1 መልአኩም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “ይህንስ ዓለም ልዑል ስለ ብዙዎች ፈጠረው፤ የሚመጣውን ግን ስለ ጥቂቶች ፈጠረው። 2 “ዕዝራ! እነሆ በፊትህ ምሳሌውን እተረጕምልሃለሁ፤ ምድርን ጠይቃት፤ ትነግርሃለችም፤ ከእርሱ ሸክላ የሚገኝበትን መሬት ታስገኛለችና፥ መሬትም ወርቅ ከእርሱ የሚገኝበትን ታስገኛለችና፥ ከወርቅ ይልቅ ሸክላ እጅግ ይበዛል። 3 የዚህ ዓለም ሥራም እንዲሁ ነው፤ በውስጡ የተፈጠሩ ብዙ ናቸው፤ የሚድኑ ግን ጥቂቶች ናቸውና።” 4 እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “ልብ ከጥበብ የተነሣ ደስ ይበላት፤ ጆሮም ነገርን ትጠጣ። 5 ጆሮ ለመስማት ተሠርትዋልና፥ ልብም ለማወቅ ተፈጥሯልና፥ ሰው ከጥቂት ሕይወት በቀር ሳይሰጠው ባልወደደው ይሄዳል። 6 አቤቱ ለባሪያህ ከፈቀድህለት፥ ዓለም ሰውን በሚችለው ገንዘብ ሙታን ሁሉ መኖርን ይችሉ ዘንድ እንዲያፈራልን እናርስና እንዘራ ዘንድ ልብንና ሕሊናን ብትሰጠን በተሻለን ነበር። 7 የእጆችህ ፍጥረት እኛ አንተ እንደተናገርህ ሁላችን የተካከልን ነንና። 8 ዛሬ በማኅፀን ትፈጥረዋለህና፥ ሥጋንና ሕዋሳትንም ትቀርጽለታለህና፥ ማስተዋልንም ትሰጠዋለህና፥ በእሳትና በውኃ ትጠብቀዋለህና፥ ያን የፈጠርኸውንም በማኅፀን ዘጠኝ ወር ትሸከመዋለህና፥ ባንተም ቃል ይጠበቃልና። 9 ዳግመኛም እናቱ በወለደችው ጊዜ፥ ከተወለደና ከተፈጠረ በኋላ፥ የሚጠባበትን ወራት እስኪጨርስ ድረስ ይህ ባሪያህ ሕፃኑ ያድግ ዘንድ፥ 10 ከሰውነትዋ በላይ ካሉ ከጡቶችዋም የጡት ፍሬ ወተት ይፈስለት ዘንድ ታዝለታለህ፥ 11 ይህ ባሪያህ እስከ ጊዜው ድረስ ያድግ ዘንድ በቸርነትህ ታሳድገዋለህ። 12 በቸርነትህም ትመግበዋለህ፤ ሕግህንም ታስተምረዋለህ፤ በጥበብህም ትገሥጸዋለህ። 13 ከዚህ በኋላ የፈጠርኸውንና ሕያው ያደረግኸውን ያን ባሪያህን ትገድለዋለህ። 14 ፈጥረህ ይህን ያህል ዘመን ያኖርኸውን ያን ባሪያህን የምታጠፋው ከሆነ እንግዲያ ለምን ፈጠርኸው? 15 አሁንም ነገርህ እውነት ነው፤ ስለ ሁሉም አንተ ታውቃለህ፤ ነገር ግን እናገር ዘንድ እኔን ያተጋኝ አይደለም። 16 ይህን የማዝን ስለ ወገኖችህና ስለ ርስትህ ነው እንጂ። 17 ይህንም በፊትህ እማልድ ዘንድ የጀመርሁት ስለ እኔም፥ ስለ እነዚያም ነው። የሚመጣውን ዓለም ሕጉን እየሰማን የምንኖር የእኛን መሰነካከል አያለሁና። 18 ስለዚህም ቃሌን ስማ፤ በፊትህ የምናገረውንም ልመናዬን አድምጥልኝ።” የዕዝራ ጸሎት19 ሳይወስዱት የዕዝራ የጸሎቱ ቃል መጀመሪያ ይህ ነው። 20 “ለዘለዓለሙ የምትኖር አቤቱ፥ በልዑል አርያም ሁነህ የምታይ፥ በሰማይ ያለህ፥ 21 ሥልጣንህ የማይሸነፍ፥ መንግሥትህ የማያልፍ፥ ሠራዊተ መላእክት በፍርሀት የሚቆሙልህ፥ 22 ነፋስና እሳት በትእዛዝህ የተፈጠሩ፥ ቃልህ ጽኑ የሆነ፥ የተናገርኸውም ጸንቶ የሚኖር፥ 23 ሥርዐትህ ጽኑ የሆነ፥ ትእዛዝህም የሚያስፈራ፥ ትእዛዝህም ጥልቆችን የሚያደርቅ፥ ቍጣህም ተራራዎችን የሚያቀልጥ፤ ሕግህም እውነት የሆነ፥ 24 አቤቱ፥ የባሪያህን ቃል ስማ፤ የባሪያህን ልመና አድምጥ፤ ነገሬንም አድምጥ። 25 እኔ በሕይወት ሳለሁ እነግርሃለሁ፤ ልቡናዬም እንዳሰበ መጠን እነግርሃለሁ፤ እመልስልሃለሁም። 26 የወገኖችህን በደል አትመልከት፤ ለአንተ የተገዙልህን ጽድቃቸውን ተመልከት እንጂ። 27 የኃጥኣንን ሥራቸውን አትመልከት፤ በመከራቸው ሥርዐትን የጠበቁትን ተመልከት እንጂ። 28 በፊትህ ክፉ ሥራን ስለሠሩ አትቈጣ፤ በፍጹም ልባቸው በሕግህ የታመኑትን አስብ እንጂ። 29 በሥራቸው እንደ እንስሳ የሆኑ ሰዎችን ጥፋት አትውደድ። ሥርዐትህን በብሩህ ልቡና ያጸኗትን አስባቸው፤ ተመልከታቸውም እንጂ። 30 ከአራዊት የከፉ ሰዎችን አትቈጣቸው። በጌትነትህ መታመን ያዘወተሩትን ውደዳቸው እንጂ። 31 ነገር ግን እኛና ከእኛ አስቀድሞ የነበሩ ሞትን የሚያመጣ ሥራን ሠራን። 32 አንተ ግን ስለ እኛ፥ ስለ በደሉ ሰዎችም ይቅር ባይ ሁን፤ በጎ ሥራ የሌለን እኛን ይቅር ብትለን ያንጊዜ ይቅር ባይ ትባላላህና። 33 በአንተ የተዘጋጀ በጎ ሥራ ያላቸው ጻድቃንን ግን በሥራቸው ይቅር ትላቸዋለህ። 34 ትቈጣው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ስለ እርሱስ ታዝን ዘንድ የመዋቲ ወገን ምንድን ነው? 35 አሁንም ከተወለደው ወገን የማይበድል እንደሌለ እውነት እናገራለሁ። 36 ነገር ግን ጌታ ሆይ፥ ስለዚህ በጎ ሥራ የሌላቸውን ይቅር ብትላቸው ቸርነትህ ፈጽሞ ይታወቃል።” 37 እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “በእኔ ዘንድ እውነትን ተናገርህ፤ አንተ እንደ ተናገርኸው እንዲሁ ነው። 38 ለሚበድሉ ሰዎች ሞትን፥ ፍርድንም፥ ጥፋትንም በእውነት አልወድላቸውም። 39 ነገር ግን ስለ ጻድቃን ደስ ይለኛል፤ የሚድኑ ዋጋቸውን ያገኛሉና። 40 እንደ ተናገርኸውም እንዲሁ ይሆናል። 41 ገበሬ ብዙ ዘር እንደሚዘራ፥ ብዙ ተክልንም እንደሚተክል፥ ጊዜውም ቢሆን ዘሩ ሁሉ የሚበቅል እንደ አይደለ፥ ተክሉም ሁሉ ሥር የሚሰድድ እንደ አይደለ፥ በዚህ ዓለም ያሉ ሰዎችም እንዲሁ ናቸው፤ ሁሉም የሚድኑ አይደሉም።” 