መዝሙር 111:10እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ትእዛዙንም የሚፈጽሙ ጥሩ ማስተዋል አላቸው፤ ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።
ምሳሌ 1:7እግዚአብሔርን መፍራት የዕውቀት መጀመሪያ ነው፤ ቂሎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።
መዝሙር 89:7እግዚአብሔር በቅዱሳን ጉባኤ መካከል በጣም የሚፈራ፣ በዙሪያውም ካሉት ሁሉ በላይ እጅግ የሚከበር ነው።
ዕብራውያን 12:28-29ስለዚህ ከቶ የማይናወጥ መንግሥት ስለምንቀበል እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደግሞም ደስ በሚያሠኘው መንገድ በአክብሮትና በፍርሀት እናምልከው፤“አምላካችን የሚባላ እሳት ነውና።”
መዝሙር 96:9በተቀደሰ ውበት ለእግዚአብሔር ስገዱ፤ ምድር ሁሉ፤ በፊቱ ተንቀጥቀጡ።
ምሳሌ 3:7በራስህ አስተያየት ጠቢብ ነኝ አትበል፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ከክፉም ራቅ።
መክብብ 12:13እነሆ፤ ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፣ የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤ አምላክን ፍራ፤ ትእዛዞቹንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።
ኢሳይያስ 8:13የምትቀድሱት እርሱ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ የምትፈሩት እርሱ ይሁን፤ የምትንቀጠቀጡለትም እርሱ ይሁን።
መዝሙር 34:9እናንተ ቅዱሳኑ፤ እግዚአብሔርን ፍሩት፤ እርሱን የሚፈሩት አንዳች አያጡምና።
ምሳሌ 14:27እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ሰውን ከሞት ወጥመድ ያድነዋል።
ዘዳግም 10:12-13አሁንም እስራኤል ሆይ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወድደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣መልካም እንዲሆንልህና ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞችና የእግዚአብሔር ሥርዐቶች እንድትጠብቅ አይደለምን?
መዝሙር 25:14እግዚአብሔር ምስጢሩን ከሚፈሩት ወዳጆቹ አይሰውርም፤ ኪዳኑንም ይገልጥላቸዋል።
ሮሜ 12:1እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው።
ዘፀአት 20:20ሙሴም ለሕዝቡ፣ “አትፍሩ፤ ኀጢአት እንዳትሠሩ የእግዚአብሔር ፍርሀት ከእናንተ ጋራ ይሆን ዘንድ፣ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ መጥቷል” አላቸው።
ሉቃስ 1:50ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።
ዘዳግም 10:12አሁንም እስራኤል ሆይ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወድደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣
ፊልጵስዩስ 2:10-11ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።
ምሳሌ 19:23እግዚአብሔርን መፍራት ወደ ሕይወት ይመራል፤ እንዲህ ያለውም ሰው እፎይ ብሎ ያርፋል፤ መከራም አያገኘውም።
1 ጴጥሮስ 2:17ለሰው ሁሉ ተገቢውን አክብሮት ስጡ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ።
መዝሙር 2:11እግዚአብሔርን በፍርሀት አገልግሉት፤ ለርሱ በመንቀጥቀጥ ደስ ያሰኛችሁ።
ምሳሌ 15:33እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብን መማር ነው፤ ትሕትናም ክብርን ትቀድማለች።
ኢሳይያስ 66:2እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጄ አልሠራችምን? እንዲገኙስ ያደረግሁ እኔ አይደለሁምን?” ይላል እግዚአብሔር። “ነገር ግን እኔ ወደዚህ፣ ትሑት ወደ ሆነና መንፈሱ ወደ ተሰበረ፣ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።
ቈላስይስ 3:23-24የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት፤ከጌታ ዘንድ እንደ ብድራት የምትቀበሉት ርስት እንዳለ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው።
