Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 78 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔርና ሕዝቡ

1 ሕዝቤ ሆይ! ትምህርቴን አድምጥ፤ ቃሌንም በጥንቃቄ ስማ፤

2 ንግግሬን በምሳሌ እጀምራለሁ፤ ከጥንት ጀምሮ የተሰወረውን ምሥጢር እገልጣለሁ።

3 ስለ ሰማናቸውና ስለ ዐወቅናቸው፥ አባቶቻችንም ስለ ነገሩን ነገሮች እናገራለሁ፤

4 እነዚህን ነገሮች ከልጆቻችን አንሰውርም፤ ስለ እግዚአብሔር ኀይል፥ ስላከናወናቸውም ታላላቅ ሥራዎችና ስላደረጋቸው ድንቅ ነገሮች ለተከታዩ ትውልድ እንናገራለን።

5 እርሱ ሥርዓትን ለያዕቆብ ልጆች ዐወጀ፤ ለእስራኤልም ሕግን መሠረተ፤ ልጆቻቸውንም እንዲያስተምሩ የቀድሞ አባቶቻችንን አዘዛቸው።

6 ይህንንም ያደረገው ተከታዩ ትውልድ እንዲያውቀውና ለልጆቹም እንዲያስተምረው ነው።

7 በዚህ ዐይነት እነርሱም በእግዚአብሔር ላይ ይታመናሉ፤ ትእዛዞቹንም ዘወትር ይፈጽማሉ እንጂ ያደረገውን ሁሉ አይረሱም።

8 እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው ዐመፀኞችና እምቢተኞች አይሆኑም፤ እነዚያ እግዚአብሔርን በማመን የጸኑ አልነበሩም፤ ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው አልኖሩም።

9 የኤፍሬም ልጆች ቀስትና ፍላጻ ይዘው ሳለ በጦርነት ቀን ሸሹ።

10 ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አልጠበቁም፤ ሕጉንም ለመፈጸም እምቢ አሉ።

11 ያሳያቸውን ተአምራት ሁሉ እና ያደረገውን መልካም ነገር ሁሉ ረሱ።

12 በግብጽ አገር በጾዓን ሜዳ የቀድሞ አባቶቻቸው እያዩ እግዚአብሔር በፊታቸው ተአምራትን አደረገ።

13 ባሕሩን ከፍሎ በመካከሉ አሳለፋቸው፤ ውሃው እንደ ግንብ እንዲቆም አደረገ።

14 ቀን በደመና፥ ሌሊት በእሳት ብርሃን መራቸው።

15 በበረሓ አለቱን ሰነጠቀ፤ ከዚያም ከጥልቅ ባሕር የሚገኘውን ያኽል ብዙ ውሃ ሰጣቸው።

16 ምንጭን ከአለት አፈለቀ፤ ውሃውም እንደ ወንዝ እንዲፈስስ አደረገ።

17 እነርሱ ግን እግዚአብሔርን በመበደል ኃጢአት መሥራት ቀጠሉ፤ በበረሓም በልዑል እግዚአብሔር ላይ ዐመፁ።

18 የተመኙትን ምግብ በመጠየቅ ሆን ብለው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት።

19 እንዲህ እያሉም በእግዚአብሔር ላይ አጒረመረሙ፤ “እግዚአብሔር በበረሓ ማእድ ዘርግቶ ምግብ ሊሰጥ ይችላልን?

20 አለቱን መሰንጠቁና ውሃም እንደ ጐርፍ ማፍሰሱ እውነት ነው፤ ታዲያ፥ ምግብን ሊሰጠን፥ ሥጋንም ሊያዘጋጅልን ይችላል ማለት ነውን?”

21 እግዚአብሔር ይህን በሰማ ጊዜ በጣም ተቈጣ፤ በያዕቆብ ልጆች ላይ እሳቱ ነደደ፤ በእስራኤልም ላይ ቊጣው ተቀጣጠለ።

22 ይህም የሆነው በእርሱ ስላላመኑና እንደሚያድናቸውም ስላልተማመኑበት ነው።

23 ሆኖም ከላይ ያሉትን ሰማያትን አዘዘ፤ የሰማይንም በሮች ከፈተ።

24 ይበሉት ዘንድ ለሕዝቡ መናን አዘነበላቸው፤ የሰማይንም ምግብ ሰጣቸው።

25 በዚህ ዐይነት ሰዎች የመላእክትን እንጀራ በሉ፤ እግዚአብሔር የሚፈልጉትን ምግብ ሁሉ ሰጣቸው።

26 የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ በኀይሉም የደቡብን ነፋስ አንቀሳቀሰ።

27 ብዙ ሥጋ እንደ አፈር፥ ብዙ ድርጭቶችንም እንደ ባሕር አሸዋ ለሕዝቡ አዘነበላቸው።

28 በሰፈራቸው መካከል በድንኳኖች ዙሪያ ድርጭቶችን አወረደላቸው።

29 ስለዚህ ሕዝቡ በልተው ጠገቡ፤ እግዚአብሔር የተመኙትን ሁሉ ሰጣቸው።

30 ይህም ሁሉ ሆኖ መጐምጀታቸው ሳይገታና ምግባቸውም ገና በአፋቸው ሳለ፥

31 የእግዚአብሔር ቊጣ በእነርሱ ላይ ተነሣ፤ የእስራኤልን ኀያላን ሰዎች ገደለ፤ ምርጥ ወጣቶችንም በአጭሩ ቀጨ።

32 ይህም ሁሉ ሆኖ ሕዝቡ ኃጢአት ከመሥራት ገና አልተገታም፤ ብዙ ተአምራት ቢያሳያቸውም በእርሱ አላመኑም።

33 ስለዚህ ዕድሜአቸውን እንደ እስትንፋስ አሳጠረ፤ ሕይወታቸውም በሽብር እንዲያልቅ አደረገ።

34 ከእነርሱ ጥቂቶቹን በሞት በቀጣበት ጊዜ የቀሩት ወደ እርሱ ይመለሱ ጀመር፤ ንስሓ ገብተውም ወደ እርሱ ከልባቸው ይመለሳሉ።

35 እግዚአብሔር አምባቸው እንደ ሆነ ያስታውሳሉ፤ ልዑል እግዚአብሔርም አዳኛቸው እንደ ሆነ ያስባሉ።

36 ነገር ግን በቃላቸው ሸነገሉት፤ የሚናገሩትም ሁሉ ሐሰት ነበር።

37 ለእርሱ ታማኞች አልነበሩም፤ የእርሱንም ቃል ኪዳን አላከበሩም።

38 ሆኖም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ምሕረትን አደረገ፤ ኃጢአታቸውን ይቅር አላቸው እንጂ አላጠፋቸውም። ብዙ ጊዜ ቊጣውን መለሰ፤ ብዙ ጊዜም መዓቱን ገታ።

39 ካለፈ በኋላ እንደማይመለስ ነፋስ፥ ሟች ፍጥረቶች መሆናቸውን አስታወሰ።

40 በበረሓ ሳሉ ብዙ ጊዜ በእርሱ ላይ ዐመፁ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ አሳዘኑት።

41 በመደጋገም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት።

42 እነርሱን ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀንና ታላቅ ኀይሉን አላስታወሱም።

43 በግብጽ አገር በጾዓን ሜዳ ያደረጋቸውን ታላላቅ ሥራዎችና ተአምራቱን ዘነጉ።

44 የወንዞቻቸውን ውሃ ወደ ደም ለወጠ፤ ስለዚህ ግብጻውያን ከወንዞቻቸው ውሃ መጠጣት አልቻሉም።

45 እነርሱን የሚያሠቃዩ ዝንቦችንና ጥፋትን የሚያስከትሉ እንቊራሪቶችን ወደ እነርሱ ላከ።

46 ሰብላቸውን ለኩብኩባ፥ ምርታቸውንም ለአንበጣ ሰጠ።

47 የወይን ተክሎቻቸውን በበረዶ፥ የበለስ ዛፎቻቸውንም በውርጭ አጠፋ።

48 ከብቶቻቸውን በበረዶ፥ በጎቻቸውንም በመብረቅ ገደለ።

49 የጥፋት መልእክተኞች ቡድን የሆኑትን አስፈሪውንና ኀይለኛ ቊጣውን፥ ማዋረዱንና ማስጨነቁን ላከባቸው።

50 ለቊጣው መንገድን አዘጋጀ፤ ከሞትም አላዳናቸውም፤ ነገር ግን ለመቅሠፍት አሳልፎ ሰጣቸው።

51 የካምን ልጆች የመጀመሪያ የወንድነት ፍሬ፥ በግብጽ በኲሮችን ሁሉ ገደለ።

52 ሕዝቡን አውጥቶ እንደ በጎች አሰማራቸው፤ በበረሓም እንደ በግ መንጋ መራቸው።

53 በሰላም ስለ መራቸው አልፈሩም፤ ነገር ግን ባሕሩ ተጥለቅልቆ ጠላቶቻቸውን አሰጠማቸው።

54 ወደ ተቀደሰችው ምድሩ፥ በኀይሉ ወደያዛት ወደ ተራራማዋ አገር አመጣቸው።

55 ከእነርሱ በፊት አሕዛብን አባረረ፤ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ለእስራኤል ነገዶች አከፋፈለ፤ ቤቶቻቸውንም ለራሱ ሕዝብ ሰጠ።

56 የእርሱ ሕዝቦች ግን በልዑል እግዚአብሔር ላይ ዐመፁ፤ ተፈታተኑትም፤ ትእዛዞቹንም አልፈጸሙም።

57 ይልቁንም እንደ አባቶቻቸው ዐመፀኞችና ከዳተኞች ሆኑ፤ እንደ ተጣመመ ፍላጻ የማያስተማምኑ ሆኑ።

58 የአሕዛብ አምልኮ በሚፈጽሙባቸው ስፍራዎቻቸው እግዚአብሔርን አስቈጡት፤ በጣዖቶቻቸውም አስቀኑት።

59 እግዚአብሔርም በሰማ ጊዜ ተቈጣ፤ ሕዝቡንም ፈጽሞ ተዋቸው።

60 በሴሎ በሰዎች መካከል ይኖርባት የነበረችውን ድንኳኑን ተዋት።

61 የኀይሉና የክብሩ መታወቂያ ምልክት የነበረችውን የቃል ኪዳን ታቦት፥ ጠላቶች ማርከው እንዲወስዱአት አደረገ።

62 የራሱን ሕዝብ ተቈጣ፤ በሰይፍ እንዲገደሉም አደረገ።

63 ጐልማሶች ሁሉ በእሳት ተቃጥለው ሞቱ፤ ልጃገረዶችም የጋብቻቸውን ደስታ ሳያዩ ተቀጩ።

64 ካህናት ሁሉ በሰይፍ ተገደሉ፤ ሚስቶቻቸውም ሊያለቅሱላቸው አልቻሉም።

65 በመጨረሻም እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰው ተነሣ፤ የወይን ጠጅ ጠጥቶ ድፍረት እንደሚሰማው ጀግና ሆነ።

66 ጠላቶቹ ተሸንፈው ወደ ኋላ እንዲሸሹና ዘለዓለማዊ ኀፍረት እንዲከናነቡ አደረገ።

67 የዮሴፍን ተወላጆች ናቀ፤ የኤፍሬምንም ነገድ አልመረጠም።

68 ነገር ግን የይሁዳን ነገድና በጣም የሚወዳትን የጽዮንን ተራራ መረጠ።

69 በዚያም በሰማይ ያለውን ቤቱን የምትመስለውን መቅደሱን ሠራ፤ ለዘለዓለም የምትኖርና እንደ ምድር የጸናች አደረጋት።

70 ባሪያውን ዳዊትን መረጠ፤ ከበጎች መሰማሪያም ወሰደው፤

71 ከበጎች እረኝነት አውጥቶም፥ የእስራኤል ንጉሥና የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠባቂ አደረገው።

72 ዳዊትም በፍጹም ቅንነት ጠበቃቸው፤ በጥበብም መራቸው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos