ዘዳግም 12:11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚያም እኔ ያዘዝኳችሁን ነገር ሁሉ የምታመጡት እግዚአብሔር አምላካችሁ ለስሙ መጠሪያ ወደ መረጠው ቦታ ይሆናል፤ ይኸውም የሚቃጠል መሥዋዕታችሁንና ሌላውንም መሥዋዕታችሁን ሁሉ፥ ዐሥራታችሁንና መባችሁን ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር የተሳላችሁትን የበጎ ፈቃድ ስጦታችሁን ሁሉ ታመጡለታላችሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከዚያም አምላካችሁ እግዚአብሔር ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ፣ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፦ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራቶቻችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ እንዲሁም ለእግዚአብሔር የተሳላችኋቸውን ምርጥ ነገሮች ሁሉ ወደዚያ ታመጣላችሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ አምላካችሁም ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደ መረጠው ስፍራ፥ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፥ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁን ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፥ አሥራቶቻችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፥ እንዲሁም ለጌታ የተሳላችሁትን ምርጥ ነገሮች ሁሉ ወደዚያ ታመጣላችሁ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በዚያን ጊዜ አምላካችሁ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ፥ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ቍርባናችሁንም፥ ዐሥራታችሁንም፥ ከእጃችሁ ሥራ ቀዳምያቱን የተመረጠውንም መባችሁን ሁሉ፥ ለአምላካችሁም የተሳላችሁትን ሁሉ ውሰዱ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዚያን ጊዜ አምላካችሁ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ፥ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ሌላ መሥዋዕታችሁንም፥ አሥራታችሁንም፥ በእጃችሁ ያነሣችሁትንም ቍርባን፥ ለእግዚአብሔርም ተስላችሁ የመረጣችሁትን ስእለታችሁን ሁሉ ውሰዱ። |
‘ሕዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ የሚሠራበት በመላው እስራኤል ምንም ዐይነት ከተማ አልመረጥኩም፤ አሁን ግን በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን መርጬአለሁ።’ ”
የአሦር የጦር አዛዥ ንግግሩን በመቀጠል እንደገና እንዲህ አለ፦ “አምላክህ እግዚአብሔር እንደሚረዳህ አድርገህ ታስባለህን? ይህማ እንዳይሆን፥ አንተ የእግዚአብሔርን የተቀደሱ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችን ደምስሰህ ‘የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ማምለክ የሚገባቸው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው በአንድ መሠዊያ ብቻ ነው’ ብለህ ወስነሃል።
ዳዊትም “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና የእስራኤል ሕዝብ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርቡበት መሠዊያ ሊኖሩ የሚገባቸው በዚህ ስፍራ ነው” አለ።
እግዚአብሔር በሌሊት ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “ጸሎትህን ሰምቼአለሁ፤ ይህን ቤተ መቅደስ ለእኔ መሥዋዕት የሚቀርብበት ስፍራ ይሆን ዘንድ መርጬዋለሁ፤
ይህን ትእዛዝ ባለመቀበል በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማፍረስ የሚሞክረውን ማንኛውንም ንጉሥ ወይም ሕዝብ የስሙ መጠሪያ ይሆን ዘንድ የመረጠ አምላክ ያስወግደው፤ ይህን ትእዛዝ ያስተላለፍኩ እኔ ዳርዮስ ስለ ሆንኩ በሙሉ መፈጸም አለበት።”
እኔ እንድመለክበት በመጀመሪያ መርጬው ወደነበረው ቦታ ወደ ሴሎ ሂዱ፤ እዚያም ምን እንዳደረግሁት ተመልከቱ፤ በሕዝቤ በእስራኤል ኃጢአት ምክንያት ሴሎን ደመሰስኩት።
