ልቤ ሆይ፥ በምሳሌ መጽሐፍ እንደተጻፈው፥ ሕይወት የሚመነጨው ከአንተ ነውና ላንተ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብኝ አውቃለሁ። ልብ አታላይ መሆኑንም መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፤ ስለዚህ በራሴ ምኞትና ስሜት እንዳልገዛ ፈቃዴን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ማስገዛት ይገባኛል።
በእውነት መኖርና እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንድችል የመንፈስ ቅዱስን መሪነት መፈለግ አለብኝ። እግዚአብሔር ልባችንን ማደሪያው ሊያደርገው ይፈልጋል፤ ነገር ግን በሁከትና በዓመፀኝነት ውስጥ እንዳይኖር፥ በትሕትና ለሚፈልጉትና መገኘቱን ለሚናፍቁ ሰዎች እንደሚያድር ማስታወስ አለብኝ።
በየማለዳው በእግዚአብሔር ቃል መሞላት አለብኝ፤ ይህም ቃሌ እርግማን ሳይሆን በረከት እንዲሆን ያደርገዋል። ዋጋ ያለው ነገር በውጫዊ መልካችን ሳይሆን በውስጣችን ባለው ነው። ስለዚህ በሁሉም ነገር ቅን መሆን ይጠበቅብኛል። ልባቸው ንጹሕ የሆኑ እግዚአብሔርን ያያሉና የተባረኩ ናቸው። ሃሌሉያ!
እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፣ “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው።
መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
መልካም ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ካከማቸው ክፉ ነገር ክፉውን ያወጣል፤ ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራልና።
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣
ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም።
ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤
ሳኦልንም ከሻረው በኋላ፣ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ እግዚአብሔርም ስለ እርሱ፣ ‘እንደ ልቤ የሆነና እኔ የምሻውን ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ሲል መሰከረለት።
ሰውየውም መልሶ፣ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል” አለው።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፤ በከንፈሩም ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ የሚያመልከኝም፣ ሰው ባስተማረው ሰው ሠራሽ ሥርዐት ነው።
እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹም ልባቸውም ወደ እኔ ስለሚመለሱ፣ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።