1 ነገሥት 8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምታቦቱ ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ 8፥1-21 ተጓ ምብ – 2ዜና 5፥2–6፥11 1 ከዚያም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን እንዲያመጡ፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የእስራኤልን ነገድ አለቆችና የእስራኤልን ጐሣዎች ሹማምት ሁሉ፣ ንጉሡ ሰሎሞን ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 2 በዓሉ በሚከበርበት ኤታኒም በተባለው በሰባተኛው ወር፣ የእስራኤል ወንዶች ሁሉ ንጉሥ ሰሎሞን ወዳለበት ተሰበሰቡ። 3 የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በመጡ ጊዜ፣ ካህናቱ ታቦቱን አነሡ፤ 4 የእግዚአብሔርን ታቦት፣ የመገናኛውን ድንኳንና በውስጡ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አመጡ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ተሸከሟቸው። 5 ንጉሥ ሰሎሞንና ዐብሮት በዚያ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ጉባኤ በታቦቱ ፊት ስፍር ቍጥር የሌላቸውን በጎችና በሬዎች ሠዉ። 6 ከዚያም ካህናቱ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት አምጥተው የቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ አግብተው ከኪሩቤል ክንፍ በታች ባለው ስፍራው አኖሩት። 7 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ከታቦቱ በላይ ባለው ስፍራ ላይ ዘርግተው፣ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን ጋረዱ። 8 መሎጊያዎቹ በጣም ከመርዘማቸው የተነሣ ጫፎቻቸው ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ካለው ከቅድስት ይታዩ ነበር፤ ከቅድስት ወዲያ ላለ ሰው ግን አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያው ይገኛሉ። 9 እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ በኋላ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋራ ኪዳን ባደረገ ጊዜ፣ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በውስጡ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላት በቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም። 10 ካህናቱ ከቤተ መቅደሱ በወጡ ጊዜ፣ ደመና የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሞላው። 11 የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ስለ ነበር፣ ከደመናው የተነሣ ካህናቱ አገልግሎታቸውን ማከናወን አልቻሉም። 12 ከዚያም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል፤ 13 እነሆ፣ እኔም ለዘላለም የምትኖርበትን ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርቼልሃለሁ።” 14 መላው የእስራኤል ጉባኤ በዚያ ቆሞ ሳለ፣ ንጉሡ ፊቱን ወደ እነርሱ መልሶ ጉባኤውን ባረከ። 15 ከዚያም እንዲህ አለ፤ “ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ ተናግሮ የሰጠውን ተስፋ፣ እርሱ ራሱ በእጁ የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ እርሱም እንዲህ ብሎ ነበርና፤ 16 ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ዕለት አንሥቶ፣ ስሜ በዚያ እንዲጠራና ቤተ መቅደስ እንዲሠራበት ከመላው የእስራኤል ነገድ አንድም ከተማ አልመረጥሁም፤ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲመራ ግን ዳዊትን መረጥሁት።’ 17 “አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቡ ዐስቦ ነበር፤ 18 እግዚአብሔር ግን አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ ‘ለስሜ ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልብህ ማሰብህ መልካም አድርገሃል፤ 19 ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝ ከአብራክህ የሚከፈለው፣ የገዛ ልጅህ ነው።’ 20 “እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል ፈጽሟል፤ እኔም እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔርም ስም ቤተ መቅደስ ሠርቻለሁ። 21 ከግብጽ ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻችን ጋራ የገባው የእግዚአብሔር ኪዳን በውስጡ ላለበት ታቦት መኖሪያ ስፍራ በዚያ አዘጋጅቻለሁ።” ሰሎሞን በምረቃው ላይ ያቀረበው ጸሎት 8፥22-53 ተጓ ምብ – 2ዜና 6፥12-40 22 ከዚያም ሰሎሞን መላው የእስራኤል ጉባኤ ባለበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ፣ 23 እንዲህም አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልባቸው በመንገድህ ከሚሄዱት ባሪያዎችህ ጋራ የፍቅር ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ በላይ በሰማይም ሆነ በታች በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም፤ 24 ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ አጽንተሃል፤ በአፍህ የተናገርኸውን ዛሬም እንደ ሆነው በእጅህ ፈጸምኸው። 