መዝሙር 5:7እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ አንተንም በመፍራት፣ ወደ ተቀደሰው መቅደስህ እሰግዳለሁ።
መዝሙር 103:17የእግዚአብሔር ምሕረት ግን፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፤ ጽድቁም እስከ ልጅ ልጅ ድረስ በላያቸው ይሆናል፤
መዝሙር 115:11እናንተ እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፤ በእግዚአብሔር ታመኑ፤ ረዳታቸውና ጋሻቸው እርሱ ነው።
ኢዮብ 28:28ከዚያም ሰውን፣ ‘እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከክፋትም መራቅ ማስተዋል ነው’ አለው።”
ሕዝቅኤል 20:41ከሕዝቦች መካከል ባወጣኋችሁ ጊዜ፣ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች በሰበሰብኋችሁ ጊዜ፣ መልካም መዐዛ እንዳለው ዕጣን እቀበላችኋለሁ፤ በእናንተም መካከል ቅዱስ መሆኔን በአሕዛብ ፊት እገልጣለሁ።
ማቴዎስ 5:16እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ።
ምሳሌ 8:13እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን መጥላት ነው፤ እኔም ትዕቢትንና እብሪትን፣ ክፉ ጠባይንና ጠማማ ንግግርን እጠላለሁ።
ያዕቆብ 4:10በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፣ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።
መዝሙር 147:10-11እርሱ በፈረስ ኀይል አይደሰትም፤ በሯጭም ብርታት ላይ ደስታውን አያደርግም።ነገር ግን እግዚአብሔር በሚፈሩት፣ በምሕረቱ በሚታመኑትም ይደሰታል።
ምሳሌ 10:27እግዚአብሔርን መፍራት ዕድሜን ያረዝማል፤ የክፉዎች ዕድሜ ግን በዐጭር ይቀጫል።
መዝሙር 111:1ሃሌ ሉያ። በቅኖች ሸንጎ፣ በጉባኤም መካከል፣ ለእግዚአብሔር በፍጹም ልቤ ምስጋና አቀርባለሁ።
ኢሳይያስ 33:6እርሱ ለዘመንህ የሚያስተማምን መሠረት፣ የድነት፣ የዕውቀትና የጥበብ መዝገብ ይሆናል፤ እግዚአብሔርንም መፍራት የዚህ ሀብት ቍልፍ ነው።
ምሳሌ 14:2አካሄዱ ቅን የሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱ ጠማማ የሆነ ግን ይንቀዋል።
ዘዳግም 5:29ታዲያ ለእነርሱም ሆነ ለልጆቻቸው ለዘላለም መልካም እንዲሆንላቸው፣ እኔን እንዲፈሩና ሁልጊዜ ትእዛዞቼን ሁሉ እንዲጠብቁ እንደዚህ ያለ ልብ ቢኖራቸው ምናለ!
መዝሙር 4:4ስትቈጡ ኀጢአት አትሥሩ፤ በዐልጋችሁም ላይ ሳላችሁ፣ ልባችሁን መርምሩ፤ ጸጥም በሉ። ሴላ
መክብብ 5:7ብዙ ሕልምና ብዙ ቃል ከንቱ ነው፤ ስለዚህ አምላክን ፍራ።
ሮሜ 14:11እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ “ ‘እኔ ሕያው ነኝና’ ይላል ጌታ፤ ‘ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር ይመሰክራል።’ ”
መዝሙር 86:11እግዚአብሔር ሆይ፤ መንገድህን አስተምረኝ፤ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን እፈራ ዘንድ፣ ያልተከፋፈለ ልብ ስጠኝ።
ኢሳይያስ 57:15ከፍ ከፍ ያለውና ልዕልና ያለው እርሱ፣ ስሙም ቅዱስ የሆነው፣ ለዘላለም የሚኖረው እንዲህ ይላል፤ “የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት፣ ከፍ ባለውና በቅዱሱ ስፍራ እኖራለሁ፤ የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋራ እሆናለሁ።
መዝሙር 112:1ሃሌ ሉያ። ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ በትእዛዙም እጅግ ደስ የሚሰኝ፤
መዝሙር 111:9ለሕዝቡ መዳንን ሰደደ፤ ኪዳኑንም ለዘላለም አዘዘ፤ ስሙም የተቀደሰና የተፈራ ነው።
መዝሙር 34:7እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም።
መዝሙር 33:8ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን ትፍራው፤ በዓለም የሚኖር ሕዝብ ሁሉ በፊቱ ይንቀጥቀጥ።
ኢሳይያስ 11:3እግዚአብሔርን በመፍራት ደስ ይለዋል። ዐይኑ እንዳየ አይፈርድም፤ ጆሮውም እንደ ሰማ አይበይንም።
ማቴዎስ 10:28ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን ፍሩ።
