Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ምሳሌ 27 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 ነገ በሚሆነው አትመካ፤ ቀን የሚያመጣውን አታውቅምና።

2 ሌላው ያመስግንህ እንጂ የገዛ አፍህ አይደለም፤ ሌላ ሰው ያወድስህ እንጂ የገዛ ከንፈርህ አይሁን።

3 ድንጋይ ይከብዳል፤ አሸዋም ሸክም ነው፤ የቂል ሰው ቍጣ ግን ከሁለቱም ይከብዳል።

4 ንዴት ጨካኝ፣ ቍጣም ጐርፍ ነው፤ በቅናት ፊት ግን ማን መቆም ይችላል?

5 የተገለጠ ዘለፋ፣ ከተደበቀ ፍቅር ይሻላል።

6 ከጠላት ደጋግሞ መሳም ይልቅ፣ የወዳጅ ማቍሰል ይታመናል።

7 ለጠገበ ማር አይጥመውም፤ ለተራበ ግን እሬት እንኳ ይጣፍጠዋል።

8 ከቤቱ ወጥቶ የሚባዝን ሰው፣ ጐጆዋን ለቅቃ እንደምትባዝን ወፍ ነው።

9 ሽቱና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ የወዳጅ ማስደሰትም ከቅን ምክሩ ይመነጫል።

10 የራስህንም ሆነ የአባትህን ወዳጅ አትተው፤ መከራ በሚያጋጥምህ ጊዜ ወደ ወንድምህ ቤት አትሂድ፤ ሩቅ ካለ ወንድም ቅርብ ያለ ጎረቤት ይሻላል።

11 ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሠኘው፤ ለሚንቁኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችል ዘንድ።

12 አስተዋይ ክፉን አይቶ ራሱን ይሸሽጋል፤ አላዋቂዎች ግን በዚያው ይቀጥላሉ፤ ይቀጡበታልም።

13 ለማይታወቅ ሰው ዋስ የሆነውን ልብሱን ግፈፈው፤ ለባዕድ ሴት የተዋሰውን በቃሉ ዐግተው።

14 ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ ባልንጀራውን በማለዳ ቢመርቅ፣ እንደ ርግማን ይቈጠራል።

15 ጨቅጫቃ ሚስት፣ በዝናብ ቀን እንደሚወርድ የማያቋርጥ ጠፈጠፍ ናት፤

16 እርሷን ለመግታት መሞከር፣ ነፋስን እንደ መግታት ወይም ዘይትን በእጅ እንደ መጨበጥ ነው።

17 ብረት ብረትን እንደሚስል፣ ሰውም ሌላውን ሰው እንደዚሁ ይስለዋል።

18 በለስን የሚንከባከብ ፍሬዋን ይበላል፤ ጌታውን የሚያገለግልም ክብርን ይጐናጸፋል።

19 ውሃ ፊትን እንደሚያሳይ፣ የሰውም ልብ ማንነቱን ገልጾ ያሳያል።

20 ሲኦልና የሙታን ዓለም እንደማይጠግቡ ሁሉ፣ የሰውም ዐይን አይረካም።

21 ብር በማቅለጫ፣ ወርቅም በከውር እንደሚፈተን፤ ሰውም በአንደበት ምስጋና ይፈተናል።

22 ቂልን በሙቀጫ ብትወቅጠው፣ እንደ እህልም በዘነዘና ብታደቅቀው፣ ቂልነቱን ልታስወግድለት አትችልም።

23 በጎችህ በምን ሁኔታ እንዳሉ ደኅና አድርገህ ዕወቅ፤ መንጋህንም ተንከባከብ፤

24 ሀብት ለዘላለም አይኖርምና፤ ዘውድም ከትውልድ ወደ ትውልድ ጸንቶ አይኖርም።

25 ደረቁ ሣር ተወግዶ፣ አዲሱ ብቅ ሲል፣ በየኰረብታው ላይ ያለው ሣር ተሰብስቦ ሲገባ፣

26 ከበግ ጠቦቶች ልብስ ታገኛለህ፤ ፍየሎችም የዕርሻ መሬት መግዣ ይሆኑሃል።

27 አንተንና ቤተ ሰብህን፣ ገረዶችህንም ጭምር ለመመገብ፣ የተትረፈረፈ የፍየል ወተት ይኖርሃል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች