ኤርምያስ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኤርምያስ በቤተ መቅደስ እንዳስተማረ 1-3 እግዚአብሔር የይሁዳ ሕዝብ ወደሚሰግዱበት ወደ ቤተ መቅደሱ የቅጽር በር ላከኝ፤ በዚያ ቆሜ እንድነግራቸው ያዘዘኝ ቃል ይህ ነው፦ “የአኗኗራችሁንና የተግባራችሁን ሁኔታ ለውጡ፤ እኔም በዚህች ምድር እንድትኖሩ እፈቅድላችኋለሁ፤ 4 ‘ይህ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው! ይህ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው፤ ይህ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው! እኛም በሰላም እንኖራለን!’ በምትሉት ከንቱ ቃላችሁ አትታመኑ። 5 “ይልቅስ የአኗኗራችሁንና የተግባራችሁን ሁኔታ ለውጡ፤ እርስ በርሳችሁ ቅንነት በሞላበት ፍቅር ተሳስራችሁ ኑሩ፤ 6 መጻተኞችን፥ እናትና አባት የሞቱባቸውን ልጆችና፥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በመጨቈን አትበዝብዙ፤ በዚህች ምድር የሚኖሩ ንጹሓን የሆኑ ሰዎችን በግፍ አትግደሉ፤ እንዳትጠፉም ለሐሰተኞች አማልክት አትስገዱ። 7 በዚህ ዐይነት ለውጥ የምታሳዩ ከሆነ ለቀድሞ አባቶቻችሁ ለዘለዓለም ርስት አድርጌ በሰጠኋቸው በዚህች ምድር እንድትኖሩ እፈቅድላችኋለሁ። 8 “ተመልከቱ! እናንተ እኮ በሚያታልሉ ከንቱ ቃላት ትተማመናላችሁ፤ 9 ከዚህም የተነሣ ትሰርቃላችሁ፤ ትገድላላችሁ፤ ታመነዝራላችሁ፤ ምላችሁም በሐሰት ትመሰክራላችሁ፤ ለባዓል መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ከዚህ በፊት የማታውቁአቸውን አማልክት ታመልካላችሁ። 10 እኔ የምጠላውን ይህን ሁሉ ነገር ከፈጸማችሁ በኋላ ወደ ቤተ መቅደሴ መጥታችሁ በፊቴ በመቆም ‘እኛ ከጥፋት ድነናል!’ ትላላችሁ። 11 ቤተ መቅደሴ የሌቦች መደበቂያ ዋሻ መሰላችሁን? የምታደርጉትን ሁሉ እነሆ እኔ ራሴ አይቼአለሁ፤ 12 እኔ እንድመለክበት በመጀመሪያ መርጬው ወደነበረው ቦታ ወደ ሴሎ ሂዱ፤ እዚያም ምን እንዳደረግሁት ተመልከቱ፤ በሕዝቤ በእስራኤል ኃጢአት ምክንያት ሴሎን ደመሰስኩት። 13 እናንተ ይህን ሁሉ በደል ፈጸማችሁ፤ ደጋግሜ ብነግራችሁም አናዳምጥም ብላችኋል፤ በጠራኋችሁም ጊዜ መልስ አልሰጣችሁኝም። 14 ስለዚህ በሴሎ ያደረግኹትን በዚህ በምትታመኑበት በቤተ መቅደሴ አደርጋለሁ፤ ለቀድሞ አባቶቻችሁና ለእናንተ በሰጠሁት በዚህ ቦታ በሴሎ ያደረግኹትን ደግሜ አደርጋለሁ። 15 ወንድሞቻችሁ የሆኑትን የእስራኤልን ሕዝብ እንዳሳደድኩ፥ እናንተንም ከፊቴ አሳድዳችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” የሕዝብ አለመታዘዝ 16 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ኤርምያስ ሆይ! ስለ ነዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ስለ እነርሱ በመጸለይም አትጩኽ፤ ስለማልማለድህ ስለ እነርሱ ልትማልደኝ አያስፈልግም፤ 17 ይልቅስ በኢየሩሳሌም መንገዶችና በይሁዳ ከተሞች የሚያደርጉትን ሁሉ አትመለከትምን? 18 ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ፤ አባቶች እሳት ያቀጣጥላሉ፤ ሴቶች ‘የሰማይ ንግሥት’ ለተባለችው ጣዖት ኅብስት ለመጋገር ሊጥ ያቦካሉ፤ እኔንም ለማስቈጣት ለሌሎች አማልክት የወይን ጠጅ መባ ያቀርባሉ። 