እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው፤
ወደ ሰፊ ስፍራ አወጣኝ፤ ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ።
“እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መለሰልኝ፤ እንደ እጄም ንጽሕና ከፈለኝ፤
የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፤ አምላኬንም በመተው ክፉ አላደረግሁም።
ሕጎቹ ሁሉ በፊቴ ናቸው፤ ከሥርዐቱም ዘወር አላልሁም።
በፊቱ ነቀፋ አልነበረብኝም፤ ራሴንም ከኀጢአት ጠብቄአለሁ።
እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ፣ በፊቱም እንዳለኝ ንጽሕና ብድራትን ከፈለኝ።
“ለታማኝ ሰው ታማኝ መሆንህን፣ ለፍጹም ሰው ፍጹም መሆንህን ታሳያለህ።
ለንጹሕ ሰው አንተም ንጹሕ መሆንህን፣ ለጠማማ ሰው ግን አንተም ጠማማ መሆንህን ታሳያለህ።
አንተ ትሑታንን ታድናለህ፤ ዐይንህ ግን ያዋርዳቸው ዘንድ፣ ትዕቢተኞችን ይመለከታል።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መብራቴ ነህ፤ እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል።
አምላኬ፣ የምሸሸግበት ዐለቴ፣ ጋሻዬና የድነቴ ቀንድ ነው፤ እርሱም ጠንካራ ምሽጌ፣ መጠጊያና አዳኜ ነው፤ ከዐመፀኛ ሰዎችም ታድነኛለህ።
ዐለቴና መድኀኒቴ እርሱ ብቻ ነው፤ መጠጊያዬም እርሱ ነው፤ እኔም አልናወጥም።
መዳኔና ክብሬ በእግዚአብሔር ነው፤ ብርቱ ዐለቴና መሸሸጊያዬ በእግዚአብሔር ነው።
አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ ይህን አልነገርኋችሁምን? ቀድሞስ አላሳወቅኋችሁምን? ለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አለን? ፈጽሞ! ወይም ሌላ ዐለት አለ? የለም! ማንንም አላውቅም።”
አምላካችን መጠጊያችንና ኀይላችን፣ በሚደርስብን መከራ ሁሉ የቅርብ ረዳታችን ነው።
“ዕረፉ፤ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ ዕወቁ፤ በሕዝቦች ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፤ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።”
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ነው፤ የያዕቆብም አምላክ መጠጊያችን ነው። ሴላ
ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ እንኳ፣ ተራሮችም ወደ ባሕር ጥልቅ ቢሰምጡ አንፈራም።
ነፍሴ ዕረፍት የምታገኘው በእግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ድነቴም የሚመጣልኝ ከርሱ ዘንድ ነው።
በዝርፊያ አትታመኑ፤ በቅሚያም ተስፋ አታድርጉ፤ በዚህ ብትበለጽጉም፣ ልባችሁ ይህን አለኝታ አያድርግ።
እግዚአብሔር አንድ ነገር ተናገረ፤ እኔም ይህን ሁለት ጊዜ ሰማሁ፤ ኀይል የእግዚአብሔር ነው።
ጌታ ሆይ፤ ምሕረትም የአንተ ነው፤ አንተ ለእያንዳንዱ፣ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ።
ዐለቴና መድኀኒቴ እርሱ ብቻ ነው፤ መጠጊያዬም እርሱ ነው፤ ከቶም አልናወጥም።
ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ ፈጥነህ አድነኝ፤ መጠጊያ ዐለት ሁነኝ፤ ታድነኝም ዘንድ ምሽግ ሁነኝ።
ከሰዎች ሤራ፣ በማደሪያህ ውስጥ ትሸሽጋቸዋለህ፤ ከአንደበት ጭቅጭቅም፣ በድንኳንህ ውስጥ ትከልላቸዋለህ።
በተከበበች ከተማ ውስጥ፣ የሚያስደንቅ ምሕረቱን ያሳየኝ፣ እግዚአብሔር ይባረክ።
እኔ በደነገጥሁ ጊዜ፣ “ከዐይንህ ፊት ተወግጃለሁ” አልሁ፤ አንተ ግን ወደ አንተ ስጮኽ፣ የልመናዬን ቃል ሰማህ።
እናንተ ቅዱሳኑ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ውደዱት! እግዚአብሔር ታማኞችን ይጠብቃል፤ ትዕቢተኞችን ግን ፈጽሞ ይበቀላቸዋል።
እግዚአብሔርን ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ፤ በርቱ፤ ልባችሁም ይጽና።
አንተ ዐለቴና መጠጊያዬ ነህና፣ ስለ ስምህ ስትል ምራኝ፤ መንገዱንም ጠቍመኝ።
ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በአጠገቤ ስፍራ አለ፤ አንተም በዐለት ላይ ትቆማለህ፤
ክብሬ በዚያ ሲያልፍ በዐለቱ ስንጥቅ ውስጥ አደርግሃለሁ፤ በዚያም እስከማልፍ ድረስ በእጄ እጋርድሃለሁ፤
በሌሊት የተቀደሰ በዓል ስታከብሩ እንደምትዘምሩ፣ ትዘምራላችሁ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ እስራኤል ዐለት፣ ሰዎች ዋሽንት እየነፉ በደስታ እንደሚወጡ፣ የእናንተም ልብ እንዲሁ ሐሤት ያደርጋል።
በልዑል መጠጊያ የሚኖር፣ በሁሉን ቻይ አምላክ ጥላ ሥር ያድራል።
ክፉ ነገር አያገኝህም፤ መቅሠፍትም ወደ ድንኳንህ አይገባም፤
በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ፣ እግርህም ከድንጋይ ጋራ እንዳይሰናከል፤
በእጆቻቸው ያነሡህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል።
በአንበሳና በእፉኝት ላይ ትጫማለህ፤ ደቦሉን አንበሳና ዘንዶውን ትረግጣለህ።
“ወድዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን ዐውቋልና እከልለዋለሁ።
ይጠራኛል፤ እመልስለታለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ፤ አከብረዋለሁ።
ረዥም ዕድሜን አጠግበዋለሁ፤ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።”
እግዚአብሔርን፣ “መጠጊያዬ፣ ምሽጌ፣ የምታመንብህ አምላኬ” እለዋለሁ።
“እንግዲህ ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል፣ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራን ብልኅ ሰው ይመስላል።
ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያን ቤት መታው፤ በዐለትም ላይ ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።
“እናንተ ጽድቅን የምትከታተሉ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልጉ ስሙኝ፤ ተቈርጣችሁ የወጣችሁበትን ዐለት፣ ተቈፍራችሁ የወጣችሁባትንም ጕድጓድ ተመልከቱ።
በሰው ዘንድ ወደ ተናቀው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠውና ክቡር ወደ ሆነው ወደዚህ ሕያው ድንጋይ እየቀረባችሁ፣
እናንተ ደግሞ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት ታቀርቡ ዘንድ፣ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ትሠራላችሁ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን መጠጊያ አደረግሁ፤ ከቶም አልፈር።
ጠላቶቼ ተነጋግረውብኛልና፣ ሕይወቴን ለማጥፋት የሚሹ በአንድ ላይ አሢረዋል፤
እነርሱም፣ “እግዚአብሔር ትቶታል፤ የሚያስጥለው የለምና፣ ተከታትላችሁ ያዙት” አሉ።
አምላክ ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ፤ አምላኬ ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን።
ባላንጣ የሆኑብኝ ይፈሩ፤ ይጥፉም፤ ሊጐዱኝ የሚፈልጉ፣ ንቀትንና ውርደትን ይከናነቡ።
እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በምስጋና ላይ ምስጋና አቀርብልሃለሁ።
አንደበቴ ስለ ጽድቅህ፣ ቀኑን ሙሉ ስለ ማዳንህ ይናገራል፤ ማቆሚያ ልኩንም አላውቅም።
መጥቼ የጌታ እግዚአብሔርን ብርቱ ሥራ ዐውጃለሁ፤ የአንተን ጽድቅ ብቻ እናገራለሁ።
አምላክ ሆይ፤ አንተ ከልጅነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እኔም እስከ ዛሬ ድረስ ድንቅ ሥራህን ዐውጃለሁ።
አምላክ ሆይ፤ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ፤ ክንድህን ለመጪው ትውልድ፣ ኀይልህን ኋላ ለሚነሣ ሕዝብ ሁሉ፣ እስከምገልጽ ድረስ።
አምላክ ሆይ፤ ጽድቅህ እስከ ሰማያት ይደርሳል፤ አንተ ታላላቅ ነገሮችን አድርገሃል፤ አምላክ ሆይ፤ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?
