ዘዳግም 26 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበመከር ወራት የሚቀርብ በኲራትና ዐሥራት 1 “እግዚአብሔር አምላክህ እንድትወርሳት ወደሚሰጥህ ምድር ገብተህ በምትወርሳትና ተደላድለህ በምትቀመጥባት ጊዜ፥ 2 ከሚሰጥህ ምድር ከምታመርተው ምርት በኲራቱን በቅርጫት በማድረግ እግዚአብሔር አምላክህ ለስሙ መጠሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ቦታ ውሰድ፤ 3 በዚያን ወራት በሥልጣን ላይ ወዳለው ካህን ሄደህ እንዲህ በለው፦ ‘እኔ ዛሬ አስቀድሞ አምላክህ እግዚአብሔር ለእኛ ለልጆቻቸው እንዲሰጠን ለአባቶቻችን በመሐላ ቃል ወደገባላቸው ምድር መግባቴን አረጋግጣለሁ።’ 4 “ካህኑም ቅርጫቱን ተቀብሎ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ለፊት ያስቀምጠዋል፤ 5 ከዚያ በኋላ በእግዚአብሔር አምላክህ ፊት ይህን መግለጫ ስጥ፦ ‘አባቴ ከቦታ ወደ ቦታ በመዞር የሚኖር ሶርያዊ ነበር፤ ጥቂት ቤተሰብ ይዞ ወደ ግብጽ በመውረድ መጻተኛ ሆኖ ኖረ፤ ጥቂት የነበረው ታላቅ፥ ኀያል፥ ብዙ ሕዝብ ሆነ። 6 ግብጻውያን ግን አስጨነቁን፤ አዋረዱን፥ ባርያዎችም ሆነን እንድናገለግል አስገደዱን። 7 እኛም ወደ አባቶቻችን አምላክ ወደ እግዚአብሔር ጮኽን፤ እግዚአብሔርም ጩኸታችንን ሰምቶ ሥቃያችንን፥ ድካማችንንና መጨቈናችንን ተመለከተ። 8 እግዚአብሔርም በታላቅ ኀይሉና ሥልጣኑ ታላቅ ፍርሀትን በማሳደር፥ ሥራዎችን ተአምራትንና ድንቅ ሥራዎችን በማሳየት ከግብጽ አወጣን። 9 ወደዚህም አምጥቶ በማርና በወተት የበለጸገችውን ይህችን ለም ምድር አወረሰን። 10 ስለዚህም እነሆ፥ እኔ እርሱ ከሰጠኝ መጀመሪያ የሆነውን በኲራት አምጥቼአለሁ።’ “ከዚህም ቀጥሎ ቅርጫቱን በእግዚአብሔር ፊት በማኖር ስገድ፤ 11 ለአንተና ለቤተሰብህም እግዚአብሔር ባደረገላችሁ መልካም ነገር ሁሉ ደስ ብሎአችሁ አመስግኑ፤ ሌዋውያንና ከእናንተ ጋር የሚኖሩ መጻተኞች በዚህ የምስጋና ሥርዓት አፈጻጸም ላይ አብረው ይገኙ። 12 “በሦስተኛው ዓመት ማለት ዐሥራት በምታወጣት ዓመት ዐሥራትህን ሁሉ አጠናቅቀህ ከሰበሰብክ በኋላ በከተማህ ለሚገኙ ለሌዋውያን፥ ለመጻተኞች፥ ለሙት ልጆችና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ሰጥተህ ጠግበው እንዲበሉ አድርግ። 13 ከዚያም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ በል፦ ‘ከቤቴ የተቀደሰውን ድርሻ ወስጄ ባዘዝከን ትእዛዞች ሁሉ መሠረት ለሌዋውያን፥ ለመጻተኞች፥ ለሙት ልጆችና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ሰጥቼአለሁ፤ ከትእዛዞችህም አልተላለፍኩም፤ የዘነጋሁትም ነገር የለም። 14 በሞት ሐዘን ጊዜ ከእርሱ አልበላሁም፤ ንጹሕ ባልሆንኩበት ጊዜ ከእርሱ ምንም አላነሣሁም፤ ስለ ሞተ ሰው ለሚቀርብ መባ ከእርሱ ምንም አላቀረብኩም፤ ባዘዝከኝ መሠረት የአንተን የአምላኬን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ። 15 በሰማይ ካለው ቅዱስ መኖሪያህ ሆነህ ወደ ታች ተመልከት፤ ሕዝብህን እስራኤልንም ባርክ፤ ለቀድሞ አባቶቻችን በገባኸው ቃል መሠረት የሰጠኸንን በማርና በወተት የበለጸገችውን ለም ምድር ባርክ።’ ለእግዚአብሔር የተለየ ሕዝብ 16 “እግዚአብሔር አምላክህ ሕጎችንና ሥርዓቶችን እንድትጠብቅ እነሆ፥ ዛሬ ያዝሃል፤ ስለዚህ በፍጹም ልብህና ነፍስህ ጠብቃቸው። 17 እግዚአብሔር አምላክህ መሆኑንና በሕጉም የምትመራ መሆንህን ዛሬ አንተ አረጋግጠሃል፤ ሥርዓቱን፥ ትእዛዞቹንና ሕጎቹን ለመጠበቅና ታዛዥ ለመሆን ቃል ገብተሃል፤ 18 ስለዚህም እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት እነሆ፥ ዛሬ ለእርሱ የተለየህ ውድ ሕዝብ አድርጎ ተቀብሎሃል፤ ትእዛዞቹንም ሁሉ እንድትፈጽም ያዝሃል፤ 19 ይህን ብታደርግ ከፈጠራቸው ሕዝቦች ሁሉ በላይ በምስጋና፥ በስም፥ በክብርም ከፍ ሊያደርግህና በሰጠውም ተስፋ መሠረት ለእርሱ የተለየህ ሕዝብ እንደሚያደርግህ ነግሮሃል።” |