Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘዳግም 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የካህናቱና የሌዋውያን ድርሻ

1 “ሌዋውያን ካህናት፥ እንዲያውም፥ መላው የሌዊ ነገድ ከቀሩት የእስራኤል ነገዶች ጋር የርስት ድርሻ የላቸውም፤ በዚህ ምትክ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕትና መባ እየተመገቡ ይኖራሉ።

2 በወንድሞቻቸው በእስራኤላውያን መካከል ርስት አይኖራቸውም፤ በሰጣቸው ተስፋ መሠረት እግዚአብሔር ርስታቸው ነው።

3 “የቀንድ ከብት ወይም በግ በሚሠዋበት ጊዜ ካህናቱ ወርቹን፥ አገጩንና፥ ጨጓራውን ይወስዳሉ።

4 ከእህልህ፥ ከወይን ጠጅህና ከወይራ ዘይትህ ከተሸለቱ በጎችህም ጠጒር እንኳ ሳይቀር የመጀመሪያውን በኲራት ስጣቸው፤

5 ለዘለዓለም በክህነት ያገለግሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከነገዶቻችሁ መካከል የሌዊን ነገድ መርጦአል።

6 “አንድ ሌዋዊ ከሚኖርበት ከማንኛውም የእስራኤል ከተማ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ቦታ ለመምጣት ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖረው፥

7 እዚያ እንደሚያገለግሉት ሌዋውያን ጓደኞቹ በእግዚአብሔር አምላኩ ፊት ያገልግል።

8 ከቤተሰብ ንብረት ሽያጭ ገንዘብ የሚቀበል ቢሆንም እንኳ እርሱም ሌሎቹ ካህናት በሚያገኙት መጠን ድርሻውን ይቀበላል።


ከአሕዛብ ልማድ ስለ መጠበቅ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

9 “አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በምትገባበት ጊዜ በዚያ የሚኖሩ ሕዝቦች የሚፈጽሙትን አጸያፊ ልማድ ሁሉ አትከተል።

10 ማንም ከመካከልህ ወንድ ልጁን፥ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ አይኑር፤ ወይም አስማተኛ፥ ሟርተኛ፥ ጠንቋይ፥ መተተኛ አይሁን።

11 ወይም ደግሞ መናፍስትን የሚጠራ ወይም ከመናፍስት ጋር የሚነጋገር፥ ወይም የሙታን መናፍስትን የሚስብ አይኑር።

12 ይህን የሚያደርግ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላና አጸያፊ ነው፤ አንተ ወደ ፊት በተራመድህ ቊጥር አምላክህ እግዚአብሔር አሕዛብን ከፊትህ ነቃቅሎ የሚያሳድድበት ምክንያት ይህንኑ ዐይነት የረከሰ ሥራ በማድረጋቸው ነው።

13 አንተ ግን ለእግዚአብሔር በፍጹም ታማኝ መሆን ይገባሃል።”


እንደ ሙሴ ያለ ሌላ ነቢይ

14 ከዚህ በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፦ “እነዚህ ሀገራቸውን አስለቅቀህ የምትወርስባቸው ሕዝቦች ሟርተኝነትንና ጥንቈላን ይወዳሉ፤ አንተ ግን እግዚአብሔር አምላክህ ይህን እንድታደርግ አይፈቅድም።

15 እግዚአብሔር ከወገኖቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ መርጦ ያስነሣላችኋል፤ እርሱ የሚላችሁንም ሁሉ በመስማት ታዛዦች ሁኑ።

16 “በሲና ተራራ ላይ በተሰበሰባችሁበት ቀን እሞታለሁ ብለህ በመፍራት እግዚአብሔር ዳግመኛ እንዳይናገርህና የመገለጡን ሁኔታ የሚያመለክተውን አስፈሪ እሳት እንዳታይ ጠይቀህ ነበር።

17 ስለዚህም እግዚአብሔር (ጥያቄው ተገቢ ነው) አለኝ፤

18 እንደ አንተ ያለ ሌላ ነቢይ ከወንድሞቻቸው መካከል አስነሣላቸዋለሁ፤ እርሱ የሚናገረውን ቃል እሰጠዋለሁ፤ እኔም የማዘውን ሁሉ ለሕዝቡ ይነግራል፤

19 በእኔ ስም የሚናገረውን የዚያን ነቢይ ቃል የማይሰማ ሁሉ እቀጣዋለሁ።

20 ነገር ግን ያላዘዝኩትን ማንኛውንም ነገር በስሜ መናገር የሚደፍር ነቢይ፥ ወይም በሌሎች አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ ይገደል።

21 “ ‘አንድ ነቢይ የሚናገረው የትንቢት ቃል ከእግዚአብሔር ያልተሰጠ መሆኑን በምን ለይቼ ዐውቃለሁ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

22 አንድ ነቢይ በእግዚአብሔር ስም ትንቢት ተናግሮ ቃሉ ሳይፈጸም ቢቀር ያ ትንቢት ነቢዩ በግምት የተናገረው ነው እንጂ ከእግዚአብሔር ተሰጥቶት የተናገረው ቃል ስላልሆነ ልትፈራው አይገባም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos