ኤርምያስ 1:16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ሕዝቤ ኃጢአት ስለ ሠሩ እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ እኔን ትተው ለሌሎች አማልክት ዕጣን ያጥናሉ፤ ምስሎችንም ሠርተው ይሰግዱላቸዋል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እኔን በመተው ክፋት ስለ ሠሩ፣ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑ፣ እጆቻቸው የሠሯቸውን ስላመለኩ፣ በሕዝቤ ላይ ፍርድን ዐውጄአለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ስለ ክፋታቸው ሁሉ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ፥ እኔን ትተውኛል፤ ለሌሎችም አማልክት ዕጣንን አጥነዋል፤ ለእጃቸውም ሥራዎች ሰግደዋልና። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ስለ ክፋታቸውም ሁሉ፥ እኔን ስለ ተዉ፥ ለሌሎችም አማልክት ስለ ሠዉ፥ ለእጃቸውም ሥራ ስለ ሰገዱ፥ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ስለ ክፋታቸውም ሁሉ፥ እኔን ስለ ተዉ ለሌሎችም አማልክት ስላጠኑ ለእጃቸውም ሥራ ስለ ሰገዱ፥ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። |
ዐዛርያስም ከንጉሥ አሳ ጋር ለመገናኘት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ አሳ ሆይ! አድምጠኝ! እናንተም የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ ስሙኝ! እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር እስከ ሆናችሁ ድረስ እርሱም ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ከፈለጋችሁትም ታገኙታላችሁ፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል፤
እነርሱ እኔን ትተው ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቅርበዋል፤ ይህም ያደረጉት በደል ቊጣዬን አነሣሥቶአል፤ በኢየሩሳሌም ላይ የተነሣሣው ቊጣዬም ይፈጸማል እንጂ አይበርድም፤
ሰው ከአንድ ዛፍ ግማሹን ለማገዶ፥ ግማሹንም ጣዖት ለመሥራት ይጠቀምበታል፤ ግማሹን እሳት አንድዶ ለመሞቅና እንጀራ ለመጋገር ይጠቀምበታል፤ በሌላው ጒማጅ ጣዖት ሠርቶ በፊቱ እየሰገደ ያመልከዋል።
በዚያን ጊዜ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ መሥዋዕት ወደሚያቀርቡላቸው ባዕዳን አማልክት ሄደው ርዳታ እንዲያደርጉላቸው ይጮኻሉ፤ ነገር ግን እነርሱ ይህ ጥፋት በሚመጣበት ጊዜ ሊያድኑአቸው አይችሉም።
“እኔ የሠራዊት አምላክ ነኝ፤ እናንተ የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ እኔ እንደ ተከልኩት ዛፍ ናችሁ፤ ነገር ግን በዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት መሥዋዕት በማቅረባችሁ አስቈጣችሁኝ፤ ስለዚህ አሁን ጥፋትን አመጣባችኋለሁ።”
በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል በላቸው፦ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ ከእኔ ተለይተው የሐሰት አማልክትን በማምለክ አገለገሉ፤ እኔን ተዉኝ፤ ሕጌንም አልፈጸሙም።
እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የእስራኤል ተስፋ ነህ፤ አንተን የሚተዉ ሁሉ ያፍራሉ፤ የሕይወት ውሃ ምንጭ የሆንከውን አንተን እግዚአብሔርን ስለ ተዉ በትቢያ ላይ እንደ ተጻፈ ስም ይደመሰሳሉ።
ሕዝቤ ግን እኔን ረስተዋል፤ ከንቱ ለሆኑ ጣዖቶችም ዕጣን ያጥናሉ፤ እነርሱም ባልታወቀ መንገድ እንዲሄዱ አድርገዋቸዋል፤ ተሰናክለውም የቀድሞውን መንገድ ትተዋል።
