Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘዳግም 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ብቸኛ የሆነ አንድ የአምልኮ ስፍራ

1 “የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በሚሰጣችሁ ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ በጥንቃቄ የምትጠብቁአቸው ኅጎችና ሥርዓቶች እነዚህ ናቸው፤

2 በምትወርሱአት ምድር የሚኖሩ ሕዝቦች በተራሮች፥ በኮረብቶችና በለመለሙ ዛፎች ሥር ለአማልክታቸው የሚሰግዱባቸውን ስፍራዎች ሁሉ ደምስሱ፤

3 መሠዊያዎቻቸውን ሁሉ አፈራርሱ፤ ከድንጋይ የተሠሩ የጣዖት ማምለኪያ ዐምዶቻቸውንም አድቅቁ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላካቸውን ምስሎች ሁሉ በእሳት አቃጥሉ፤ የተቀረጹ ጣዖቶቻቸውን ሰባብሩ፤ ስሞቻቸውንም ከቦታቸው አጥፉ።

4 “እናንተ ለእግዚአብሔር አምላካችሁ የምትሰግዱለት እነዚህ አሕዛብ ለአማልክታቸው በሚሰግዱላቸው ዐይነት መሆን የለበትም።

5 አምላካችሁ እግዚአብሔር ከነገዶቻችሁ ሁሉ መካከል ለእርሱ መኖሪያ ይሆን ዘንድ በዚያ ስሙ እንዲጠራበት የሚመርጠውን ቦታ ፈልጉና ወደዚያ ሂዱ፤

6 እዚያም የሚቃጠል መሥዋዕታችሁንና ሌላውንም መሥዋዕታችሁን ሁሉ፥ ዐሥራታችሁንና መባችሁን፥ ለእግዚአብሔር የተሳላችሁትንና የበጎ ፈቃድ ስጦታችሁን፥ የከብቶቻችሁንና የበጎቻችሁን በኲር ታቀርባላችሁ፤

7 እዚያም በባረካችሁ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት እናንተና ቤተሰቦቻችሁ ሁሉ ተሰብስባችሁ ትበላላችሁ፤ በድካማችሁ ያገኛችሁትን መልካም ነገር ሁሉ ትደሰቱበታላችሁ።

8 “ያ ሰዓት በሚደርስበት ጊዜ እስከ አሁን እንደ ፈለጋችሁ በምትፈጽሙት ዐይነት አታደርጉም፤ እነሆ እስከ አሁን የመሰላችሁን ታደርጉ ነበር፤

9 እግዚአብሔር አምላካችሁ ወደሚሰጣችሁና በሰላም ዕረፍት አድርጋችሁ ወደምትኖሩባት ርስት ገና አልገባችሁም፤

10 እግዚአብሔር አምላካችሁ በሰጣችሁ ምድር ለመኖር ዮርዳኖስን ትሻገራላችሁ፤ በደኅና እንድትኖሩ በዙሪያ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉ ዕረፍት ይሰጣችኋል፤

11 ከዚያም እኔ ያዘዝኳችሁን ነገር ሁሉ የምታመጡት እግዚአብሔር አምላካችሁ ለስሙ መጠሪያ ወደ መረጠው ቦታ ይሆናል፤ ይኸውም የሚቃጠል መሥዋዕታችሁንና ሌላውንም መሥዋዕታችሁን ሁሉ፥ ዐሥራታችሁንና መባችሁን ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር የተሳላችሁትን የበጎ ፈቃድ ስጦታችሁን ሁሉ ታመጡለታላችሁ።

12 እናንተ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆቻችሁ፥ ከወንዶችና ከሴቶች አገልጋዮቻችሁ፥ እንዲሁም ከእናንተ ጋር የርስት ክፍያ ከሌላቸው በከተሞቻችሁ ከሚኖሩ ከሌዋውያን ጋር በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ትደሰታላችሁ።

13 የሚቃጠል መሥዋዕትህን በማናቸውም ቦታ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ።

14 መሥዋዕትህን ሁሉ ማቅረብ የሚገባህ ከነገዶችህ መካከል የአንዱ ግዛት በሆነው ክፍል እና እግዚአብሔር በሚመርጠው በአንድ ስፍራ ብቻ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህንም ሆነ ሌላውንም እኔ ያዘዝኩህን ሁሉ በዚያ ስፍራ ብቻ ትፈጽማለህ።

15 “ሆኖም በሚያሰኛችሁ ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር አምላካችሁ በሰጣችሁ በረከት መሠረት ከከተሞቻችሁ በማናቸውም ቦታ ዐርዳችሁ ልትበሉ ትችላላችሁ፤ የአጋዘንና የሚዳቋ ሥጋ ለመብላት እንደሚችል ንጹሕ የሆነ ወይም ንጹሕ ያልሆነ ሰው ያን የታረደውን ሥጋ ሊበላው ይችላል።

