ዘዳግም 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበሐዘን ጊዜ የተከለከለ የለቅሶ ልምድ 1 “እናንተ የአምላካችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ ስለዚህ ለሞተ ሰው በምታዝኑበት ጊዜ ፊታችሁን አትንጩ፤ ጠጒራችሁንም አትላጩ፤ 2 አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተለየህ ሕዝብ ነህ፤ በምድር ላይ ከሚኖሩ ከሌሎች ሕዝቦች መካከል ለእርሱ የተለየህ ሕዝብ ትሆን ዘንድ ለራሱ መርጦሃል። የሚበሉና የማይበሉ እንስሶች ( ዘሌ. 11፥1-47 ) 3 “ርኩስ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትብሉ፤ 4 ስለዚህም ልትበሉአቸው የተፈቀዱላችሁ እንስሶች እነዚህ ናቸው፤ ይኸውም የቀንድ ከብቶችን፥ በጎችንና ፍየሎችን፥ 5 አጋዘን ሚዳቋ፥ ቦራይሌ፥ የሜዳ ፍየል፥ ዋላ፥ ድኩላንና ብሖርን ትበላላችሁ። 6 በአጠቃላይም ሰኮናቸው የተከፈለና የሚያመሰኩ እንስሶችን ትበላለህ፤ 7 ነገር ግን ሰኮናቸው ያልተከፈለውንና የማያመሰኩትን እንስሶች አትብሉ፤ በዚህም ዐይነት ግመል፥ ጥንቸልና ሽኮኮ የመሳሰሉትን አትብሉ፤ እንደነዚህ ያሉት እንስሶች የሚያመሰኩ ቢሆኑም ሰኮናቸው ያልተከፈለ በመሆኑ የረከሱ ሆነው ይቈጠራሉ፤ 8 ዐሣማዎችን አትብሉ፤ እነርሱ ሰኮናቸው የተከፈለ ቢሆንም ስለማያመሰኩ የረከሱ ሆነው ይቈጠራሉ፤ እንደነዚህ ያሉትን እንስሶች መብላት ይቅርና በድናቸውን እንኳ አትንኩ። 9 “ከዓሣ ዐይነቶችም ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ሁሉ መብላት ትችላላችሁ፤ 10 ነገር ግን በውሃ ውስጥ የሚገኘው ክንፍና ቅርፊት የሌለው ፍጥረት ሁሉ አይበላም፤ እንደነዚህ ያሉት እንስሶች በእናንተ ዘንድ የረከሱ ሆነው መቈጠር አለባቸው። 11 “ከወፍ ዐይነቶችም ንጹሓን የሆኑትን ትበላላችሁ። 12 ሊበሉ የማይገባቸው ግን እነዚህ ናቸው፦ ንስር፥ ገዴ፥ ዓሣ ኣውጭ፥ 13 ጭልፊት፥ ጭላት፥ በየወገኑ፥ 14 ቊራ በየወገኑ፥ 15 ሰጎን፥ ጠላቋ፥ ዝይ፥ በቋል በየወገኑ፥ 16 ጒጒት፥ ጋጋኖ፥ የውሃ ዶሮ፥ 17 ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥ እርኩም 18 ሸመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፥ ጅንጁላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ። 19 “ክንፍ ያላቸው ጥቃቅን ነፍሳት ሁሉ የረከሱ ናቸው፤ እንደነዚህ ያሉት አይበሉም፤ 20 ነገር ግን ከእነርሱ መካከል በተለይ ንጹሓን የሆኑትን ትበላላችሁ። 21 “ሞቶ የተገኘውን እንስሳ አትብላ፤ በመካከልህ የሚኖሩ የውጪ አገር ሰዎች እንዲመገቡት ፍቀድላቸው፤ ወይም ለውጪ አገር ሰዎች በዋጋ ልትሸጥላቸው ትችላለህ። አንተ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተለየህ ሕዝብ ነህ። “የፍየልን ግልገል በእናቱ ወተት አትቀቅል። የዐሥራት አወጣጥ ሕግ 22 “በየዓመቱ አርሰህ ከምታገኘው ሰብል ሁሉ ከዐሥር እንዱን እጅ ለይተህ ታስቀምጣለህ፤ 23 ሁልጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራት ትማር ዘንድ ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ቦታ የእህልህን፥ የወይን ጠጅህን፥ የዘይትህን ዐሥራት፥ እንዲሁም የከብቶችህንና የበጎችህን በኲራት በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላለህ፤ 24 ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ ጊዜ እርሱ ለስሙ መጠሪያ እንዲሆን የመረጠው ቦታ ከአንተ በጣም ሩቅ በመሆኑ ለይተህ ያስቀመጥከውን ዐሥራት ለማጓጓዝ ቢያስቸግርህ፥ 25 ዐሥራቱን ሸጠህ ገንዘቡን በመያዝ እግዚአብሔር እንዲመለክበት ወደ መረጠው ቦታ ሂድ። 26 እዚያም በገንዘቡ የምተፈልገውን ነገር ከብት፥ ወይም በግ፥ ወይም የወይን ጠጅ፥ ወይም ጠንካራ መጠጥ፥ ወይም ማንኛውንም የመረጥከውን ነገር ገዝተህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት አንተና ቤተሰብህ በመብላት ተደሰቱ። 27 “በከተሞችህ የሚኖሩ ሌዋውያን ድርሻ ወይም ርስት ስለሌላቸው እነርሱን ችላ አትበል። 28 በየሦስተኛው ዓመት መጨረሻ ላይ ከእርሻችሁ ሰብል ሁሉ ከዐሥር አንዱን እያወጣችሁ በከተሞቻችሁ አከማቹ፤ 29 በከተሞቻችሁ የሚኖሩ ከእናንተ ጋር የተካፈሉት ርስት የሌላቸው ሌዋውያን፥ የውጪ አገር ስደተኞች፥ እናትና አባት የሌላቸው የሙት ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸው መጥተው ይብሉ፤ ይህን ሁሉ ብታደርጉ አምላካችሁ እግዚአብሔር በምትሠሩት ነገር ሁሉ ይባርካችኋል። |