ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ ተረፈ ባሮክ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 አቤሜሌክም ተነሥቶ ከከተማ ወደ ውጭ ከወጣ በኋላ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 2 እነሆም፥ መልአክ መጥቶ ወደ ባሮክ መራው፤ በመቃብር ቤትም ተቀምጦ አገኘው። 3 ሰላምታም በተሰጣጡ ጊዜ እርስ በርሳቸው ተለቃቅሰው ተሳሳሙ፤ በሙዳዩም ውስጥ በለሱን አይቶ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አቀና። 4 እንዲህም ብሎ ጸለየ፤ “ለወዳጆቹ ለጻድቃን ዋጋቸውን የሚሰጣቸው አምላክ ገናና ነው፤ ነፍሴ ሆይ፥ ተዘጋጂ፤ ለቅዱስ ማደሪያሽ ለሥጋ ይህን እየነገርሽ ደስ ይበልሽ፤ ልቅሶሽም ወደ ደስታ ይመለስልሻል። 5 ከዚያም በኋላ የታመነው ይመጣል፤ ወደ ሬሳሽም ይመልስሻል፤ ድንግል ወደ ሆነው ወደ ሃይማኖትሽም ተመልከች። 6 እንደምትነሺም ወደ እነዚህ በለሶች ተመልከች፤ ከተለቀሙ ስድሳ ስድስት ዓመት ነው፤ አልደረቁም፤ አልተሉምም፤ ነገር ግን ወተታቸው እስከ ዛሬ ገና ይፈስሳል። 7 ኀጢአት የለብሽምና፥ የበለሱን ሙዳይ ከጠበቀ ከእውነተኛው መልአክም ዘንድ የታዘዝሺውን ትእዛዝ ጠብቀሻልና ሥጋዬ በአንቺ እንዲህ ያደርጋል፤ እርሱም ዳግመኛ በኀይሉ ይጠብቅሻል።” 8 ባሮክም እንዲህ ብሎ ከጸለየ በኋላ አቤሜሌክ መለሰ፤ “እኔን የሰወረ እግዚአብሔር ለኤርምያስ ወደ ባቢሎን የምንጽፋቸውን ቃሎች ይገልጥልን ዘንድ ዳግመኛ ተነሥተህ ጸልይ” አለው። 9 ባሮክም ጸለየ፤ እንዲህም አለ፥ “ኀያል አምላክ፥ ብርሃንም ከአፍህ የሚወጣ ጌታ ሆይ፥ እለምንህ ዘንድ እወድዳለሁ፤ 10 ለቸርነትህም እገዛለሁ፤ ስምህም ገናና ነው፤ እርሱንም መርምሮ ማወቅ የሚቻለው የለም። 11 በልቡናዬ ፈቃድህን ለማድረግ በደግነት የታወቅሁ እሆን ዘንድ፥ ለአገልጋይህ ለኤርምያስም ወደ ባቢሎን ጽፌ እልክ ዘንድ የኔን የባሪያህን ልመና ስማ።” 12 ይህንም ሲጸልይ መልአኩ መጥቶ ለባሮክ እንዲህ አለው፥ “ብሩህ ነገርን የምትመክር ባሮክ ሆይ፥ አንተ ወደ ኤርምያስ ትልክ ዘንድ ማንን እልካለሁ? ብለህ አታስብ። 13 ነገ ፀሐይ ሲወጣ ንስር ወደ አንተ ይመጣል፤ ወደ ኤርምያስም የምትልከውን ነገር አንተ መርምር፤ በመጽሐፍም ጻፍ።” 14 የእስራኤልን ልጆች እንዲህ በላቸው፥ “በእናንተ ዘንድ እንግዳ ሰው ቢኖር እስከ ዐሥራ አምስት ቀን ድረስ ከእናንተ ይለይ። 15 ከዚህም በኋላ ወደ ሀገራችሁ አገባችኋለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ እስከ ዐሥራ አምስት ቀንም ድረስ ከባቢሎን ያልተለየ ሰው ቢኖር ኤርምያስ ወደ ከተማ ገብቶ በባቢሎን ያሉ እስራኤልን ይዝለፋቸው፤ ይላል እግዚአብሔር።” 16 ይህንም ከተናገረ በኋላ መልአኩ ከባሮክ ዘንድ ሄደ። ባሮክም እስከ አደባባዩ ድረስ ሸኘው፤ ወረቀትና ጥቁር ቀለምም አመጣ። 17 የእግዚአብሔር አገልጋዩ ባሮክ እንዲህ ብሎ ደብዳቤ ጻፈ፥ “ስለ ስድባችንና ስለ ጥፋታችን ያዘንን ሆነን እንወጣ ዘንድ ፈጣሪያችን አልተወንምና ወደ ባቢሎን ለተማረከው ለኤርምያስ ደስታና ሐሤት ይሁን። 18 ስለዚህ ነገር ጌታችን እንባችንን አይቶ አዘነልን፤ አስቀድሞ ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለይስሐቅ፥ ለያዕቆብም ያጸናውን ቃል ኪዳን ዐሰበ። 19 መልአኩንም ወደ እኔ ልኮ ወደ አንተ የላክሁብህን ነገሮች ነገረኝ። 20 “ከግብፅ ምድርና ከእሳት ቤቶች ያወጣን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ያደረጋቸው ነገሮች እኒህ ናቸው፤ ልቡናችሁን ከፍ ከፍ አደረጋችሁ፤ በፊቱም አንገታችሁን አደነደናችሁ እንጂ ሕጉን ሁሉ አልጠበቃችሁምና። 21 እግዚአብሔር ከወዳጄ ከኤርምያስ አፍ ቃሌን አልሰማችሁም ብሏልና ለባቢሎን አገዛዝ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ ቃሌን የሰሙ ሰዎችን ግን ከባቢሎን አወጣቸዋለሁ፤ ከባቢሎንም ወጥተው በኢየሩሳሌም እንግዳ አይሆኑም። 22 መንገዳቸውንም ልታውቅባቸው ብትወድድ በዮርዳኖስ ውኃ ፈትናቸው፤ የዚህን ደብዳቤ ምልክት ያልሰማ ሰው ግን የበለጠ ምልክት ማኅተም አለ።” 23 ባሮክም እንዲህ ጽፎ ከመቃብር ቤት ወጣ፤ ንስሩም፥ “ሃይማኖትን የምታስተምር ባሮክ ሆይ፥ ቸር አለህን?” አለው። 24 ባሮክም፥ “ከሰማይ አዕዋፍ ሁሉ የተመረጥህ ነህና፥ በዐይኖችህም ብርሃን የታወቅህ ነህና ትናገራለህ። 25 አሁንም በዚህ ምን ልታደርግ መጣህ? ንገረኝ” አለው። ንስሩም፥ “የወደድኸውን ሁሉ ልትልከኝ ወደዚህ መጣሁ” አለው። 26 ባሮክም፥ “እነዚህን ነገሮች ለኤርምያስ ወደ ባቢሎን ማድረስ ትችላለህን?” አለው፤ ንስሩም፥ “ስለዚህ ተላክሁ” አለው። 27 ባሮክም ደብዳቤውን ያዘ፤ ከዚያ አቤሜሌክ ከሰጠው ከበለሱ ሙዳይም ዐሥራ አምስቱን በለስ አምጥቶ በንስሩ አንገት አሰረ። 28 “የአዕዋፍ ሁሉ ንጉሣቸው ንስር ሆይ፥ በሰላምና በደኅና ሂደህ ወሬያቸውን አምጣልን እልሃለሁ አለው። 29 ኖኅ የላከውን፥ ዳግመኛም ወደ እርሱ መመለስን እንቢ ያለውን ቁራ አትምሰለው። ነገር ግን ለኖኅ ቃሏን ሦስት ጊዜ የመለሰች ርግብን ምሰላት። 30 እንደዚሁም ሁሉ ለአንተ በጎ ነገር ይሆንህ ዘንድ እኒህን ያማሩ ነገሮች ለኤርምያስና ከእርሱ ጋራ ላሉ እስራኤል ውሰድ፤ አምላክ ለመረጣቸው ወገኖች ይህን ደስታ ንገራቸው። 31 አዕዋፍም ሁሉ ቢከብቡህ፥ ይገድሉህም ዘንድ ወድደው የጽድቅ ጠላቶች ሁሉ ቢከብቡህ ስለ እውነት ቀድመሃቸው ሂድ። 32 ጌታም ኀይልን ይሰጥሃል፤ የተወረወረ ፍላጻ ቀንቶ እንዲሄድ አንተም በፈጣሪህ ኀይል ቀንተህ ሂድ እንጂ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል” አለው። |