Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 44 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በግብጽ ለሚኖሩ እስራኤላውያን የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል

1 በሰሜን ግብጽ ውስጥ ሚግዶል፥ ጣፍናስና ሜምፊስ ተብለው በሚጠሩት ከተሞችና በአገሪቱም ደቡባዊ ክፍል ተበታትነው ስለሚኖሩት እስራኤላውያን ሁሉ እግዚአብሔር ተናገረኝ፤

2 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “በኢየሩሳሌምና በሌሎችም የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ ያመጣሁትን ጥፋት እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል፤ አሁንም እንኳ እንደ ፈራረሱ ናቸው፤ ማንም አይኖርባቸውም፤

3 ይህም የሆነበት ምክንያት በእነዚያ ከተሞች ይኖሩ የነበሩ ሕዝብ ክፉ ሥራ በመሥራት ስላስቈጡኝ ነው፤ እነርሱ ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቀረቡ፤ እነርሱም ሆኑ እናንተ ወይም የቀድሞ አባቶቻችሁ ያላመለኩአቸውን አማልክት አመለኩ፤

4 እኔ የምጠላቸውን እነዚህን አጸያፊ ነገሮች እንዳታደርጉ ያስጠነቅቋችሁ ዘንድ አገልጋዮቼን ነቢያትን ወደ እናንተ ደጋግሜ ልኬ ነበር።

5 እናንተ ግን እነርሱን ማዳመጥም ሆነ ለሚናገሩት ቃል ዋጋ ልትሰጡት አልፈለጋችሁም፤ ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት የማቅረብ ክፉ ልምዳችሁን መተው አልፈለጋችሁም፤

6 ስለዚህም በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ ቊጣዬንና መዓቴን በማፍሰስ በእሳት እንዲጋዩ አደረግሁ፤ እነርሱም ዛሬ እንደሚታዩት ሁሉ ፍርስራሾችና ባድማ ሆነዋል።

7 “አሁንም እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እስቲ ልጠይቃችሁ፦ እናንተስ ራሳችሁ ለምን ይህን ሁሉ ክፉ ነገር ታደርጋላችሁ? ከይሁዳ ሕዝብ መካከል አንድ እንኳ ለዘር እንዳይተርፍ በወንዶችና በሴቶች፥ በልጆችና በሕፃናት ላይ ጥፋት እንዲመጣ ለምን ትፈልጋላችሁ?

8 መጥታችሁ በምትኖሩባት በዚህችስ በግብጽ ምድር ለጣዖቶች በመስገድና ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት በማቅረብ ስለምን ታስቈጡኛላችሁ? ወይስ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ እንዲዘባበቱባችሁና ስማችሁንም መራገሚያ ያደርጉት ዘንድ ራሳችሁን በራሳችሁ ማጥፋት ትፈልጋላችሁን?

9 በቀድሞ አባቶቻችሁ፥ በይሁዳ ነገሥታትና በሚስቶቻቸው፥ በእናንተ በራሳችሁና በሚስቶቻችሁ አማካይነት በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ የተፈጸመውን ክፉ ሥራ ሁሉ ረስታችሁታልን?

10 ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ራሳችሁን ዝቅ በማድረግ ትሑታን ሆናችሁ አልተገኛችሁም፤ ለእኔ ክብር አልሰጣችሁኝም፤ ለቀድሞ አባቶቻችሁና ለእናንተ በሰጠሁትም ሕግና ደንብ ጸንታችሁ መኖር አልፈለጋችሁም።

11 “ስለዚህም የእስራኤል አምላክ እኔ የሠራዊት ጌታ በእናንተ ላይ በቊጣ ተነሣሥቼ ይሁዳን በሙሉ እደመስሳለሁ፤

12 በይሁዳ ከስደት ከተረፉት መካከል ወደ ግብጽ ወርደው በዚያ ለመኖር የወሰኑትን ሁሉ እንዲጠፉ አደርጋለሁ፤ ከትልቅ እስከ ትንሽ በጦርነት ወይም በረሀብ በግብጽ አገር ይሞታሉ። እነርሱም ለሕዝቦች አስደንጋጭ ይሆናሉ፤ ሕዝብም ሁሉ ይዘባበትባቸዋል፤ ስማቸውንም መራገሚያ ያደርጉታል።

13 ኢየሩሳሌምን በጦርነት፥ በራብና በቸነፈር እንደቀጣሁ፥ በግብጽ የሚኖሩትንም እቀጣለሁ፤

14 በይሁዳ ከስደት ተርፈው ወደ ግብጽ ወርደው ከሚኖሩት መካከል አንድ እንኳ የሚያመልጥ ወይም የሚተርፍ አይኖርም፤ እንደገና ይኖሩባት ዘንድ ወደሚናፍቋት ወደ ይሁዳ የሚመለስ ማንም አይኖርም፤ ከጥቂት ስደተኞች በቀር ተመልሶ የሚመጣ አይኖርም።”

15 ሚስቶቻቸው ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት የሚያቀርቡ መሆናቸውን የሚያውቁ ወንዶች ሁሉ፥ በግብጽ ደቡባዊ ክፍል የሚኖሩት እስራኤላውያንና በዚያ ቆመው የነበሩት ሴቶች ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው በመቅረብ እንዲህ አሉኝ፦

16 “አንተ በእግዚአብሔር ስም የተናገርከውን ሁሉ መስማት አንፈልግም፤

17 እኛ እንፈጽማለን ብለን ያሰብነውን ነገር ሁሉ እናደርጋለን፤ የሰማይ ንግሥት ተብላ ለምትጠራው አምላካችን ዕጣን እናጥናለን፤ እኛና የቀድሞ አባቶቻችን፥ ንጉሦቻችንና መሪዎቻችን በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ስናደርግ በነበረው ዐይነት አሁንም የወይን ጠጅ መባ እናቀርብላታለን። ይህን ሁሉ በምናደርግበት በዚያን ጊዜ ብዙ ሲሳይ ነበረን፤ ባለጸጎችም ስለ ነበርን ምንም ችግር አልነበረብንም።

18 ነገር ግን ለሰማይ ንግሥት የሚቃጠል መሥዋዕትና ለእርስዋም የወይን ጠጅ መባ ማቅረብን ካቋረጥንበት ጊዜ ጀምሮ ምንም ያተረፍነው ነገር የለም፤ ሕዝባችንም በጦርነትና በረሀብ አልቆአል።”

19 ሴቶችም ጨምረው ሲናገሩ፥ “በሰማይ ንግሥት እንጎቻ በምንጋግርበት ጊዜ፥ ለእርስዋ መሥዋዕትና የወይን ጠጅ መባ በምናቀርብበት ጊዜ፥ ከባሎቻችን ተለይተን ያደረግነው ነገር አልነበረም።”

20 በዚህ ዐይነት የመለሱልኝን ወንዶች፥ ሴቶችና ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አልኳቸው፦

21 “እናንተና የቀድሞ አባቶቻችሁ፥ ንጉሦቻችሁና መሪዎቻችሁ፥ በምድሪቱም የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ፥ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ዕጣን ታጥኑ እንደ ነበረ፥ እግዚአብሔር አያስበውም ወይም ረስቶታል ብላችሁ ታስባላችሁን?

22 እነሆ በአሁኑ ጊዜ ምድራችሁ ፍርስራሽ ሆናለች፤ የሚኖርባትም የለም፤ ምድሪቱ አጸያፊ ሆናለች፤ ሕዝብም ሁሉ እንደ ተረገመች ይቈጥሩአታል፤ እግዚአብሔር የዐመፅና የክፋት ሥራችሁን ሁሉ አይታገሥም።

23 ይህም ሁሉ መቅሠፍት የደረሰባችሁ ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት በማቅረባችሁ፥ እግዚአብሔርን በማሳዘናችሁ፥ ለሕጉ፥ ለድንጋጌውና ለሥርዓቱም ባለመታዘዛችሁ ነው።”

24-25 ከይሁዳ ተሰደው በግብጽ ስለሚኖሩት ሕዝብ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ የነገረኝን ሁሉ ለሕዝቡ ሁሉ በተለይም ለሴቶቹ እንዲህ በማለት ነገርኳቸው፦ “እናንተና ሚስቶቻችሁ ለሰማይ ንግሥት ስእለት ለመስጠት ቃል ገብታችኋል፤ ይኸውም እናንተ ለእርስዋ ዕጣን ልታጥኑላት፥ የወይን ጠጅም መባ ልታፈሱላት የገባችሁትን ቃል ኪዳን ፈጽማችኋል፤ እንግዲያውስ ቀጥሉ፤ የገባችሁትን ቃል ጠብቁ፤ መሐላችሁንም ፈጽሙ፤

26 ነገር ግን በግብጽ ስለምትኖሩ እስራኤላውያን ሁሉ እኔ እግዚአብሔር በኀያሉ ስሜ በመማል የወሰንኩትን ስሙ፤ ከእናንተ ማንም ሰው ‘ሕያው ልዑል እግዚአብሔርን’ ብሎ በስሜ እንዲምል አልፈቅድም።

27 ደግ ነገር ሳይሆን ክፉ ነገር እንዲደርስባችሁ አደርጋለሁ፤ ከእናንተ አንድ እንኳ ሳይተርፍ ሁላችሁም በጦርነትና በረሀብ ትሞታላችሁ፤

28 ነገር ግን ከእናንተ ጥቂቶች ብቻ ከሞት ተርፈው ከግብጽ ወደ ይሁዳ ይመለሳሉ፤ በዚያን ጊዜ ወደ ግብጽ የወረዱ ስደተኞች የእኔ ወይስ የእናንተ የማንኛችን ቃል እውነት እንደ ሆነ ያረጋግጣሉ፤

29 በዚህ ቦታ በምቀጣችሁ ጊዜ ‘በእናንተ ላይ ጥፋትን አመጣለሁ’ ብዬ የተናገርኩት ቃል እውነት እንደሚሆን እኔ እግዚአብሔር አረጋግጥላችኋለሁ፤

30 እኔ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ቀድሞ ጠላቱ ለነበረና ይገድለው ዘንድ ለሚፈልገው ለባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አሳልፌ እንደ ሰጠሁት ሁሉ፥ ሖፍራ ተብሎ የሚጠራውን የግብጽ ንጉሥ ሊገድሉት ለሚፈልጉ ጠላቶቹ አሳልፌ እሰጠዋለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos