ዘዳግም 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 “ከከብት ወይም ከበግ መንጋዎች መካከል አንዳች ነውር ያለበትን እንስሳ ለእግዚአብሔር ለአምላክህ መሥዋዕት አድርገህ አታቅርብ፤ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው። 2 “እግዚአብሔር አምላክህ ከሚሰጥህ ከተሞች በአንድዋ የሚገኝ ወንድ ወይም ሴት በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር አድርጎ ቃል ኪዳኑን ያፈርስ ይሆናል፤ 3 እንዲሁም እኔ የከለከልኳቸውን፦ ፀሐይን፥ ጨረቃን፥ ከዋክብትን ያመልክ ይሆናል፤ 4 እንዲህ ያለውን ወሬ በምትሰማበት ጊዜ በጥብቅ መርምር፤ እንደዚህ ያለውም ክፉ ነገር በእስራኤል መደረጉ እርግጠኛ ሆኖ ከተገኘ፥ 5 ያን ሰው ወይም ያቺን ሴት ከከተማ ወደ ውጪ አውጥተህ በድንጋይ ወግረህ ግደል። 6 ሆኖም በዚህ ሁኔታ በሞት መቀጣት የሚገባው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች በእርሱ ላይ ከመሰከሩበት በኋላ ነው፤ ምስክሩ አንድ ብቻ ከሆነ ግን ያ ሰው አይገደል። 7 ምስክሮቹ የመጀመሪያዎቹን ድንጋዮች ይወርውሩ፤ ከዚያም ቀጥሎ ሌላው ሕዝብ በድንጋይ ይውገረው፤ በዚህም ዐይነት እንደዚህ ያለውን ክፉ ነገር ሁሉ ከመካከልህ ታስወግዳለህ። አስቸጋሪ የፍርድ ጉዳዮች 8 “በደም ማፍሰስ፥ በሰብአዊ መብት፥ በግድያ ወይም እነዚህን በመሳሰሉ ጉዳዮች በከተሞችህ በሚነሡ ክርክሮች የፍርድ አሰጣጡ አስቸጋሪ ቢሆንብህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ቦታ ፈጥነህ በመሄድ 9 ከሌዋውያን ወገን ካህናት ለሆኑትና በዚያን ጊዜ ዳኛ ለሆነው ጉዳዩን አቅርብ፤ ጉዳዩንም እነርሱ ይወስኑ። 10 እግዚአብሔር በሚመርጠው ቦታ ሆነው የሚሰጡህን ውሳኔ በትክክል እሥራ ላይ አውል፤ እነርሱም የሚነግሩህን በጥንቃቄ ጠብቅ። 11 በሚሰጡአችሁ መመሪያና ሕግ መሠረት ሁሉን አድርጉ፤ ከዚያም ወደ ግራ ወይም ወደ ቀኝ ፈቀቅ አትበሉ። 12 ዳኛውን ወይም አምላክህን እግዚአብሔርን በማገልገል ላይ ያለውን ካህን ባለመታዘዝ የሚዳፈር ሰው ቢኖር በሞት ይቀጣ። በዚህም ዐይነት እንደዚህ ያለውን ክፉ ነገር ሁሉ ከእስራኤል ታስወግዳለህ። 13 ከዚያን በኋላ ሰው ሁሉ ይህን ሰምቶ ይፈራል፤ ይህንንም የመሰለ ክፉ ነገር ለመፈጸም የሚዳፈር አይኖርም። ስለ ንጉሥ የተሰጠ መመሪያ 14 “እግዚአብሔር አምላክህ ወደሚሰጥህ ምድር በመግባት ምድሩን ወርሰህ ከተደላደልክ በኋላ በዙሪያዬ እንዳሉት ሕዝቦች ንጉሥ ላንግሥ ብትል፥ 15 እግዚአብሔር አምላክህ የሚመርጥልህን ንጉሥ ልታነግሥ ትችላለህ፤ በአንተም ላይ የምታነግሠው ንጉሥ ከወገንህ መካከል ይሁን፥ ከወገንህ ያልሆነውን የውጪ አገር ሰው ልታነግሥ አይገባህም። 16 ያም ንጉሥ ለሠራዊቱ ብዙ ፈረሶች ያሉት መሆን የለበትም፤ እግዚአብሔር ሕዝቡ ወደ ግብጽ እንዳይመለሱ ስለ አዘዘ ፈረሶችን ለመግዛት ወደ እዚያ ሰዎችን አይላክ። 17 ደግሞም ንጉሡ ብዙ ሚስቶች እንዲኖሩት ማድረግ እግዚአብሔርን ከመከተል ስለሚገታው ንጉሡ ብዙ ሚስቶች እንዲኖሩት አያስፈልገውም፤ ወርቅና ብርም በብዛት አያከማች። 18 ይልቅስ ንጉሥ በሚሆንበት ጊዜ እነዚህ በሌዋውያን ካህናት ተጠብቀው የሚኖሩት የእግዚአብሔር ሕግጋት የተጻፉበትን መጽሐፍ አንድ ቅጅ እንዲኖረው ያድርግ። 19 ይህን መጽሐፍ አጠገቡ በማኖር በዘመኑ ሁሉ ያንብበው፤ ይህንንም ቢያደርግ እግዚአብሔርን ማክበርና በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉትንም ሕጎችና ደንቦች በጥንቃቄና በታማኝነት መፈጸምን ይማራል። 20 ራሱንም ከወገኖቹ ከእስራኤላውያን እበልጣለሁ ብሎ እንዳይታበይና ከእግዚአብሔርም ትእዛዞች እንዳይርቅ ይጠብቀዋል። ይህን ቢያደርግ ለብዙ ዘመን ይነግሣል፤ ልጆቹም በእስራኤል ላይ ለብዙ ዘመን ይነግሣሉ። |