ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 መልአኩም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “አንተ ራስህ ገምግመው፤ እኔ ከነገርሁህ ምልክት ያለፈ ብታይ፥ 2 ልዑል የፈጠረውን ዓለም ይጐበኝበት ዘንድ ያለው ጊዜ እንደ ደረሰ ያንጊዜ ዕወቅ። 3 በዓለም በየሀገሩ ሽብር በሆነ ጊዜ፥ አሕዛብም በታወኩ ጊዜ፥ ሕዝቡም በተሸበሩ ጊዜ፥ አለቆችም በተዋጉ ጊዜ፥ መሳፍንቱም በደነገጡ ጊዜ፥ 4 ስለዚህ ልዑል ከጊዜው አስቀድሞ እንደ ተናገረ ያንጊዜ ዕወቅ። 5 በዓለም የሆነው ሁሉ አስቀድሞ በቃል፥ ኋላም በመገለጥ እንደ ሆነ፥ 6 እንዲሁም የልዑል ዓለም መጀመሪያ በቃል፥ በተአምርና በኀይል፥ ኋላ ግን በሥራና በድንቅ ነው። 7 በምግባሩና በአመነበት ሃይማኖቱ የዳነና ማምለጥ የቻለ፥ 8 ከነገርሁህ ሥቃይ የሚድን እርሱ ብቻ ነው፤ ከዚህ ዓለም ለእኔ በለየኋት በምድሬና በድንበሬም ሕይወትን ያያል። 9 ዛሬ ትእዛዜን ቸል ያሉ ያንጊዜ መከራን ይቀበላሉ፤ እኔን መፍራትን የተዉና የናቁኝም በገሃነም ውስጥ ይጨነቃሉ። 10 እኔ እየረዳኋቸው በሕይወታቸው ሳሉ የማያውቁኝም ሁሉ፥ 11 እነርሱ ነጻ ሳሉ በሕጌ ላይ የታበዩም ሁሉ፥ 12 የትዕግሥቴም ቦታ ክፍት ሆኖላቸው ሳለ ልብ ያላደረጉኝ፥ የናቁኝም ሁሉ፥ ከሞቱ በኋላ ያውቁኝ ዘንድ አላቸው። 13 አንተ ግን ኃጥኣን እንዴት እንደሚፈረድባቸው አትመርምር፤ ጻድቃን በዓለማቸው እንዴት እንደሚድኑ መርምር እንጂ፤ የሚመጣው ዓለም ስለ እነርሱ ነውና።” 14 እኔም መለስሁለት፤ እንዲህም አልሁት፦ 15 “ዝናም ከካፊያ እንደሚበዛ ከሚድኑት ኋለኞች ይልቅ የሚጠፉት እንደሚበዙ ቀድሞ ተናገርሁ፤ ዛሬም እናገራለሁ።” 16 እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ዘሩ በእርሻው መጠን እንደ ሆነ ፍርዱም እንደ ሥራው ነው፤ አጫጁም በአራሹ መጠን ነው። 17 ዛሬ በውስጡ የሚኖሩበት ዓለማቸው ሳይፈጠር ያዘጋጀሁት ዓለም በጊዜው ነውና። 18 ያንጊዜም የተከራከረኝ የለም፤ ማንም የነበረ የለምና። 19 አሁንም በምግብና ፍለጋ በሌለው በዘለዓለማዊ ሕግ በተዘጋጀው ዓለም ከተፈጠሩ በኋላ በሥራቸው ሞት ነበር። 20 ዓለሙንም ባየሁት ጊዜ እነሆ፥ እነርሱ ጠፉ። በምድር በተዘራው ሥራቸውም እነሆ፥ ዓለም ይጨነቃል። 21 ሄጄም ለጥቂቶቹ ራራሁላቸው፤ ከዘለላውም ውስጥ ፍሬዎችን ለእኔ አስቀረሁ። ከብዙ ዛፍም አንድ ተክል መረጥሁ። 22 በከንቱ የተወለዱ ብዛታቸው ይጠፋል፤ በብዙ ሥራ የጸናች ፍሬዬም፥ ተክሌም ትጠበቃለች። 23 አንተ ግን ዳግመኛ ሰባት ቀን ብትጾምና ብትጸልይ፥ 24 ግንብ ወደአልተሠራባት ምድረ በዳ ብትሄድና ከእንጨት ፍሬ ብቻ ብትበላ፥ ሥጋም ባትበላ፥ ከእንጨቱ ፍሬ ብቻ በቀርም ወይን ባትጠጣ፥ 25 ወደ ልዑል ሁልጊዜ ብትጸልይ መጥቼ እነግርሃለሁ።” አራተኛው ራእይ 26 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ ስሙ አርፋድ ወደሚባል ምድረ በዳ ሄድሁ። 