ይህንንም የማደርገው ሕዝቡ እኔን ስለ ተዉና ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት በማቅረብ ይህን ስፍራ ስላረከሱ ነው፤ እነርሱም ሆኑ የቀድሞ አባቶቻቸው ከይሁዳ ነገሥታት ጭምር ስለ ነዚህ አማልክት የሚያውቁት ነገር የለም፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ንጹሖች ሰዎችን በመግደል ይህ ስፍራ በደም የተሞላ እንዲሆን አድርገውታል።
ሕዝቤ ሁለት ኃጢአት ሠርተዋል፤ ይኸውም የሕይወት ውሃ ምንጭ የሆንኩትን እኔን ትተውኛል፤ ውሃ መቋጠር የማይችሉ የተሸነቈሩ ጒድጓዶችን ለራሳቸው ቆፍረዋል።”
እነሆ የራስሽ ክፋት ይቀጣሻል፤ ክሕደትሽ ይፈርድብሻል፤ እኔን አምላክሽን እግዚአብሔርን መተውሽና ለእኔም የምታሳዪውን ክብር ማስቀረትሽ ምን ያኽል ከባድና መራራ በደል እንደ ሆነ ትረጂአለሽ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ጌታ የሠራዊት አምላክ ነኝ።”
“በእጃችሁ የሠራችኋቸው አማልክት እስቲ የት አሉ? የሚችሉ ከሆነ መከራ ሲደርስባችሁ ተነሥተው ያድኑአችሁ፤ ይሁዳ ሆይ! ከተሞችህ ብዙዎች በሆኑ መጠን አማልክትህም በዝተዋል።”
ምድር ታለቅሳለች፤ ሰማይም በጨለማ ይጋረዳል፤ ይህን እግዚአብሔር ተናግሮአል፤ ሐሳቡም አይለወጥም፤ ቊርጥ ውሳኔ አድርጎአል፤ ወደ ኋላም አይመለስም።
እኛ እንፈጽማለን ብለን ያሰብነውን ነገር ሁሉ እናደርጋለን፤ የሰማይ ንግሥት ተብላ ለምትጠራው አምላካችን ዕጣን እናጥናለን፤ እኛና የቀድሞ አባቶቻችን፥ ንጉሦቻችንና መሪዎቻችን በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ስናደርግ በነበረው ዐይነት አሁንም የወይን ጠጅ መባ እናቀርብላታለን። ይህን ሁሉ በምናደርግበት በዚያን ጊዜ ብዙ ሲሳይ ነበረን፤ ባለጸጎችም ስለ ነበርን ምንም ችግር አልነበረብንም።
ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ፤ አባቶች እሳት ያቀጣጥላሉ፤ ሴቶች ‘የሰማይ ንግሥት’ ለተባለችው ጣዖት ኅብስት ለመጋገር ሊጥ ያቦካሉ፤ እኔንም ለማስቈጣት ለሌሎች አማልክት የወይን ጠጅ መባ ያቀርባሉ።
ከዚህም የተነሣ ትሰርቃላችሁ፤ ትገድላላችሁ፤ ታመነዝራላችሁ፤ ምላችሁም በሐሰት ትመሰክራላችሁ፤ ለባዓል መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ከዚህ በፊት የማታውቁአቸውን አማልክት ታመልካላችሁ።
እኔ ልዑል እግዚአብሔር ‘አንድ ነገር የማደርግበት ጊዜ ቀርቦአል፤ አልገታም፤ አልምርም፤ ሐሳቤን አለውጥም፤ እንደ አካሄድሽና እንደ ሥራሽ እፈርድብሻለሁ’ ” ብዬ ተናግሬአለሁ።
ነገር ግን ሕዝቤን እስራኤልን ይበልጥ ወደ እኔ እንዲቀርቡ በጠራኋቸው መጠን፥ እነርሱ ይበልጥ ከእኔ እየራቁ ሄዱ። በዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት መሥዋዕት ከማቅረብና ለምስሎቹም ዕጣን ከማጠን አልተቈጠቡም።
ይህ በጥጃ ምስል የተሠራ ጣዖት በአናጢ እጅ የተሠራ ስለ ሆነ አምላክ ሊሆን አይችልም፤ ስለዚህ በጥጃ ምስል የተሠራው የሰማርያ ጣዖት ተሰባብሮ ይወድቃል።
እግዚአብሔር እንደ ነጐድጓድ ያለ ድምፁን በሠራዊቱ ላይ ያሰማል፤ ሠራዊቱ ምንኛ ብዙ ነው! ትእዛዙን የሚቀበሉ ከቊጥር በላይ ናቸው፤ በእርግጥም የእግዚአብሔር ቀን ታላቅ ነው፤ በጣም አስፈሪ ስለ ሆነ በዚያ ቀን ማን ችሎ ይቆማል?
“ክፉ ነገር በማድረግ እግዚአብሔርን ስለ ተውክ በምታደርገው ነገር ሁሉ ፈጽመህ እስክትጠፋ ድረስ እርግማንን፥ ሁከትንና ውርደትን ያመጣብሃል።
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንተ በቅርብ ጊዜ እንደ ቀድሞ አባቶችህ ትሞታለህ፤ ከዚያ በኋላ ይህ ሕዝብ ከእርሱ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ያፈርሳል። እኔንም በመተው በሚወርሰው ምድር የሚገኙትን ጣዖቶች ያመልካል።
በእነዚህ መቅሠፍቶች ከሞት የተረፉት የሰው ዘር ከእጃቸው ሥራ ተመልሰው ንስሓ አልገቡም፤ አጋንንትንና ከወርቅ፥ ከብር፥ ከናስ፥ ከድንጋይና ከእንጨት የተሠሩ ማየት ወይም መስማት ወይም መሄድ የማይችሉትን ጣዖቶች ማምለክንም አልተዉም።