16 ነገር ግን ደማቸውን አትብላ፤ ደሙን እንደ ውሃ በመሬት ላይ አፍስሰው፤

17 ለእግዚአብሔር የምታቀርበው መባ በምትኖርበት በማናቸውም ስፍራ ሁሉ መበላት የለበትም፤ ይኸውም የእህልህ፥ የወይን ጠጅህ፥ የወይራ ዘይትህ ዐሥራት ወይም የከብቶችህና የበጎችህ በኲር፥ ለእግዚአብሔር የተሳልከው የበጎ ፈቃድ ስጦታህ ሁሉ በማናቸውም የመኖሪያ ስፍራ ሁሉ አይበላም።

18 አምላክህ እግዚአብሔር በሚመርጥልህ ቦታ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆችህ፥ ከወንዶችና ከሴቶች አገልጋዮችህ፥ እንዲሁም በከተሞችህ ከሚኖሩ ሌዋውያን ጋር እነዚህን ትበላለህ፤ እዚያም በድካምህ ያገኘኸውን መልካም ነገር ሁሉ ትደሰትበታለህ፤

19 በምድርህ በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ሌዋውያንን ቸል እንዳትል ተጠንቀቅ።

20 “በሰጠህ ተስፋ መሠረት እግዚአብሔር ግዛትህን በሚያሰፋበት ጊዜ፥ በሚያሰኝህ ጊዜ ሁሉ ሥጋ መመገብ ትችላለህ።

21 እግዚአብሔር የመረጠው ያ አንድ ስፍራ ሩቅ ቢሆንብህ ግን በሚያሰኝህ ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር ከሰጠህ የከብትም ሆነ የበግ መንጋ መርጠህ እኔ ባዘዝኩህ መሠረት ማረድ ትችላለህ፤ ሥጋውንም በቤት ትበላዋለህ።

22 የነጻም ሆነ ያልነጻ ማንኛውም ሰው የአጋዘንም ሆነ የሚዳቋ ሥጋ በሚበላው ዐይነት ያንን ሥጋ መብላት ይችላል።

23 ነገር ግን የሕይወት መኖሪያ በደም ውስጥ ስለ ሆነ ደም ያለበትን ሥጋ ከመብላት ብቻ ተጠንቀቅ፤ ስለዚህ ሕይወትን ከሥጋ ጋር አትብላ።

24 ደምን አትብላ፤ ይልቅስ እንደ ውሃ በመሬት ላይ አፍስሰው።

25 ለአንተና ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም ይሆንልህ ዘንድ ደምን አትብላ፤ ይህንንም በማድረግህ እግዚአብሔርን ደስ ታሰኛለህ።

26 ስለዚህም የተቀደሰ መባህንና ለእግዚአብሔር የተሳልከውን ስጦታ ወደተመረጠው ቦታ ብቻ ውሰድ።

27 የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን፥ ማለትም ሥጋውንና ደሙን ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አቅርብ። የሌሎች መሥዋዕቶችህ ደም ከአምላክህ ከእግዚአብሔር መሠዊያ አጠገብ ይፍሰስ፤ ሥጋውን ግን ልትበላ ትችላለህ።

28 ለአንተና ከአንተም በኋላ ለልጆችህ ለዘለዓለም መልካም ይሆንላችሁ ዘንድ እኔ ዛሬ የማዝህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቅ፤ ይህንንም ስታደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን ነገርን ማድረግህ ነው።


ጣዖት ማምለክ እንደማይገባ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

29 “በምድራቸው ላይ ጦርነት በምታደርግበት ጊዜ እግዚአብሔር ሕዝቦችን ይደመስሳል፤ ምድራቸውንም ወርሰህ ትኖርበታለህ።

30 እነዚህ ሕዝቦች ከተደመሰሱ በኋላ እነርሱ ያደርጉ የነበረውን ድርጊት በማድረግ ወጥመድ ውስጥ አትግባ፤ እኔም እንደ እነርሱ አደርጋለሁ በማለት እነዚህ አሕዛብ አማልክቶቻቸውን እንዴት ያመልኩ ነበር ብለህ አትጠይቅ።

31 አንተ ለእግዚአብሔር ለአምላክህ የምትሰግድለት፥ እነዚህ አሕዛብ ለባዕዳን አማልክታቸው በሚሰግዱላቸው ዐይነት መሆን የለበትም፤ እነርሱ ለባዕዳን አማልክቶቻቸው በሚሰግዱበት ጊዜ የሚፈጽሙት ነገር ሁሉ እጅግ አጸያፊና በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው፤ እነርሱ ሌላው ቀርቶ የገዛ ልጆቻቸውን በመሠዊያዎቻቸው ላይ ለአማልክታቸው በእሳት ያቃጥላሉ።

32 “እንግዲህ እኔ ያዘዝኩህን ሁሉ አድርግ፤ በእርሱ ላይ ምንም ነገር አትጨምር፤ ከእርሱም አንዳች ነገር አታጒድል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos