ዘዳግም 31 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየኢያሱ በሙሴ እግር መተካት 1 ሙሴም ይህን ሁሉ ቃል ለእስራኤል ሕዝብ ተናግሮ ከፈጸመ በኋላ፥ 2 እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ የእኔ ዕድሜ መቶ ኻያ ዓመት ስለ ሆነ ከእንግዲህ ወዲህ እናንተን መምራት አይቻለኝም፤ ከዚህም በላይ እኔ ዮርዳኖስን እንደማልሻገር እግዚአብሔር ነግሮኛል፤ 3 አምላካችሁ እግዚአብሔር በፊታችሁ እየሄደ ይመራችኋል፤ በዚያ የሚኖሩትንም ሕዝቦች ደምስሶ ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ እግዚአብሔር በተናገረውም መሠረት ኢያሱ መሪያችሁ ይሆናል። 4 እግዚአብሔር የአሞራውያንን ነገሥታት ሲሖንንና ዖግን ድል ነሥቶ አገራቸውን እንዳጠፋ ሁሉ በእነርሱም ላይ እንዲሁ ያደርጋል። 5 እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ድልን ያጐናጽፋችኋል፤ ስለዚህ ልክ እኔ ያዘዝኳችሁን ትእዛዝ በእነርሱ ላይ ትፈጽማላችሁ። 6 ቈራጥነትና ድፍረት ይኑራችሁ፤ ከእነርሱም የተነሣ ከቶ አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነው፤ አይጥላችሁም፤ አይተዋችሁም።” 7 ከዚህም በኋላ ሙሴ ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ አለው፤ “በርታ ድፍረትም ይኑርህ፤ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው በመሐላ ቃል በገባላቸው መሠረት ምድሪቱን ይወርሱ ዘንድ ሕዝቡን መርተህ የምታስገባ አንተ ነህ፤ 8 ራሱ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር በመሆን ይመራሃል፤ አይጥልህም ከቶም አይተውህም፤ ስለዚህ አትፍራ፤ ተስፋም አትቊረጥ።” ሕጉ በየሰባት ዓመት መነበብ እንዳለበት 9 ከዚያ በኋላ ሙሴ የእግዚአብሔርን ሕግ ጽፎ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት አገልጋዮች ለሆኑት ለሌዋውያን ካህናትና ለእስራኤል ሕዝብ አለቆች ሰጣቸው። 10 እነርሱንም እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “ዕዳ ሁሉ በሚሰረዝበት በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ ላይ በሚከበረው የዳስ በዓል፥ 11 እስራኤላውያን ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እርሱ በሚመርጠው ቦታ በሚሰበሰቡበት ጊዜ ይህን ሕግ በፊታቸው አንብብ። 12 ሁሉም ሰምተውት አምላካችሁን እግዚአብሔርን መፍራት እንዲማሩና የዚህን ሕግ ቃላት ሁሉ በጥንቃቄ እንዲጠብቁ ወንዶችንም፥ ሴቶችንም፥ ልጆችንም፥ በከተሞቻችሁ የሚኖሩ መጻተኞችንም በአንድነት ሰብስቡ። 13 በዚህም ዐይነት የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ሕግ ሰምተው የማያውቁ ዘሮቻችሁ ሁሉ ሊያዳምጡት ይችላሉ፤ ስለዚህም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሱአት ምድር በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር መታዘዝን ይማራሉ።” እግዚአብሔር ለሙሴና ለኢያሱ የሰጣቸው መመሪያ 14 ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አንተ የመሞቻህ ጊዜ ደርሶአል፤ የሚመራበትን ትእዛዝ እሰጠው ዘንድ ኢያሱን ጠርተህ አንተና እርሱ ወደ መገናኛው ድንኳን ቅረቡ፤” ሙሴና ኢያሱም አብረው ወደ መገናኛው ድንኳን ቀረቡ፤ 15 እግዚአብሔርም በድንኳኑ ደጃፍ በቆመ በደመና ዐምድ ተገለጠላቸው። 16 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንተ በቅርብ ጊዜ እንደ ቀድሞ አባቶችህ ትሞታለህ፤ ከዚያ በኋላ ይህ ሕዝብ ከእርሱ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ያፈርሳል። እኔንም በመተው በሚወርሰው ምድር የሚገኙትን ጣዖቶች ያመልካል። 17 ይህም በሚሆንበት ጊዜ እኔ በእነርሱ ላይ ተቈጥቼ እለያቸዋለሁ፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይደመሰሳሉ፤ በእነርሱም ላይ ብዙ አሠቃቂ መቅሠፍት ይመጣባቸዋል፤ በዚያን ጊዜ፥ ‘ይህ ችግር የመጣብን አምላካችን በመካከላችን ስለሌለ አይደለምን?’ ይላሉ። 18 ባዕዳን አማልክትን በማምለክ በሠሩት ኃጢአት እኔ በዚያ ጊዜ ፈጽሞ አልረዳቸውም። 19 “ይህን መዝሙር ጽፈህ ለእስራኤላውያን አስተምራቸውና እንዲዘምሩት አድርግ፤ ይህም መዝሙር በእነርሱ ላይ ማስረጃ ይሆንልኛል። 20 ለቀድሞ አባቶቻቸው በመሐላ ቃል ኪዳን በገባሁላቸው መሠረት በማርና በወተት ወደ በለጸገችው ምድር አስገባቸዋለሁ፤ በዚያም በልተው በጠገቡና በወፈሩ ጊዜ እኔን ይተዋሉ፤ ቃል ኪዳኔንም አፍርሰው ሌሎች አማልክትን ያመልካሉ። 21 ብዙ ከባድ ችግሮች ሲደርሱባቸው ይህ በልጆቻቸው የማይረሳ መዝሙር ሲዘመር ምስክር ይሆንባቸዋል። በመሐላ ቃል ወደገባሁላቸው ምድር ከማስገባቴ በፊት አሁን እንኳ ምን ዐይነት ዝንባሌ እንዳላቸው ዐውቃለሁ።” 22 በዚያኑ ዕለት ሙሴ መዝሙሩን ጽፎ ለእስራኤል ሕዝብ አስተማረ። 23 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “በርታ ደፋርም ሁን፤ እኔ ልሰጣቸው በመሐላ ቃል ወደገባሁላቸው ምድር የእስራኤልን ሕዝብ መርተህ ታገባለህ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ።” 24 ሙሴም የዚህን ሕግ ቃላት እስከ መጨረሻ በመጽሐፍ ጽፎ ከጨረሰ በኋላ፥ 25 የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያንን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ 26 “የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበትን ይህን መጽሐፍ ወስዳችሁ፥ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት አጠገብ አኑሩት፤ በዚህም ዐይነት በሕዝቡ ላይ ምስክር ይሆንባቸዋል። 27 የእስራኤል ሕዝብ ምን ያኽል ዐመፀኞችና አንገተ ደንዳኖች እንደ ሆኑ ዐውቃለሁ፤ በእኔ ሕይወት ዘመን ከእነርሱ ጋር ሳለሁ እንኳ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፁ ናቸው፤ ከሞትሁ በኋላማ ከዚህ ይበልጥ ያምፃሉ፤ 28 ስለዚህም ይህን ሁሉ እነግራቸው ዘንድ የነገድ መሪዎቻችሁንና የሕዝብ አለቆችን ሰብስቡልኝ፤ እኔ ሰማይንና ምድርን በእነርሱ ላይ ምስክሮች አድርጌ እጠራለሁ። 29 እኔ ከሞትሁ በኋላ ካዘዝኳቸው ትእዛዝ በመውጣት የርኲሰትን ሥራ እንደሚፈጽሙ ዐውቃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ በመሥራት ስለሚያስቈጡት መቅሠፍት ያመጣባቸዋል።” የሙሴ መዝሙር 30 ከዚህ በኋላ ሙሴ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት የዚህን መዝሙር ቃሎች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ አነበበ። |