ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ከዚህም በኋላ ይህን ነገር ተናግሬ በጨረስሁ ጊዜ ባለፈችው በዚያች ሌሊት አስቀድሞ ወደ እኔ የመጣው ያ መልአክ ወደ እኔ ተላከ። 2 እንዲህም አለኝ፥ “ዕዝራ ሆይ፥ ተነሥ፤ እነግርህ ዘንድ ወደ አንተ የመጣሁ የእኔን ቃል ስማ።” 3 እኔም አልሁት፥ “ጌታዬ ተናገር፤” እርሱም አለኝ፥ “በአንድ ሰፊ ቦታ ባሕር አለች፤ እርስዋም ሰፊና ጥልቅ ናት። 4 ጠባብ የመግቢያ መንገድም አላት፤ የመስኖ ውኃ ቦይ ያህልም ትሆናለች። 5 ያያትና ያገኛት ዘንድ ወደዚያች ባሕር ሊገባ የወደደ ቢኖር ያን ጠባቡን መግቢያዋን ካላለፈ ወደ አደባባይዋ መግባት እንዴት ይችላል? 6 ወይም በሜዳ የተሠራች፥ ከበረከቱም ሁሉ የተመላች አንዲት ከተማ አለች። 7 የመግቢያዋም መንገድ ጠባብ ነው፤ በገደል ውስጥም ናት፤ በቀኝዋ እሳት፥ በግራዋም ጥልቅ ውኃ አለ። 8 አንዲት መንገድ በውኃና በእሳት መካከል አለች፤ መንገድዋም ከአንድ ሰው እግር ጫማ በቀር አትችልም። 9 ይህች ከተማ የተሰጠችው የሚወርሳት ሰው ቢኖር ያን ጠባቡን መንገድ ካላለፈ ርስቱን እንዴት ያገኛል?” 10 እኔም፥ “አቤቱ፥ እንደዚሁ ነው” አልሁት። እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “የእስራኤል ምድራቸው፥ ዕድል ፈንታቸውም እንዲሁ ነው። 11 ዓለምን ስለ እነርሱ ፈጥሬዋለሁና። 12 አዳምም ትእዛዜን ባፈረሰ ጊዜ የዚህ ዓለም ጎዳናው ሰንከልካላና ጠባብ፥ ጐድጓዳና የከፋ፥ መከራው የበዛ፥ ጻዕርና ጋርን የተመላ ሆነ። 13 የዚያኛው ዓለም ግን ጎዳናው ታላቅ ነው፤ ሰፊም ነው፤ ብሩህም ነው፤ ሞት የሌለበት የሕይወት ፍሬንም ያፈራል። 14 ሕያዋን የምትሆኑ እናንተም ያን ሰንከልካላና ያን ኀጢአት ካላለፋችሁት ለእናንተ የተዘጋጀውን ማግኘት አትችሉም። 15 አሁንስ አፈር የምትሆን አንተ ለምን ትታወካለህ? ሟች የምትሆን አንተስ ለምን ትናወጣለህ? 16 ያለውን ነው እንጂ የሚመጣውን በልብህ ለምን አታስብም?” የኃጥኣን ዕድል ፈንታ 17 እኔም መልሼ አልሁት፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ ጻድቃን ይህን ዓለም እንደሚወርሱት፥ ኃጥኣን ግን እንደሚጠፉ አንተ በሕግህ እነሆ፥ ተናገርህ። 18 ጻድቃን ሰፊውን ተስፋ እያደረጉ ጠባቡን ይታገሡታልና፤ ጠባቡን የሚታመኑ ኃጥኣን ግን ሰፊውን አያገኙትም።” 19 እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “አንተ በፍርድ ከአንዱ ከእግዚአብሔር የምትሻል አይደለህም፤ ከልዑልም አንተ የምትራቀቅ አይደለህም። 20 የሠራውን የእግዚአብሔርን ሕጉን ያቃለሉ እነዚያ ይጥፉ፤ 21 እግዚአብሔር ሕጉን ሠርተው በሕይወት እንዲኖሩ አዟቸዋልና። ሕጉን ቢጠብቁ ግን ባልተፈረደባቸውም ነበር። 22 ኃጥኣን ግን ካዱት፤ ተዉትም፤ ለራሳቸውም ክፉ አሳብን አሰቡ። 23 ሽንገላንና ዐመፅን ለራሳቸው ገንዘብ አደረጉ፤ ከዚህም ሁሉ ጋር እግዚአብሔር የለም አሉ፤ መንገዱንም ተዉ። 24 ሕጉንም ካዱ፤ ቃል ኪዳኑንም ቸል አሉ፤ በሥርዐቱም አልታመኑም፤ ሥራውንም ናቁ፤ አምልኮቱንም አላሰቡም። 25 ስለዚህ የተራቈተው ለተራቈቱት ነው፤ የተሞላውም ለተሞሉት ነው። የመሲሕ መንግሥት 26 “እኔ የነገርሁህ ምልክት የሚገለጥበት ወራት እነሆ፥ ይመጣልና፥ ዛሬ የምትታይ ከተማ ታልፋለች፤ ዛሬ የተሰወረች ምድርም ትገለጻለች። 27 እኔ ከነገርሁህ ከክፉ ሥራ የዳነ ሁሉ ክብሬን የሚያይ እርሱ ነው። 28 የእኔ መሲሕ አብረውት ካሉት ጋር ይገለጣልና፥ የሚነሡትንም ደስ ያሰኛቸዋል። 29 ከዚህ በኋላ ልጄ መሲሑ ይፈጽማል፤ አእምሮ ያለውም ሰው ሁሉ ይፈጽማል፤ 30 ዓለምም እንደ ቀድሞው ሰባት ቀን ዝም ያለውን ያህል ወደ ቀድሞ አነዋወሩ ይመለሳል፤ የሚቀርም የለም። 31 ከሰባት ቀን በኋላም የነቃበት ጊዜ የሌለ ሰው ይነሣል፤ የመዋቲ ሰው ዓለምም ያልፋል። 32 ምድርም የተቀበሩባትን ሰዎች ትመልሳለች፤ መሬትም በውስጡ ያረፉትን ሰዎች ይመልሳል፤ ከዚህም በኋላ አብያተ ነፍስ በውስጣቸው የተቀመጡ ነፍሳትን ይመልሳሉ። 33 ያንጊዜም ልዑል በፈጠረው በዙፋኑ ላይ ይገለጣል፤ ቸርነቱም ትመጣለች፤ ይቅርታውም ትመለሳለች፤ ትዕግሥቱም ትሰበሰባለች። 34 ቍርጥ ፍርድ ብቻ ይቀራል፤ ጽድቅ ትጸናለች፤ ሃይማኖትም ትገለጣለች። 35 ሰውን ሥራው ይከተለዋል፤ ዋጋውም ይገለጣል፤ ቅንነቱም ትነቃለች፤ ኀጢአቱም አታንቀላፋም። 36 የቍርጥ ፍርድ ጕድጓድ በዕረፍት ቦታ አንጻር ይከፈታል። በደስታ ገነትም አንጻር እሳተ ገሃነም ይገለጣል። 37 “ያንጊዜም ልዑል ከሙታን የተነሡ አሕዛብን፦ ‘እነሆ እዩ፤ የካዳችሁትም ማን እንደ ሆነ ዕወቁ፤ ያልተገዛችሁ ለማን ነው? የናቃችሁትስ የማንን ትእዛዝ ነው?” ይላቸዋል። 38 እነሆ፥ ወደ ፊታችሁ እዩ፤ በወዲህ ደስታና ዕረፍት አለ፤ በወዲያም ፍርድና እሳት አለ።’ 39 “ልዑል በፍርድ ቀን አሕዛብን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘የፍርድ ቀንስ እንዲህ ናት፤ ፀሐይ፥ ጨረቃም፥ ከዋክብትም የሉአትም። 40 ደመናም፥ መብረቅም፥ ነጐድጓድም፥ ነፋስም፥ ውኃም፥ ሰማይም፥ ጨለማም፥ ሌሊትም፥ መዓልትም የሉአትም፤ 41 ክረምት፥ በጋም፥ መከርም፥ ብርድም፥ ሐሩርም፥ ጥቅል ነፋስ፥ በረድ፥ ውርጭ፥ ጉም፥ ዝናም፥ ጠል የለባትም። 42 ማታና ጧት፥ ብርሃንና ብልጭልጭታ፥ ፋናና መብራት፥ ሁሉ ለእርሱ የተጠበቀለትን ያይበት ዘንድ ከእግዚአብሔር ከጌትነቱ ብርሃን ብቻ በቀር ይህ ሁሉ የለም። 43 የዚያች ሰዓት ርዝመቷ እንደ ሰባት ዓመት ይሆናል። 44 ፍርዱም፥ ቅጣቱም ይህ ነው’ ይህንም ለአንተ ብቻ ነገርሁ።” የሚድኑ ጥቂቶች ስለመሆናቸው 45 እኔም እንዲህ አልሁት፥ “አሁንም አቤቱ፥ ትእዛዝህን ጠብቀው የኖሩ ብፁዓን ናቸው። 46 ነገር ግን ስለ ጠየቅሁህ ነገር ከሕያዋን መካከል የማይበድል ማንነው? ከተወለደስ ወገን ሕግህን ያልተወ ማንነው? 47 አሁንም በሚመጣው ዓለም ደስ ታሰኛቸው ዘንድ ያለህ ጻድቃን ጥቂት እንደ ሆኑ፥ የሚፈረድባቸውም ብዙዎች እንደ ሆኑ አያለሁ። 