19 በዚህ እኔን የሚያስቈጡ ይመስላቸዋልን? ይልቅስ ራሳቸውን ይጐዳሉ፤ ኀፍረትንም በራሳቸው ላይ ያመጣሉ፤ 20 ስለዚህ እኔ ጌታ እግዚአብሔር ቤተ መቅደሴ በተሠራበት በዚህ ቦታ ላይ ብርቱ ቊጣዬን አፈሳለሁ፤ በሰዎችና በእንስሶች ላይ፥ በዛፎችና በሰብልም ሁሉ ላይ ሳይቀር አፈሰዋለሁ፤ ቊጣዬ ማንም ሊያጠፋው እንደማይችል እሳት ይሆናል። 21 “እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ እላለሁ፦ ‘በመሠዊያችሁ ላይ የምታቀርቡትን የሚቃጠለውንም ሆነ ሌላውን መሥዋዕታችሁን ሰብስባችሁ ሥጋውን ለራሳችሁ ብሉት።’ 22 የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብጽ ባወጣኋቸውም ጊዜ ስለሚቃጠልም ሆነ ስለ ሌላው ዐይነት መሥዋዕት ምንም ትእዛዝ አልሰጠኋቸውም፤ 23 ነገር ግን እኔ አምላካቸው ስሆን እነርሱም ሕዝቤ ይሆኑ ዘንድ ለእኔ መታዘዝ እንደሚገባቸው ብቻ ነገርኳቸው፤ ሁሉ ነገር እንዲከናወንላቸው ከፈለጉም እኔ በሰጠኋቸው ሥርዓት እንዲኖሩ አዘዝኳቸው። 24 እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም፤ ትኲረትም አልሰጡትም፤ በዚህ ፈንታ በእልኽና በክፋት የተሞላው ልባቸው የመራቸውን አደረጉ፤ ወደ ፊት ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ። 25 የቀድሞ አባቶቻችሁ ከግብጽ ከወጡበት ቀን አንሥቶ እስከዚህች ቀን ድረስ አገልጋዮቼን ነቢያትን እያከታተልኩ ከመላክ የተቈጠብኩበት ጊዜ የለም። 26 ነገር ግን ያዳመጠኝም ሆነ ለትእዛዜ ትኲረት የሰጠ ሰው አልነበረም፤ ይልቁንም ከቀድሞ አባቶቻችሁ ብሳችሁ እልኸኞችና ዐመፀኞች ሆናችሁ።” 27 “እንዲሁም አንተ ኤርምያስ ሆይ! ይህን ሁሉ ቃል ለሕዝቤ ትነግራቸዋለህ፤ ነገር ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸዋለህ፤ አይመልሱልህም። 28 ይህ ሕዝብ ለእኔ ለአምላኩ የማይታዘዝና ከቅጣቱም ሥነ ሥርዓትን መማር የማይፈልግ ሆኖአል፤ በዚህ ምክንያት እውነት ጨርሳ ጠፍታለች፤ ስለ እርስዋ በአንደበቱ የሚያነሣ እንኳ የለም።” በሂኖም ሸለቆ የተፈጸመ አሠቃቂ በደል 29 “የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፥ ጠጒራችሁን ተላጭታችሁ በመጣል እዘኑ፤ ዛፎች በሌሉባቸው ኰረብቶች ራስ ላይ ሙሾ አውጡ፤ እኔ እግዚአብሔር ተቈጥቻለሁ፤ ሕዝቤንም ከፊቴ አሽቀንጥሬ ጥያለሁ። 30 “የይሁዳ ሕዝብ ክፉ ነገር አድርገዋል፤ ይኸውም እኔ የምጠላቸውን ጣዖቶቻቸውን አስገብተው በውስጡ በማኖር ቤተ መቅደሴን አርክሰዋል። 31 ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት እያቃጠሉ መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ በሂኖም ሸለቆ ውስጥ ‘ቶፌት’ ተብሎ የሚጠራ መሠዊያ ሠርተዋል፤ ይህም እኔ ያላዘዝኳቸውና በፍጹምም ያላሰብኩት ነገር ነው። 32 ስለዚህ የዚያ ቦታ ስም የቤን ሂኖም ሸለቆ ወይም ቶፌት መባሉ ቀርቶ የዕርድ ሸለቆ ተብሎ የሚጠራበት ጊዜ ይመጣል፤ ሌላ የመቃብር ስፍራ ስለማይገኝ ያ ሸለቆ ራሱ የሕዝቡ መቃብር ይሆናል። 33 ሬሳቸውም የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊት ሲሳይ ይሆናል፤ አስፈራርቶ የሚያባርርላቸውም አይኖርም። 34 ምድሪቱ ባድማ ትሆናለች፤ በኢየሩሳሌም መንገዶችና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ የሠርግ ዘፈን፥ የደስታና የሐሤት ድምፅ ከቶ እንዳይሰማ አደርጋለሁ። |