ራእይ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)መግቢያና ሰላምታ 1 ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፤ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፤ 2 እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ። 3 ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው። 4-5 ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ ካለውና ከነበረው፥ ከሚመጣውም፥ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፥ ከታመነውም ምስክር፥ ከሙታንም በኵር፥ የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለወደደን፥ ከኀጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥ 6 መንግሥትም፥ ለአባቱም ለእግዚአብሔር ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኀይል ይሁን፤ አሜን። 7 እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዐይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፤ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፤ አሜን። 8 ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ “አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ፤” ይላል። የክርስቶስ በራዕይ መገለጥ 9 እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል ዮሐንስ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ። 10 በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፤ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ፤ 11 እንዲሁም “የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊላደልፊያም ወደ ሎዲቅያም በእስያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ፤” አለኝ። 12 የሚናገረኝንም ድምፅ ለማየት ዘወር አልሁ፤ ዘወርም ብዬ ሰባት የወርቅ መቅረዞች አየሁ፤ 13 በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፤ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰ ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር። 14 ራሱና የራሱ ጠጕርም እንደ ነጭ የበግ ጠጕር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፤ ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤ 15 እግሮቹም በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውሃዎች ድምፅ ነበረ። 16 በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፤ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፤ ፊቱም በኀይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ ነበረ። 17 ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ፤ እንዲህም አለኝ “አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው እኔ ነኝ፤ 18 ሕያውም እኔ ነኝ፤ ሞቼም ነበርሁ፤ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ። 19 እንግዲህ ያየኸውን አሁንም ያለውን ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ። 20 በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምሥጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላእክት ናቸው፤ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው። |