48 ከዚህም ያሳተን፥ ወደ ጥፋትም የመራን፥ ወደ ሞት ጎዳናና ወደ ጥፋት መንገድም የወሰደን፥ ከዛሬ ጀምሮ ከእኛ ሕይወትን ያራቃት፥ ክፉ ልቡና በእኛ ጸንትዋልና። ይህም በተወለዱ ሁሉ ላይ ነው እንጂ በጥቂቶች ብቻ አይደለም።” 49 መልአኩም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “ስማኝ ልንገርህ፤ ዳግመኛም አስተምርሃለሁ። 50 ስለዚህ ነገር ልዑል ሁለት ዓለምን እንጂ አንድ ዓለምን ብቻ አልፈጠረም። 51 አንተ ግን የጻድቃን ቍጥራቸው ጥቂት ነው፤ ብዙዎችም አይደሉም፤ የኃጥኣን ግን ቍጥራቸው ብዙ ነው ብለሃልና፥ 52 እርሳሱን ከሸክላ ጋር ሥራ።” 53 እኔም አልሁት፥ “አቤቱ፥ ይህ እንዴት ይቻለኛል።” 54 እንዲህም አለኝ፥ “ይህን ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ምድርን ጠይቃት፤ ትነግርሃለችም፤ ተናገራት፤ ትመልስልሃለችም። 55 እነሆ፥ ወርቁን፥ ብሩንም፥ ናሱንም፥ ብረቱንና እርሳሱን፥ ሸክላውንም አንቺ ታስገኚዋለሽ በላት። 56 ብር ከወርቅ፥ ናስም ከብር፥ ብረትም ከናስ፥ እርሳስም ከብረት፥ ሸክላም ከእርሳስ ይበዛል። 57 እንግዲህ አንተ ራስህ ዕወቅ፥ የትኛው ይከብራል? የትኛውስ ይወደዳል? የሚበዛው ነውን? ወይስ የሚያንሰው ነው?” 58 እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “ጌታዬ ሆይ የሚያንሰው ይወደዳል፤ የሚበዛውም ይረክሳል።” 59 እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ያሰብኸውን አንተ ራስህ መዝነው፤ ከብዙው ካለው ይልቅ፥ ከጥቂቱ ያለው እጅግ ደስ ይለዋልና ከእኔ ዘንድ የሚገኝ የጻድቃን ደስታቸው እንደዚሁ ነው። 60 ስለሚድኑ ስለ ጥቂቶች ደስ ይለኛል፤ ክብሬን ያገኛሉና። ስሜም በእነርሱ ተመስግኖአልና። 61 ስለሚጠፉ ስለ ብዙዎች ልቡናዬን አላሳዝነውም። እነርሱ ዛሬ በእሳት ተመስለዋልና፥ እንደ እሳት ነበልባልም ሆነዋልና፥ እንደ ጢስም ነድደውና ተንነው ጠፍተዋልና።” የዕዝራ ልቅሶ 62 እኔም መለስሁለት፤ እንዲህም አልሁት፥ “ምድር ሆይ እንዳንቺ ያለ ልዩ ፍጥረት ከመሬትሽ ለምን ተገኘ? 63 ነገር ግን ክፉ ልቡና ከሚፈጠርልን ይልቅ ባይፈጠርልን በተሻለን ነበር። 64 ክፉ ልብም ከእኛ ጋር ያድጋል፤ ስለ እርሱም ይፈረድብናል፤ ሳናውቀው እንጐዳለንና። 65 የሰው ልጆች ያልቅሱ፤ የምድረ በዳ አውሬዎች ግን ደስ ይበላቸው፤ ከአዳም የተወለዱ ሁሉም ያልቅሱ፤ የእንስሳ መንጋዎችም ደስ ይበላቸው። 66 የሚጠብቃቸው ቍርጥ ፍርድ ስለሌለ፥ ፍርድንም ገሃነምንም ስለማያውቁት፥ ከሞቱም በኋላ መነሣትን ተስፋ ስለማያደርጉ እነርሱ ከእኛ እጅግ ይሻላሉና። 67 የምንነሣው ትንሣኤ ምን ይጠቅመናል? 68 የተወለድን ሁሉ በኀጢአት ተሰጠምን፤ ዐመፅንም ተሞላን፤ በደላችንም ጸና። 69 ከሞትን በኋላ ወደ ፍርድ ባንሄድ በተሻለን ነበር አልሁት።” |