“እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና።
በዚህም ምክንያት በሙሉ ትጋት በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ለመጨመር ጣሩ፤ በበጎነት ላይ ዕውቀትን፣
በዕውቀት ላይ ራስን መግዛት፣ ራስን በመግዛት ላይ መጽናትን፣ በመጽናት ላይ እውነተኛ መንፈሳዊነትን፣
በእውነተኛ መንፈሳዊነት ላይ ወንድማዊ መተሳሰብን፣ በወንድማዊ መተሳሰብ ላይ ፍቅርን ጨምሩ።
እነዚህ ባሕርያት ተትረፍርፈው ቢኖሯችሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ዳተኞችና ፍሬ ቢሶች ከመሆን ይጠብቋችኋል።
በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን።
ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤
ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም፤ እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሷልና።
እርሱ ግን፣ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” አለኝ። ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ።
ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንድንመላለስባቸው ያዘጋጀልንን መልካም የሆኑትን ሥራዎች እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።
እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ የተቀደሰ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ገንዘቡ ያደረገው ሕዝብ ናችሁ።
“የቀደመውን ነገር አታስቡ፤ ያለፈውን እርሱ።
እነሆ፤ አዲስ ነገር አደርጋለሁ! እርሱም አሁን ይበቅላል፤ አታስተውሉትምን? በምድረ በዳም መንገድ አዘጋጃለሁ፤ በበረሓም ምንጭ አፈልቃለሁ፤
እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ የደረሱት፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ፣ እውነተኛ መሆኑ እንዲረጋገጥና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ክብርንና ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው።
እግዚአብሔር አምላክሽ በመካከልሽ አለ፤ እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤ በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል።”
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋራ በሚመጣበት ጊዜ በአምላካችንና በአባታችን ፊት ነቀፋ የሌለባችሁና ቅዱሳን ሆናችሁ እንድትገኙ ልባችሁን ያጽና።
በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።
መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
ብፁዕ ነው፣ በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣ በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣ በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ፤
ነገር ግን ደስ የሚሠኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል።
እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።
ወንድሞቼ ሆይ፤ ልዩ ልዩ መከራ ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት፤
የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያመጣምና።
ስለዚህ ርኩሰትንና ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ክፋትን አስወግዳችሁ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን፣ በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በትሕትና ተቀበሉ።
ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ ሆናችሁ ራሳችሁን አታታልሉ።
ቃሉን የሚሰማ፣ ነገር ግን የሚለውን የማይፈጽም ሰው ፊቱን በመስተዋት እንደሚያይ ሰው ነው፤
ራሱንም አይቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል፤
ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ ተመልክቶ የሚጸና፣ የሰማውን የሚያደርግና የማይረሳ ሰው በሥራው ብሩክ ይሆናል።
አንደበቱን ሳይገታ፣ ልቡን እያሳተ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚል ሰው፣ ራሱን ያታልላል፤ ሃይማኖቱም ከንቱ ነው።
በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳትና ከዓለም ርኩሰት ራስን መጠበቅ ነው።
ምክንያቱም የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ።
ምንም የማይጐድላችሁ ፍጹማንና ምሉኣን እንድትሆኑ ትዕግሥት ሥራውን ይፈጽም።
እንግዲህ እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ ሸክም የሚሆንብንን ሁሉ፣ በቀላሉም ተብትቦ የሚይዘንን ኀጢአት አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ።
አባቶቻችን መልካም መስሎ እንደ ታያቸው ለጥቂት ጊዜ ይቀጡን ነበር፤ እግዚአብሔር ግን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለእኛ ጥቅም ሲል ይቀጣናል።
ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል።
ስለዚህ የዛለውን ክንዳችሁንና የደከመውን ጕልበታችሁን አበርቱ።
ዐንካሳው እንዲፈወስ እንጂ የባሰውኑ እንዳያነክስ “ለእግራችሁ ቀና መንገድ አብጁ።”
ከሰው ሁሉ ጋራ በሰላም ለመኖር የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ለመቀደስም ፈልጉ፤ ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት አይችልም።
ከእናንተ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጐድልበት፣ ደግሞም መራራ ሥር በቅሎ ችግር እንዳያስከትልና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ።
ለአንድ ጊዜ መብል ሲል ብኵርናውን እንደ ሸጠው እንደ ዔሳው፣ ማንም ሴሰኛ ወይም እግዚአብሔርን የማያከብር ሆኖ እንዳይገኝ ተጠንቀቁ።
በኋላም ይህንኑ በረከት ሊወርስ በፈለገ ጊዜ እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ በረከቱን በእንባ ተግቶ ቢፈልግም ለንስሓ ስፍራ ሊያገኝ አልቻለም።
ሊዳሰስ ወደሚችለውና በእሳት ወደሚቃጠለው ተራራ፣ ወደ ጨለማው፣ ወደ ጭጋጉና ወደ ዐውሎ ነፋሱ አልደረሳችሁም፤
ወደ መለከት ድምፅ ወይም ቃልን ወደሚያሰማ ድምፅ አልመጣችሁም፤ የሰሙትም ሌላ ቃል ተጨምሮ እንዳይናገራቸው ለመኑ።
የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።
ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጣችሁ፣ የሰላም ሐሳብ እንጂ ለክፉ አይደለም።
በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።
እግዚአብሔር ይረዳቸዋል፤ ይታደጋቸዋልም፤ ከክፉዎች እጅ ነጥቆ ያወጣቸዋል፤ እርሱን መጠጊያ አድርገዋልና ያድናቸዋል።
መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል፤
ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።
በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።
በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤ የሚከስሽንም አንደበት ሁሉ ትረቺያለሽ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፤ ከእኔ የሚያገኙትም ጽድቃቸው ይኸው ነው፤” ይላል እግዚአብሔር።