በጽድቅህም ታደገኝ፤ አስጥለኝም፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ አድነኝም።
ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ የተፈተነ ድንጋይ፣ የመሠረት ድንጋይ፣ ለጽኑ መሠረት የሚሆን የከበረ የማእዘን ድንጋይ፣ በጽዮን አኖራለሁ፤ በርሱም የሚያምን አያፍርም።
የጻድቃን ድነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ በመከራ ጊዜም መጠጊያቸው እርሱ ነው።
በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።
እግዚአብሔር ይረዳቸዋል፤ ይታደጋቸዋልም፤ ከክፉዎች እጅ ነጥቆ ያወጣቸዋል፤ እርሱን መጠጊያ አድርገዋልና ያድናቸዋል።
በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።
“እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ።
ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤
“ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ።
ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”
ለድኻ መጠጊያ፣ በጭንቅ ጊዜ ለችግረኛ መጠለያ፣ ከማዕበል መሸሸጊያ፣ ከፀሓይ ትኵሳትም ጥላ ሆነሃል። የጨካኞች እስትንፋስ፣ ከግድግዳ ጋራ እንደሚላጋ ማዕበል ነውና፤
እግዚአብሔር አንድ ነገር ተናገረ፤ እኔም ይህን ሁለት ጊዜ ሰማሁ፤ ኀይል የእግዚአብሔር ነው።
ጌታ ሆይ፤ ምሕረትም የአንተ ነው፤ አንተ ለእያንዳንዱ፣ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ።
በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋራ ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቁ።
ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።
“ወድዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን ዐውቋልና እከልለዋለሁ።
ይጠራኛል፤ እመልስለታለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ፤ አከብረዋለሁ።
ረዥም ዕድሜን አጠግበዋለሁ፤ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።”
ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል። ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው።
ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማነው?
ስለ እግዚአብሔር ምሕረት ለዘላለም እዘምራለሁ፤ በአፌም ታማኝነትህን ከትውልድ እስከ ትውልድ እገልጻለሁ።
አንተ ረዓብን የተሰየፈ ያህል አደቀቅኸው፤ በብርቱ ክንድህም ጠላቶችህን በተንሃቸው።
ሰማያት የአንተ ናቸው፤ ምድርም የአንተ ናት፤ ዓለምንና በውስጧ ያለውን ሁሉ አንተ መሠረትህ።
ሰሜንንና ደቡብን የፈጠርህ አንተ ነህ፤ ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ሐሤት ያደርጋሉ።
አንተ ክንደ ብርቱ ነህ፤ እጅህ ኀያል ናት፤ ቀኝ እጅህም ከፍ ከፍ ያለች ናት።
ጽድቅና ፍትሕ የዙፋንህ መሠረቶች ናቸው፤ ምሕረትና ታማኝነት በፊትህ ይሄዳሉ።
ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እልልታን የሚያውቅ፣ በፊትህም ብርሃን የሚሄድ ሕዝብ፤
ቀኑን ሙሉ በስምህ ደስ ይላቸዋል፤ በጽድቅህም ሐሤት ያደርጋሉ፤
አንተ የብርታታቸው ክብር ነህና፤ በሞገስህም ቀንዳችንን ከፍ ከፍ አደረግህ።
ጋሻችን የእግዚአብሔር ነውና፤ ንጉሣችንም የራሱ የእስራኤል ቅዱስ ነው።
በዚያ ጊዜ በራእይ ተናገርህ፤ ታማኝ ሕዝብህንም እንዲህ አልህ፤ “ኀያሉን ሰው ሥልጣን አጐናጸፍሁት፤ ከሕዝብ መካከል የተመረጠውንም ከፍ ከፍ አደረግሁት።
ምሕረትህን ለዘላለም እንደምትመሠርት፣ ታማኝነትህንም በሰማይ እንደምታጸና እናገራለሁ።