25 “አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት፣ ‘ልጆችህ አንተ እንደ አደረግኸው ሁሉ በሚያደርጉት ሁሉ በጥንቃቄ በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አታጣም’ ብለህ የሰጠኸውን ተስፋ አጽናለት። 26 እንግዲህ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም። 27 “ነገር ግን አምላክ በርግጥ በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማይ፣ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ እንኳ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ! 28 ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎትና ስለ ምሕረት ያቀረበውን ልመና አድምጥ፤ በዛሬው ዕለት ባሪያህ በፊትህ የሚያቀርበውን ጩኸትና ጸሎት ስማ። 29 ባሪያህ ወደዚህ ቦታ የሚያቀርበውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ፣ ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’ ወደ አልኸው በዚህ ስፍራ ወዳለው ቤተ መቅደስ ዐይኖችህ ሌትና ቀን የተከፈቱ ይሁኑ። 30 ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ ጸሎት በሚያቀርቡበት ጊዜ፣ ልመናቸውን ተቀበል፤ መኖሪያህ በሆነው በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል። 31 “አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድልና እንዲምል ቢጠየቅ፣ እርሱም መጥቶ በቤተ መቅደሱ በመሠዊያህ ፊት ቢምል፣ 32 ይህን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም፤ በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ፤ ለበደለኛው ስለ አድራጎቱ የእጁን ክፈል፤ ከበደል ነጻ ለሆነውም ንጽሕናውን ይፋ በማድረግ ይህንኑ አረጋግጥለት። 33 “ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ በጠላቶቻቸው ድል በሚሆኑበት ጊዜ፣ ወደ አንተም ተመልሰው ስምህን ቢጠሩ፣ በዚህም ቤተ መቅደስ ወደ አንተ ቢጸልዩና ልመናቸውን ቢያቀርቡ፣ 34 በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸውም ምድር መልሳቸው። 35 “አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ ሰማዩ ተዘግቶ ዝናብ ሳይዘንብ ቢቀር፣ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢጠሩ፣ ስላስጨነቅሃቸውም ከኀጢአታቸው ቢመለሱ፣ 36 በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የባሪያዎችህን የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ የሚሄዱበትን ቀናውን መንገድ አስተምራቸው፤ ርስት አድርገህ ለሕዝብህ በሰጠሃቸውም ምድርህ ላይ ዝናብን አዝንብ። 37 “በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር፣ ዋግ ወይም አረማሞ፣ አንበጣ ወይም ኵብኵባ በሚከሠትበት ጊዜ፣ ወይም ከተሞቻቸውን ጠላት በሚከብብበት ጊዜ፣ እንዲሁም ማንኛውም ዐይነት ጥፋት ወይም በሽታ በሚደርስባቸው ጊዜ፣ 38 ከሕዝብህ ማንኛውም ሰው ወይም መላው እስራኤል የልቡን ጭንቀት ዐውቆ እጆቹን ወደዚህ ቤት በመዘርጋት ማንኛውንም ጸሎትና ልመና በሚያቀርብበት ጊዜ ሁሉ፣ 39 በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ይቅር በል፤ አድርግም። የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ የምታውቅ አንተ ብቻ ስለ ሆንህ ልቡን ለምታውቀው ለእያንዳንዱ ሰው እንደ አካሄዱ ክፈለው፤ 40 ይኸውም እነርሱ ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ፣ አንተን እንዲፈሩህ ነው። 41 “ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ፣ ነገር ግን ከስምህ ታላቅነት የተነሣ ከሩቅ የመጣ ባዕድ ሰው ቢኖር፣ 42 ሰዎች ከሩቅ የመጣው ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ጠንካራዪቱ እጅህ፣ ስለ ተዘረጋችው ክንድህ ሰምቶ ነውና፤ እንግዳው መጥቶ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢጸልይ፣ 43 አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ገዛ ሕዝብህ እንደ እስራኤል፣ ስምህን በማወቅ እንዲፈሩህ፣ የሠራሁትም ይህ ቤት ስምህ የሚጠራበት ቤት መሆኑን እንዲያውቁ ባዕዱ ሰው የሚጠይቅህን ሁሉ አድርግ። 44 “ሕዝብህ ጠላታቸውን ለመውጋት አንተ ወደምትልካቸው ወደ የትኛውም ቦታ ለጦርነት በሚወጡበት ጊዜ፣ አንተ ወደ መረጥሃት ከተማና እኔ ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ወደ እግዚአብሔር ቢጸልዩ፣ 45 ጸሎትና ልመናቸውን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ፍትሕንም አጐናጽፋቸው። 46 “መቼም ኀጢአት የማይሠራ ሰው የለምና ሕዝብህ በአንተ ላይ ኀጢአት ቢሠሩ፣ አንተም ተቈጥተህ ለጠላቶቻቸው አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣ እነርሱም ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ የጠላት ምድር ቢጋዙ፣ 47 በተጋዙበት አገር ሳሉ ወደ ልቡናቸው ቢመለሱ፣ ንስሓ ቢገቡና በምርኮ ምድር ሳሉ፣ ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ ብለው ቢለምኑህ፣ 48 እንዲሁም ማርከው በወሰዷቸው ጠላቶቻቸው አገር፣ በምርኮ ምድር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፣ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር፣ ወደ መረጥሃትም ከተማና እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፣ 49 በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውንና፤ ልመናቸውን ስማ፤ ፍረድላቸውም። 50 በአንተ ላይ ስለ ሠሩት ኀጢአት፣ የበደሉህንም የሕዝብህን ኀጢአት ይቅር በል፤ የማረኳቸውም እንዲራሩላቸው አድርግ። 51 ከዚያች እንደ ብረት ማቅለጫ እቶን እሳት ከሆነችው፣ ከግብጽ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህም ርስትህም ናቸውና። 52 “አሁንም ዐይኖችህ ለባሪያህና ለሕዝብህ ለእስራኤል ልመና የተከፈቱ ይሁኑ፤ ወደ አንተ በሚጮኹበትም ጊዜ ሁሉ ስማቸው፤ 53 ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አባቶቻችንን ከግብጽ ባወጣህ ጊዜ፣ በባሪያህ በሙሴ አማካይነት እንደ ተናገርኸው ሁሉ፣ ርስትህ ይሆኑ ዘንድ ከምድር ሕዝቦች ሁሉ ለይተሃቸዋልና።” 54 ሰሎሞንም ይህን ሁሉ ጸሎትና ልመና ለእግዚአብሔር አቅርቦ ከፈጸመ በኋላ፣ እጆቹን ወደ ሰማይ በመዘርጋት፣ በጕልበቱ ተንበርክኮ ከነበረበት ከእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ተነሣ። 55 ከዚያም ቆሞ መላውን የእስራኤልን ጉባኤ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ ሲል መረቀ፤ 56 “በሰጠው ተስፋ መሠረት ለሕዝቡ ለእስራኤል ዕረፍትን ለሰጠ እግዚአብሔር ምስጋና ይግባው፤ በባሪያው በሙሴ አማካይነት ከተሰጠው መልካም ተስፋ ሁሉ አንድም ቃል አልቀረምና። 57 አምላካችን እግዚአብሔር ከአባቶቻችን ጋራ እንደ ነበረ ሁሉ ከእኛም ጋራ ይሁን፤ አይተወን፤ አይጣለንም። 58 በመንገዱም ሁሉ እንድንሄድ፣ ለአባቶቻችን የሰጣቸውን ትእዛዞች፣ ሥርዐቶችና ደንቦች እንድንጠብቅ ልባችንን ወደ እርሱ ይመልስ። 59 በየዕለቱም ባሪያውንና ሕዝቡን እስራኤልን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ እንዲረዳቸው፣ ይህች በእግዚአብሔር ፊት ያቀረብኋት የራሴ ልመና በቀንና በሌሊት ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፊት ትቅረብ። 60 ይኸውም የምድር ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደ ሆነና ከርሱ በቀር ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ነው። 61 ስለዚህ እንደ ዛሬው ዕለት ሁሉ፣ በሥርዐቱ እንድትኖሩና ትእዛዙን እንድትጠብቁ ልባችሁ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የተገዛ ይሁን።” የቤተ መቅደሱ መመረቅ 8፥62-66 ተጓ ምብ – 2ዜና 7፥1-10 62 ከዚያም ንጉሡና ከርሱ ጋራ ያሉት እስራኤል ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አቀረቡ። 63 ሰሎሞንም ሃያ ሁለት ሺሕ በሬ፣ መቶ ሃያ ሺሕ በግና ፍየል የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ንጉሡና እስራኤላውያንም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በዚህ ሁኔታ ቀደሱ። 64 በዚያ ዕለትም ንጉሡ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ያለውን የአደባባዩን መካከለኛ ክፍል ቀደሰ፤ በዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባንና የኅብረት መሥዋዕቱን ሥብ አቀረበ፤ ይህን ያደረገውም በእግዚአብሔር ፊት የነበረው የናስ መሠዊያ በጣም ትንሽ ከመሆኑ የተነሣ፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕት የእህሉን ቍርባንና የኅብረት መሥዋዕቱን ስብ መያዝ ባለመቻሉ ነበር። 65 በዚያ ጊዜም ሰሎሞን ዐብረውት ከነበሩት ከእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ጋራ፣ ማለትም ከሐማት መተላለፊያ እስከ ግብጽ ደረቅ ወንዝ ካለው ምድር ከተሰበሰበው ታላቅ ጉባኤ ጋራ በዓሉን አከበረ። እነርሱም ሰባት ቀን፣ በተጨማሪም ሌላ ሰባት ቀን በድምሩ ዐሥራ አራት ቀን በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት በዓሉን አከበሩ። 66 በስምንተኛው ቀን ሕዝቡን አሰናበተ፤ ሕዝቡም ንጉሡን መረቁ፤ እግዚአብሔር ለባሪያው ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ባደረገው በጎ ነገር ሁሉ ከልብ ተደስተው ሐሤት በማድረግ ወደ የቤታቸው ተመለሱ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.