ዘዳግም 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)አምልኮት ሊፈጸምበት የሚገባ ትክክለኛ ቦታ 1 “በምድር ላይ በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ትወርሷት ዘንድ በሚሰጣችሁ ሀገር ታደርጉት ዘንድ የምትጠብቁት ሥርዐት፥ ፍርድም ይህ ነው። 2 እናንተ የምትወርሱአቸው አሕዛብ አማልክቶቻቸውን ያመለኩባቸውን፥ በረዥም ተራሮች፥ በኮረብቶችም ላይ ከለምለምም ዛፍ በታች ያለውን ስፍራ ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉት፤ 3 መሠዊያቸውንም አፍርሱ፤ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ዐጸዶቻቸውንም ቁረጡ፤ የአማልክቶቻቸውንም ምስሎች በእሳት አቃጥሉ፤ ከዚያም ስፍራ ስማቸውን አጥፉ። 4 ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር እንዲህ ያለ ሥራ በዚያ አትሥሩ። 5 ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር ከከተሞቻችሁ ሁሉ በአንዱ ስሙ ይጠራ ዘንድ የመረጠውን ስፍራ ትሻላችሁ፤ ወደዚያም ትመጣላችሁ። 6 ወደዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ቍርባናችሁንም፥ ዐሥራታችሁንም፥ ቀዳምያታችሁን፥ ስዕለታችሁንም፥ በፈቃዳችሁ የምታቀርቡትን፥ የላማችሁንና የበጋችሁንም በኵራት ውሰዱ። 7 በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ብሉ፤ እጃችሁንም በምትዘረጉበት፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር በባረካችሁ ነገር ሁሉ፥ እናንተና ቤተሰባችሁ ደስ ይበላችሁ። 8 ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን፥ እኛ በዚህ ዛሬ የምናደርገውን ሁሉ አታድርጉ፤ 9 አምላካችሁ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ማረፊያና ርስት እስከ ዛሬ ድረስ አልደረሳችሁምና። 10 ዮርዳኖስን ግን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር በሚያወርሳችሁ ምድር በተቀመጣችሁ ጊዜ፥ ያለ ፍርሀትም እንድትኖሩ ከከበቡአችሁ ጠላቶች ሁሉ ዕረፍት በሰጣችሁ ጊዜ፥ 11 በዚያን ጊዜ አምላካችሁ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ፥ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ቍርባናችሁንም፥ ዐሥራታችሁንም፥ ከእጃችሁ ሥራ ቀዳምያቱን የተመረጠውንም መባችሁን ሁሉ፥ ለአምላካችሁም የተሳላችሁትን ሁሉ ውሰዱ። 12 እናንተም፥ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም፥ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁም፥ ከእናንተ ጋር ክፍልና ርስት ስለሌለው በደጆቻችሁ ውስጥ የተቀመጠው ሌዋዊም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ። 13 የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በሚታይህ ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ። 14 ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ከነገዶችህ ከአንዱ ዘንድ በመረጠው ስፍራ በዚያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን አቅርብ፤ በዚያም ዛሬ እኔ የማዝዝህን ሁሉ አድርግ። 15 “ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ሰጠህ በረከት፥ እንደ ፈቀድህ፥ በሀገርህ ሁሉ ውስጥ አርደህ ሥጋን ብላ፤ ከአንተ ንጹሕ ሰው፥ ንጹሕም ያልሆነ ሰው እንደ ሚዳቋና እንደ ዋላ ያለውን ይብላው። 16 ደሙን ግን እንደ ውኃ በምድር ላይ አፍስሱት እንጂ አትብሉት። 17 የእህልህን፥ የወይን ጠጅህን፥ የዘይትህንም ዐሥራት፥ የላምህንና የበግህንም በኵራት፥ የተሳልኸውንም ስእለት ሁሉ፥ በፈቃድህ ያቀረብኸውን፥ የእጅህንም ቀዳምያት በከተሞችህ ሁሉ ውስጥ መብላት አትችልም። 18 ነገር ግን አንተ፥ ወንድና ሴት ልጅህም፥ ወንድና ሴት አገልጋይህም፥ በሀገርህም ውስጥ ያለው መጻተኛ አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብሉት፤ እጅህንም በምትዘረጋበት ነገር ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ። 19 በምድርህ ላይ በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ሌዋዊዉን ቸል እንዳትል ተጠንቀቅ። 20 “አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ነገረህ ድንበርህን ባሰፋልህ ጊዜ፥ ሰውነትህም ሥጋ መብላት ስለ ወደደች፦ ሥጋ ልብላ ስትል፥ ሰውነትህ ከወደደችው ሁሉ ብላ። 21 አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙ ይጠራ ዘንድ የመረጠው ስፍራ ከአንተ ሩቅ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ከሰጠህ ከላምና ከበግ መንጋህ እንዳዘዝሁህ እረድ፤ ሰውነትህም የወደደችውን በሀገርህ ውስጥ ብላው። 22 ሚዳቋና ዋላ እንደሚበሉ እንዲሁ ብላው፤ ከአንተ ንጹሕ ሰው፥ ንጹሕም ያልሆነ ይብላው። 23 ደምን እንዳትበላ ተጠንቀቅ፤ ደሙ ነፍሱ ነውና፥ ነፍስም ከሥጋ ጋር አይበላምና። 24 በምድር ላይ እንደ ውኃ አፍስሰው እንጂ አትብላው። 25 በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ጥሩ የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ፥ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም እንዲሆንላችሁ፥ አትብላው። 26 ነገር ግን የተቀደሰውን ነገርህን፥ ስእለትህንም ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር ስሙ በዚያ እንዲጠራ ወደ መረጠው ስፍራ ሂድ። 27 ሥጋውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አቅርብ፤ የመሥዋዕትህም ደም በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፥ ሥጋውንም ብላው። 28 በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ጥሩ የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ፥ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ ለዘለዓለም መልካም ይሆንላችሁ ዘንድ እኔ የማዝዝህን እነዚህን ቃሎች ሁሉ ሰምተህ ጠብቅ። ለጣዖት መስገድ እንደማይገባ 29 “አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳቸው ዘንድ የምትሄድባቸውን አሕዛብ በፊትህ ባጠፋ ጊዜ፥ አንተም በወረስሃቸው ጊዜ፥ በምድራቸውም በተቀመጥህ ጊዜ፥ ከፊትህ ከጠፉ በኋላ እነርሱን ለመከተል እንዳትሻ፥ 30 አምላኮቻቸውንም እንዳትሻ፥ አሕዛብም ለአምላኮቻቸው እንደሚያደርጉ እኔም አደርጋለሁ እንዳትል ራስህን ጠብቅ። 31 ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እንዲሁ አታድርግ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአምላኮቻቸው በእሳት ስለሚያቃጥሉ አሕዛብ ለአምላኮቻቸው የሚያደርጉትን ርኩስ ነገር እግዚአብሔር ይጠላልና። 32 “እኔ ዛሬ የማዝዝህን ነገር ሁሉ ታደርገው ዘንድ ጠብቅ፤ ምንም በእርሱ ላይ አትጨምር፤ ከእርሱም ምንም አታጕድል። |