ምክንያቱም በመጽሐፍ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “እነሆ፤ የተመረጠና የከበረ የማእዘን ድንጋይ፣ በጽዮን አኖራለሁ፤ በርሱም የሚያምን ፈጽሞ አያፍርም።”
ከዚህ የተነሣ እናንተ ከቅዱሳን ጋራ የአንድ አገር ዜጋ፣ የእግዚአብሔርም ቤተ ሰብ አባል ናችሁ እንጂ፣ ከእንግዲህ ወዲህ መጻተኞችና እንግዶች አይደላችሁም።
በዚህም፣ የዓለምን ክፉ መንገድ ተከትላችሁ፣ በአየር ላይ ላሉት መንፈሳውያን ኀይላት ገዥ ለሆነውና አሁንም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙት ሰዎች ላይ ለሚሠራው መንፈስ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር።
በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑ ራስ ድንጋይም ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ ነው፤
በአንተ ላይ ታምናለችና፣ በአንተ የምትደገፈውን ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።
በእግዚአብሔር ለዘላለም ታመኑ፤ ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም ዐለት ነውና።
ብፁዕ ነው፤ ረዳቱ የያዕቆብ አምላክ የሆነ፣ ተስፋውንም በአምላኩ በእግዚአብሔር ላይ የጣለ ሰው፤
እርሱ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ የፈጠረ፣ ታማኝነቱም ለዘላለም የሆነ ነው፤
እርሱም መቅደስ ይሆናል፤ ለሁለቱ የእስራኤል ቤት ግን የሚያደናቅፍ ድንጋይ፣ የሚጥልም ዐለት ይሆንባቸዋል፤ ለኢየሩሳሌም ሕዝብም ወጥመድና አሽክላ ይሆናል።
ሰዎቹ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ነፍሳቸው ተመራ ሊወግሩት ስለ ተመካከሩ ዳዊት በጣም ተጨነቀ፤ ነገር ግን ዳዊት በአምላኩ በእግዚአብሔር በረታ።
የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።
እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር በተቀበልነው መጽናናት፣ በመከራ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል፣ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።
ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርጋለች፤ እርሱ ረዳታችንና ጋሻችን ነው።
ልባችን በርሱ ደስ ይለዋል፤ በቅዱስ ስሙ ታምነናልና።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ተስፋ ባደረግንህ፣ በእኛ ላይ ምሕረትህ ትሁን።
ፍርሀት በሚይዘኝ ጊዜ፣ መታመኔን በአንተ ላይ አደርጋለሁ።
ቃሉን በማመሰግነው አምላክ፣ በእግዚአብሔር ታምኛለሁ፤ አልፈራም፤ ሥጋ ለባሽ ምን ሊያደርገኝ ይችላል?
ሃሌ ሉያ። ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ።
እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ ጽዮን ሆይ፤ አምላክሽ ለትውልድ ሁሉ ንጉሥ ነው። ሃሌ ሉያ።
በምኖርበት ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ በሕይወትም እስካለሁ ለአምላኬ እዘምራለሁ።
ኮሬብ አጠገብ ባለው ዐለት በዚያ እኔ በአንተ ፊት እቆማለሁ። ዐለቱን ምታው፤ ከርሱም ሕዝቡ የሚጠጡት ውሃ ይወጣል።” ስለዚህ ሙሴ በእስራኤል አለቆች ፊት ይህንኑ አደረገ።
በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው።
ዐውሎ ነፋሱን ጸጥ አደረገ፤ የባሕሩም ሞገድ ረጭ አለ።
ከምሥራቅና ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ፣ ከየአገሩ የሰበሰባቸው እንዲህ ይናገሩ።
ጸጥ በማለቱም ደስ አላቸው፤ ወዳሰቡትም ወደብ አደረሳቸው።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴን ስማ፤ ጸሎቴንም አድምጥ።
ልቤ በዛለ ጊዜ፣ ከምድር ዳርቻ ወደ አንተ እጣራለሁ፤ ከእኔ ይልቅ ከፍ ወዳለው ዐለት ምራኝ።