻችሁንም አፈርሳለሁ፤ የመሥዋዕታችሁንም መዓዛ አላሸትትም። 32 ምድሪቱንም የተፈታች አደርጋለሁ፤ የሚቀመጡባት ጠላቶቻችሁም ከእርስዋ የተነሣ ይደነቃሉ። 33 እናንተንም በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ በሄዳችሁበትም ሁሉ ሰይፍ ታጠፋችኋለች፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፤ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ። 34 “በዚያም በተፈታችበት ዘመን ሁሉ እናንተም በጠላቶቻችሁ ምድር ሳላችሁ፥ ምድሪቱ ሰንበት በማድረግዋ ደስ ይላታል፤ በዚያም ጊዜ ምድሪቱ ታርፋለች፤ ስንበትንም በማድረግዋ ደስ ይላታል። 35 እናንተ ተቀምጣችሁባት በነበረ ጊዜ በሰንበቶቻችሁ አላረፈችም ነበርና በተፈታችበት ዘመን ሁሉ ታርፋለች። 36 በጠላቶቻቸውም ምድሮች ሳሉ ከእናንተ ተለይተው በቀሩት ላይ በልባቸው ድንጋጤን እሰድድባቸዋለሁ፤ በነፋስም የምትንቀሳቀስ የቅጠል ድምፅ ታሸብራቸዋለች፤ ከሰይፍ እንደሚሸሹ ይሸሻሉ ፤ 37 ማንም ሳያሳድዳቸው ከሰይፍ እንዲሸሹ እርስ በርሳቸው ይሰነካከላሉ፤ እናንተም በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም። 38 በአሕዛብም መካከል ትጠፋላችሁ፤ የጠላቶቻችሁም ምድር ትውጣችኋለች። 39 ከእናንተም ተለይተው የቀሩት ስለ ኀጢአታቸው ይጠፋሉ፤ በአባቶቻቸውም ኀጢአት ደግሞ በጠላቶቻቸው ምድር ይቀልጣሉ። 40 “እንደ ከዱኝ፥ ቸልም እንዳሉኝ፥ በፊቴም አግድመው እንደ ሄዱ፥ ኀጢአታቸውንና፥ የአባቶቻቸውን ኀጢአት ይናዘዛሉ። 41 እኔም ደግሞ አግድሜ ከእነርሱ ጋር በቍጣ ሄድሁ፤ በጠላቶቻቸውም ምድር አጠፋቸዋለሁ። ነገር ግን በዚያን ጊዜ ያልተገረዘው ልባቸው ያፍራል፤ ስለ ኀጢአታቸውም ይናዘዛሉ፤ 42 ያን ጊዜ እኔ ከያዕቆብ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ደግሞም ከይስሐቅ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን፥ ከአብርሃምም ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ምድሪቱንም አስባለሁ። 43 ምድርም ከእነርሱ መጥፋት የተነሣ ባዶ ትቀራለች፤ እነርሱም ሳይኖሩ በተፈታችበት ዘመን ዕረፍት ታደርጋለች፤ ፍርዴንም ስለ ናቁ፥ ነፍሳቸውም ሥርዐቴን ስለ ተጸየፈች የኀጢአታቸውን ቅጣት ይሸከማሉ። 44 ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝና እነርሱ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ፥ እስካጠፋቸው ድረስ ከእነርሱም ጋር ያለኝን ቃል ኪዳን እስካፈርስ ድረስ አልጥላቸውም፤ አልጸየፋቸውምም። 45 እኔ አምላካቸው እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብፅ ምድር ከግዞት ቤት እንዳወጣኋቸው የቀድሞ ቃል ኪዳናቸውን ስለ እነርሱ አስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝና።” 46 እግዚአብሔርም በእርሱና በእስራኤል ልጆች መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ እጅ የሰጣቸው ሥርዐቶችና ፍርዶች፥ ሕግጋትም እነዚህ ናቸው። |