42 እኔም መለስሁለት፤ እንዲህም አልሁት፥ “በፊትህ ባለሟልነትንስ ካገኘሁ ልናገር። 43 የገበሬ ዘርስ ባይበቅል ምናልባት ዝናም ባያገኝ ይሆናል፤ ስለዚህም ይጠፋል። 44 ነገር ግን በእጅህ የፈጠርኸው፥ በአምሳልህም የመሰልኸው ሰው አምሳልህ ነውና፥ ስለ እርሱም ሁሉን ፈጥረሃልና፥ እንግዲህ እንደ ገበሬ ዘር ለምን ታደርገዋለህ? 45 አቤቱ አገባብህም አይደለም፤ ለወገኖችህ ራራ፤ ርስትህንም ይቅር በል እንጂ፤ ፍጥረትህን ይቅር ትለዋለህና።” 46 እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “በዚህ ዓለም ያለው በዚህ ዓለም ላሉት ምሳሌያቸው ነው፤ የወዲያው ዓለም ግን በወዲያው ዓለም ለሚኖሩ ምሳሌያቸው ነው። 47 ነገር ግን ዕውቀት ያነሰህ አንተ ከእኔ ይልቅ ፍጥረቴን ፈጽመህ ትወድድ ዘንድ፥ ይልቁንም አንተ ኃጥእ ሳትሆን በብዙ ወገን ኃጥእን ትመስላለህ። 48 ነገር ግን ስለዚህ በልዑል ዘንድ ትመሰገናለህ፤ 49 ራስህን አዋርደሃልና፥ ፈጽመህም ትመሰገን ዘንድ እንደሚገባህ ራስህን እንደ ጻድቃን አላደረግህምና። 50 አሁንም በዚህ ዓለም የሚኖሩ ጐስቋሎች በኋላ ዘመን ብዙ መከራን ይቀበላሉ። በብዙ ትዕቢት ኖረዋልና። 51 አንተ ግን ለራስህ ዕወቅ፤ እንደ አንተ ያሉትንም ክብር መርምር፤ 52 ገነት ለእናንተ ተከፍታለችና፥ ዕፀ ሕይወትም ተተክሏልና፥ የሚመጣውም ዓለም ተዘጋጅቶ ተሠርትዋልና፥ ደስታም ተሠርታለችና፥ ዕረፍትም ተነጥፋለችና፥ በጎ በረከትም ጸንታለችና፥ የጥበብ ሥርዋ ተገኝትዋልና። 53 እንግዲህ ወዲህ ደዌ አበቃ፤ ሞትም ጠፋ፤ መቃብርም ተሰወረች፤ ሙስናም ጠፋ። 54 መከራም ተዘነጋ፤ የሕይወት መዝገብም ተገለጠ። 55 እንግዲህ ወዲህ ስለሚጠፉት ሰዎች ብዛት መመራመርን አትድገም። 56 እነርሱ ነጻነትን አግኝተው ልዑልን ንቀውታልና፥ ሕጉንም አቃልለዋልና፥ ሥርዐቱንም ትተዋልና። 57 ጻድቃኑንም ረግጠዋቸዋልና። 58 እንደሚሞቱም እያወቁ በልቡናቸው እግዚአብሔርን አንፈልገውም ብለዋልና። 59 ስለዚህም ይህ በጎው ለእናንተ እንደ ሆነ እንዲሁም ይህ ጥፋት ለእነርሱ ነው። 60 እነርሱ ከተፈጠሩ በኋላ የፈጣሪያቸውን ስም አሳድፈውታልና፥ ያዘጋጀላቸውን እግዚአብሔርንም አላመሰገኑትምና። 61 አሁንም ፍርዳቸው ይደርስባቸዋል። 62 ለአንተና እንደ አንተ ለአሉ ለጥቂቶች እንጂ ይህን ለብዙዎች አልተናገርሁም።” 63 እኔም መለስሁለት፤ እንዲህም አልሁት፥ “አቤቱ! እነሆ፥ እስካሁን ድረስ በኋላ ዘመን ታደርገው ዘንድ ያለህን ብዙ ምልክት ነገርኸኝ፤ ነገር ግን ጊዜው መቼ እንደ ሆነ አልነገርኸኝም።” |