27 በሣር ውስጥ ተቀመጥሁ፤ የምድረ በዳንም ፍሬ ተመገብሁ፤ የበላሁትም ያጠግበኝ ነበር። 28 ከዚህም ከሰባተኛው ቀን በኋላ በሣር ውስጥ ተኝቼ ሳለሁ ልቤ እንደ ቀድሞው ታወከብኝ። 29 አንደበቴንም አቅንቼ በልዑል ፊት እናገር ጀመርሁ፤ 30 እንዲህም አልሁ፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ ዛፍና ሣር በሌሉበት ምድረ በዳ ለአባቶቻችን ፈጽመህ ታየሃቸው። 31 እንዲህም አልሃቸው፦ ‘አንተ እስራኤል ስማኝ፤ ቃሌንም አድምጠኝ፤ 32 እነሆም እኔ ሕጌን በውስጣችሁ እዘራለሁና፥ በላያችሁም ፍሬን ያፈራልና፥ ለዘለዓለሙም ትከብሩበታላቸሁና።’ 33 አባቶቻችንም ሕግህን ተቀብለው አልጠበቁም፤ በሥርዐትህም አልጸኑም፤ የሕግህ ፍሬ ግን አልጠፋም፤ የአንተ ገንዘብ ስለሆነ ይጠፋ ዘንድ አይቻልምና። 34 ሕግ ያንተ ገንዘብ ስለሆነች በውስጣቸው የተዘራውን ተግባራቸውን አልጠበቁምና ሕግህን ተቀብለው ያልጠበቁ ጠፉ። 35 ምድርም ዘርን ከተቀበለች በኋላ፥ ባሕርም መርከብ በውስጧ ከገባ በኋላ፥ ዕቃም በውስጡ መብልና መጠጥን ከጨመሩበት በኋላ፥ 36 ያንጊዜ የዚያ የዘሩ፥ የዚያም የመርከቡ፥ የዚያም የመብሉና የመጠጡ ይጠፋ ዘንድ ጊዜው ቢሆን እንደዚሁ የሚጠፋ ይሆናል። ነገር ግን የያዙት ይቀራሉ። ለእኛስ እንደዚሁ አይደለም። ሕግን ተቀብለን የበደልን እኛ እንጠፋለንና፥ የተቀበለው ልባችንም እንዲሁ ነው፤ ሕጉ ግን በክብሩ ይኖራል እንጂ አይጠፋም።” ስለምታለቅሰው ሴት የዕዝራ ራእይ 37 በዐይኖችም በተመለከትሁ ጊዜ በቀኝ በኩል እነሆ፥ አንዲት የምታለቅስ ሴትን አየሁ፤ በታላቅ ድምፅም ትጮኽ ነበር፤ እጅግም አዝና ነበር፤ ልብሷም ተቀድዶ ነበር፤ በራሷም ላይ ዐመድ ነስንሳ ነበር። 38 ያ ቀድሞ የማስበው አሳቤም ተለየኝ፤ ወደ እርሷም ተመልሼ፥ “ምን ያስለቅስሻል? ልቡናሽንስ ለምን ታሳዝኛለሽ? አልኋት።” 39 እርስዋም አለችኝ፥ “ጌታዬ ለራሴ አለቅስ ዘንድ በመከራዬም ላይ መከራን እጨምር ዘንድ ተወኝ፤ ፈጽሜ እኔ አዝኛለሁና፥ ልቡናዬም ተጨንቃለችና።” 40 እኔም፥ “ምን ሆነሻል? ንገሪኝ” አልኋት። 41 እርስዋም አለችኝ፥ “እኔ ባሪያህ ከጥንት ጀምሮ መካን ነበርሁ፤ ሠላሳ ዘመን ከባሌ ጋር ስኖር ልጅ አልወለድሁም። 42 እኔም በዚያ በሠላሳው ዘመን ሁልጊዜ በየጊዜውና በየሰዓቱ በመዓልትና በሌሊት ወደ ልዑል እጸልይ ነበር። 43 ከዚህም ከሠላሳ ዓመት በኋላ እግዚአብሔር የባሪያውን ልመና ሰማ፤ መከራዬንም አየ፤ ድካሜንና ሥቃዬን ተመልክቶ አንድ ልጅ ሰጠኝ፤ በእርሱም ፈጽሞ ደስ አለኝ፤ እኔም፥ ባሌም፥ ያገሬም ሰዎች ሁሉ ደስ አለን፤ እግዚአብሔርንም አመሰገንነው። 44 በብዙ ድካምም አሳደግሁት። 45 ከዚህም በኋላ አካለ መጠን ባደረሰ ጊዜ ሚስት አጋባሁት፤ ሰርግንም ሰረግሁለት። |