1 ጴጥሮስ 1:17ለሰው ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደየሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ፣ በዚህ ምድር በእንግድነት ስትኖሩ በፍርሀት ኑሩ።
ምሳሌ 9:10“የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው።
መዝሙር 30:4እናንተ የምትታመኑት፤ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ቅዱስ ስሙንም አወድሱ።
ኢሳይያስ 50:10ከእናንተ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ የባሪያውንም ቃል የሚሰማ ማን ነው? ያ ሰው በጨለማ የሚሄድ ከሆነና፣ ብርሃንም ከሌለው፣ በእግዚአብሔር ስም ይታመን፤ በአምላኩም ይደገፍ።
ሮሜ 6:13ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።
ምሳሌ 1:29ዕውቀትን ስለ ጠሉ፣ እግዚአብሔርንም መፍራት ስላልመረጡ፣
መዝሙር 139:23-24እግዚአብሔር ሆይ፤ መርምረኝ፤ ልቤንም ዕወቅ፤ ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ፤የክፋት መንገድ በውስጤ ቢኖር እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ።
1 ዜና መዋዕል 16:29ለስሙ የሚገባውን ክብር ለእግዚአብሔር ስጡ፤ መባ ይዛችሁ በፊቱ ቅረቡ፤ በቅድስናውም ክብር ለእግዚአብሔር ስገዱ።
መዝሙር 22:23እናንተ እግዚአብሔርን የምትፈሩ፤ አወድሱት፤ እናንተ የያዕቆብ ዘር ሁላችሁ፤ አክብሩት፤ የእስራኤልም ዘር ሁላችሁ፤ እርሱን ፍሩት።
ሮሜ 12:2መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
መዝሙር 130:4ነገር ግን በአንተ ዘንድ ይቅርታ አለ፤ ስለዚህም ልትፈራ ይገባሃል።
መዝሙር 33:18እነሆ፤ የእግዚአብሔር ዐይኖች በሚፈሩት ላይ ናቸው፤ ምሕረቱንም በሚጠባበቁት ላይ አትኵረዋል።
ማቴዎስ 6:9“እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ “ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤
መዝሙር 76:7መፈራት ያለብህ አንተ ብቻ ነህ፤ በተቈጣህ ጊዜ ማን በፊትህ መቆም ይችላል?
ሮሜ 11:20ትክክል ነው፤ እነርሱ የተሰበሩት ካለማመን የተነሣ ነው፤ አንተም በእምነት ቆመሃል፤ ፍራ እንጂ ትዕቢተኛ አትሁን።
መዝሙር 101:3በዐይኔ ፊት፣ ምናምንቴ ነገር አላኖርም። የከሓዲዎችን ሥራ እጠላለሁ፤ ከእኔም ጋራ አይጣበቅም።
መዝሙር 118:1እግዚአብሔር ቸር ነውና አመስግኑ፤ ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
መዝሙር 149:5ቅዱሳን በዚህ ክብር ይጓደዱ፤ በመኝታቸውም ላይ እልል እያሉ ይዘምሩ።
መዝሙር 104:31የእግዚአብሔር ክብር ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤ እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይበለው፤
ምሳሌ 3:12አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወድደውን ይገሥጻልና።
ኢሳይያስ 40:30-31ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ይታክታሉም፤ ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ።እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።
መዝሙር 112:7ክፉ ወሬ አያሸብረውም፤ ልቡ እግዚአብሔርን በመተማመን የጸና ነው።
ምሳሌ 14:26እግዚአብሔርን የሚፈራ ጽኑ ዐምባ አለው፤ ልጆቹም መጠጊያ ይኖራቸዋል።
መዝሙር 27:4እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።
1 ሳሙኤል 12:14እግዚአብሔርን የምትፈሩና የምታመልኩ፣ የምትታዘዙትና በትእዛዞቹ ላይ የማታምፁ ከሆነ፣ እንዲሁም እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ከተከተላችሁ መልካም ይሆንላችኋል።
መዝሙር 130:7በእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፣ በርሱም ዘንድ ማዳን አለና፣ እስራኤል ሆይ፤ በእግዚአብሔር ተስፋ አድርግ።
ሮሜ 3:18“በዐይናቸው ፊት ፈሪሀ እግዚአብሔር የለም።”
ኢሳይያስ 51:12“የማጽናናችሁ እኔ፣ እኔው ብቻ ነኝ፤ ሟች የሆኑትን ሰዎች፣ እንደ ሣር የሚጠወልጉትን የሰው ልጆች ለምን ትፈራለህ?
መዝሙር 149:1ሃሌ ሉያ። ለእግዚአብሔር አዲስ ቅኔ ተቀኙ፤ ምስጋናውንም በቅዱሳን ጉባኤ ዘምሩ።