እግዚአብሔር ሆይ፤ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰው ኰረብታህስ ማን መኖር ይችላል?
አካሄዱ የቀና፣ ጽድቅን የሚያደርግ፤ ከልቡ እውነትን የሚናገር፤
የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፤ አንተ ግን ከዚህ ሁሉ ሽሽ፤ ጽድቅን፣ እውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወትን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ትዕግሥትንና ገርነትን ተከታተል።
በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ።
መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
በጽድቅ የሚራመድ፣ ቅን ነገር የሚናገር፣ በሽንገላ የሚገኝን ትርፍ የሚንቅ፣ መማለጃን ላለመቀበል እጁን የሚሰበስብ፣ የግድያን ሤራ ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን፣ ክፋትን ላለማየት ዐይኑን የሚጨፍን፣
ይህ ሰው በከፍታ ላይ ይኖራል፤ የተራራም ምሽግ መጠጊያው ይሆናል፤ እንጀራ ይሰጠዋል፣ ውሃውም አይቋረጥበትም።
እግዚአብሔር አምላክ ፀሓይና ጋሻ ነውና፤ እግዚአብሔር ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ያለ ነቀፋ የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም።
ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።
ፍቅርና ታማኝነት ከቶ አይለዩህ፤ በዐንገትህ ዙሪያ እሰራቸው፤ በልብህም ጽላት ላይ ጻፋቸው።
ምንም ጕዳት ሳያደርስብህ፣ ያለ ምክንያት ሰውን አትክሰስ።
በክፉ ሰው አትቅና፤ የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ።
እግዚአብሔር ጠማማን ሁሉ ይጸየፋልና፤ ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል።
የእግዚአብሔር ርግማን በክፉዎች ቤት ላይ ነው፤ የጻድቃንን ቤት ግን ይባርካል።
እርሱ በዕቡያን ፌዘኞች ላይ ያፌዛል፤ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል።
ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ ሞኞችን ግን ለውርደት ያጋልጣቸዋል።
በዚያ ጊዜ ሞገስንና ማስተዋልን፣ በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ታገኛለህ።
እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ፤
እንዲሁም ጌታን ደስ የሚያሠኘውን ፈልጉ።
ፍሬ ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋራ ምንም ዐይነት ግንኙነት አይኑራችሁ፤ ይልቁን ግለጡት፤
በድብቅ የሚሠሩትን ነገር መናገር ራሱ አሳፋሪ ነውና።
ብርሃን የበራበት ነገር ሁሉ ግልጽ ሆኖ ይታያል፤
ምክንያቱም ሁሉን ነገር እንዲታይ የሚያደርገው ብርሃን ነውና፤ ስለዚህም፣ “አንተ የተኛህ ንቃ፤ ከሙታን ተነሣ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሏል።
እንግዲህ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ።
ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ።
ስለዚህ ሞኞች አትሁኑ፤ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ።
በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና።
በመዝሙርና በውዳሴ፣ በመንፈሳዊም ዝማሬ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በልባችሁ ለጌታ ተቀኙ፤ አዚሙም።
ክርስቶስ እንደ ወደደን ራሱንም ስለ እኛ መልካም መዐዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ተመላለሱ።
ከክፉ ራቅ፤ መልካሙንም አድርግ፣ ለዘላለምም ትኖራለህ።
እግዚአብሔር ፍትሕን ይወድዳልና፣ ታማኞቹንም አይጥልም። ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል፤ የኀጢአተኛው ዘር ግን ይጠፋል።
ይህም ጸጋ በኀጢአት መኖርንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን፣ በአሁኑ ዘመን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ፣ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት እንድንኖር ያስተምረናል፤
ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?
ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው።
ቀድሞ ስለ ነበራችሁበት ሕይወትም፣ በሚያታልል ምኞቱ የጐደፈውን አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል፤
ደግሞም በአእምሯችሁ መንፈስ እንድትታደሱ፣
እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው።
በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፤ ነፍሴ በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች፤ ሙሽራ ራሱን እንደሚያሳምር፣ ሙሽራዪቱም በዕንቈቿ እንደምታጌጥ፣ የድነትን ልብስ አልብሶኛል፤ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል።
በቀን እንደምንመላለስ በአግባብ እንመላለስ። በጭፈራና በስካር አይሁን፤ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤ በክርክርና በቅናትም አይሁን።
ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም ይፈጽም ዘንድ ለሥጋ በዐሳባችሁ አትመቻቹለት።
ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤
ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።
ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ እኛም በብርሃን ብንመላለስ፣ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል።
ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ። እንደ ብርሃን ልጆች ኑሩ፤
የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ሁሉ ዘንድ ነውና።
ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው።
ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤
የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፤ ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።
በዚህም ምክንያት በሙሉ ትጋት በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ለመጨመር ጣሩ፤ በበጎነት ላይ ዕውቀትን፣
በዕውቀት ላይ ራስን መግዛት፣ ራስን በመግዛት ላይ መጽናትን፣ በመጽናት ላይ እውነተኛ መንፈሳዊነትን፣
በእውነተኛ መንፈሳዊነት ላይ ወንድማዊ መተሳሰብን፣ በወንድማዊ መተሳሰብ ላይ ፍቅርን ጨምሩ።
ታጠቡ፤ ራሳችሁንም አንጹ፤ ክፉ ሥራችሁን ከፊቴ አርቁ፤ ክፉ ማድረጋችሁን ተዉ፤
መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን እሹ፣ የተገፉትን አጽናኑ፤ አባት ለሌላቸው ቁሙላቸው፤ ለመበለቶችም ተሟገቱ።
የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣
ደግሞም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሠኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት።
“ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ ባሪያ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።
በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳትና ከዓለም ርኩሰት ራስን መጠበቅ ነው።
እግዚአብሔር “ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል”።
በጎ የሆነውን ጸንቶ በማድረግ ክብርን፣ ሞገስንና ዘላለማዊነትን ለሚሹ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል።
ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንድንመላለስባቸው ያዘጋጀልንን መልካም የሆኑትን ሥራዎች እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።
መልካም ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ካከማቸው ክፉ ነገር ክፉውን ያወጣል፤ ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራልና።
እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት።
ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።
ንጹሕ እጅና ቅን ልብ ያለው፤ ነፍሱን ለሐሰት ነገር የማያስገዛ፤ በውሸት የማይምል።
እርሱ በረከትን ከእግዚአብሔር ዘንድ፣ ጽድቅንም ከአዳኝ አምላኩ ይቀበላል።
የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፤ በዚያ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
የእስራኤል ሕዝብ፣ “ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበል።
ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት፤ ጻድቃን በርሷ በኩል ይገባሉ።