በተቀደሰው ስፍራ ለእግዚአብሔር ቊርባን ያቀርብ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ደም በከንቱ እንዳፈሰሰ ተቈጥሮ ይፈረድበታል፤ ከሕዝቡም ይለያል።
መሥዋዕትህን ሁሉ ማቅረብ የሚገባህ ከነገዶችህ መካከል የአንዱ ግዛት በሆነው ክፍል እና እግዚአብሔር በሚመርጠው በአንድ ስፍራ ብቻ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህንም ሆነ ሌላውንም እኔ ያዘዝኩህን ሁሉ በዚያ ስፍራ ብቻ ትፈጽማለህ።
አምላክህ እግዚአብሔር በሚመርጥልህ ቦታ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆችህ፥ ከወንዶችና ከሴቶች አገልጋዮችህ፥ እንዲሁም በከተሞችህ ከሚኖሩ ሌዋውያን ጋር እነዚህን ትበላለህ፤ እዚያም በድካምህ ያገኘኸውን መልካም ነገር ሁሉ ትደሰትበታለህ፤
እግዚአብሔር የመረጠው ያ አንድ ስፍራ ሩቅ ቢሆንብህ ግን በሚያሰኝህ ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር ከሰጠህ የከብትም ሆነ የበግ መንጋ መርጠህ እኔ ባዘዝኩህ መሠረት ማረድ ትችላለህ፤ ሥጋውንም በቤት ትበላዋለህ።
አምላካችሁ እግዚአብሔር ከነገዶቻችሁ ሁሉ መካከል ለእርሱ መኖሪያ ይሆን ዘንድ በዚያ ስሙ እንዲጠራበት የሚመርጠውን ቦታ ፈልጉና ወደዚያ ሂዱ፤
ሁልጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራት ትማር ዘንድ ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ቦታ የእህልህን፥ የወይን ጠጅህን፥ የዘይትህን ዐሥራት፥ እንዲሁም የከብቶችህንና የበጎችህን በኲራት በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላለህ፤
“ከከብትህ ወይም ከበግህ መንጋ የሚወለደውን ወንድ የሆነ በኲር ሁሉ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አድርግ፤ በኲር የሆኑትን በሬዎች ለማንኛውም ተግባር አትጠቀምባቸው፤ እንዲሁም ከበጎች መንጋ በኲሮችን ጠጒራቸውን አትሸልት፤
“በደም ማፍሰስ፥ በሰብአዊ መብት፥ በግድያ ወይም እነዚህን በመሳሰሉ ጉዳዮች በከተሞችህ በሚነሡ ክርክሮች የፍርድ አሰጣጡ አስቸጋሪ ቢሆንብህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ቦታ ፈጥነህ በመሄድ
የቀሩትም የእስራኤል ሕዝብ የሮቤል፥ የጋድና በምሥራቅ ያሉት የምናሴ ነገዶች በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ በከነዓን ምድር በምትገኘው በእስራኤላውያን ይዞታ በሆነችው በገሊሎት መሠዊያ መሥራታቸውን ሰሙ።
“የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚለው እንዲህ ነው፦ ‘በእስራኤል አምላክ ላይ ያላችሁን እምነት እንዴት ታጓድላላችሁ? ለራሳችሁ መሠዊያ በመሥራት ከእግዚአብሔር ርቃችኋል፤ በእርሱም ላይ ዐምፃችኋል፤
ለእግዚአብሔር የማንታዘዝ ከሆንንና የሠራነውን መሠዊያ የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባን፥ ወይም የአንድነት መሥዋዕት ልናቀርብበት አስበን ከሆነ ራሱ እግዚአብሔር ይቅጣን፤
እኛ እርሱን የሠራነው በእኛና በእናንተ ሕዝብ መካከል ምልክት ሆኖ እንዲኖር ነው፤ ይኸውም ከእኛ በኋላ ለሚነሡት ትውልዶች በተቀደሰ ድንኳኑ ፊት እግዚአብሔርን እንደምናመልክ የሚቃጠልና ሌላም መሥዋዕት፥ እንዲሁም የአንድነት መሥዋዕት ስናቀርብ ለመኖራችን ምስክር ይሆናል፤ ይኸውም የእናንተ ዘሮች የእኛን ልጆች ‘ከእግዚአብሔር ጋር ምንም ግንኙነት የላችሁም’ እንዳይሉአቸው ለማድረግ ይጠቅማል፤
እኛ በእግዚአብሔር ላይ አላመፅንም፤ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የእህል መባ፥ ወይም ሌላ መሥዋዕት ለማቅረብ አስበን ሌላ መሠዊያ በመሥራት እግዚአብሔርን ማምለክ አልተውንም፤ ከእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ለፊት ከቆመው ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ከተሠራው ሌላ የተለየ መሠዊያ መሥራት ከእኛ ይራቅ።”
ነገር ግን በዚሁ ጊዜ እንጨት በመቊረጥና ውሃ በመቅዳት ለእስራኤል ሕዝብና ለእግዚአብሔር መሠዊያ አገልጋዮች እንዲሆኑ አደረገ። እነርሱም እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ስሙ እንዲጠራበት በመረጠው ቦታ፥ ይህንኑ አገልግሎት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ።