መዝሙር 116 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምከሞት የዳነ ሰው ለእግዚአብሔር ያቀረበው ምስጋና 1 ጩኸቴንና ልመናዬን ስለ ሰማ እግዚአብሔርን እወደዋለሁ። 2 እርሱን በምጠራው ጊዜ ሁሉ ስለሚሰማኝ፥ በዘመኔ ሁሉ ወደ እርሱ እጮኻለሁ። 3 የሞት አደጋ ዙሪያዬን ከበበኝ፤ የመቃብር አስፈሪ ሁኔታ አሠቀቀኝ፤ በችግርና በሐዘን ተሸነፍኩ። 4 በዚያን ጊዜ “አምላክ ሆይ! እባክህ አድነኝ!” ብዬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽኩ። 5 እግዚአብሔር ቸርና እውነተኛ ነው፤ አምላካችን መሐሪ ነው። 6 እግዚአብሔር የዋሆች የሆኑትን ይጠብቃል፤ እኔ በተቸገርኩ ጊዜ አድኖኛል። 7 እግዚአብሔር መልካም ነገር ስላደረገልኝ፥ ከእንግዲህ ወዲያ አልጨነቅም። 8 እግዚአብሔር ከሞት አዳነኝ፤ እንባዬ እንዲቆም አደረገ፤ እግሮቼንም ከመደናቀፍ ጠበቃቸው። 9 ስለዚህ ሕያዋን በሚገኙበት በእግዚአብሔር ፊት እኖራለሁ። 10 “እጅግ ተሠቃየሁ” ባልኩበት ጊዜ እንኳ አንተን ማመኔን አልተውኩም። 11 በፍርሃቴ ጊዜ እንኳ “ማንም የሚታመን የለም” አልኩ። 12 ስላደረገልኝ መልካም ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ምን ውለታ ልመልስ እችላለሁ? 13 እግዚአብሔር ስላዳነኝ አመሰግነዋለሁ፤ የወይን ጠጅ መባም አቀርብለታለሁ። 14 በሕዝብ ጉባኤ ፊት ተገኝቼ ለእግዚአብሔር የተሳልኩትን አቀርባለሁ። 15 የቅዱሳን ሞት በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነው። 16 እግዚአብሔር ሆይ! እኔ የአንተ ነኝ፤ የብላቴናይቱ አገልጋይህ ልጅ ነኝ፤ እስራቴን ፈተህልኛል። ከሞት ያዳንከኝ አንተ ነህ። 17 የምስጋና መሥዋዕት አቀርብልሃለሁ፤ ወደ አንተም እጸልያለሁ። 18 በእርሱ ሕዝብ ጉባኤ ፊት ተገኝቼ ለእግዚአብሔር የተሳልኩትን አቀርባለሁ፤ 19 የማቀርበውም በኢየሩሳሌም መካከል በሚገኘው በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ነው። እግዚአብሔር ይመስገን! |