Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የይሁዳ ሕዝብ ኃጢአትና የደረሰባቸው ቅጣት

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ኃጢአታችሁ በብረት ብዕር ተጽፎአል፤ ሹል በሆነው አልማዝ በልባችሁ ጽላትና በመሠዊያዎቻችሁ ቀንዶች ላይ ተቀርጾአል።

2 በመላ አገራችሁ፥ በኮረብቶችና በተራሮች ላይ እንዲሁም በታላላቅ ዛፎች ሥር ሕዝቡ በየትውልዱ መሠዊያዎችንና የተለዩ ዐምዶችን አቁሞ አሼራ ተብላ ለምትጠራው ጣዖት ይሰግዳሉ።

3 በመላ አገራችሁ በፈጸማችሁት ከፍተኛ ኃጢአት ምክንያት ያላችሁን ሀብትና ንብረት እንዲሁም መሠዊያዎቻችሁን ሁሉ በምርኮ ጠላቶቻችሁ እንዲወስዱ አደርጋለሁ።

4 ቊጣዬ እንደ እሳት እንዲቀጣጠል ስላደረጋችሁ እርሱም ለዘለዓለም ስለሚነድ የሰጠኋችሁን ርስት ሁሉ እንድታጡና በማታውቁት አገር ጠላቶቻችሁን እንድታገለግሉ አደርጋለሁ።”


ልዩ ልዩ ምሳሌዎች

5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔን ትቶ በሰው የሚታመንና፥ ‘ኀይል ይሆነኛል’ ብሎ በሥጋ ለባሽ ሰው የሚመካ የተረገመ ይሁን።

6 እንዲህ ዐይነቱ ሰው ማንም ሊኖርበት በማይችል በጨው ምድርና በበረሓ እንደሚበቅል ቊጥቋጦ ነው፤ በሕይወቱ ሙሉ ምንም መልካም ነገርን አያገኝም።

7 “በእኔ ብቻ ተማምኖ የሚኖር ሰው ግን የተባረከ ነው።

8 እርሱም በወራጅ ምንጭ አጠገብ እንደ ተተከለና በውሃም ውስጥ ሥር እንደ ሰደደ ዛፍ ይሆናል፤ ዘወትር ቅጠሉ ለምለም ሆኖ የሚኖር ይህ ዐይነቱ ዛፍ የፀሐይ ሐሩር እንኳ አያሰጋውም፤ ዝናብ ባይዘንብለትም እንኳ ፍሬ ከማፍራት አይገታም።

9 “የሰው ልብ ከሁሉ ነገር በላይ ተንኰለኛና ጠማማ ነው፤ ውስጠ ምሥጢሩን የሚረዳ ማነው?

10 እኔ እግዚአብሔር ግን የሰውን አእምሮና የሰውን ልብ እመረምራለሁ፤ እያንዳንዱንም ሰው በአካሄዱና በሥራው መጠን ዋጋውን እሰጠዋለሁ።”

11 ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ሀብትን የሚሰበስብ፥ ያልጣለችውን ዕንቊላል ታቅፋ እንደምትፈለፍል ቆቅ ነው፤ በዕድሜው አጋማሽ የሰበሰበውን ሃብት ሁሉ ያጣል። በመጨረሻም ሞኝነቱ ግልጥ ይሆናል።

12 ቤተ መቅደሳችን የተሠራበት ቦታ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከፍ እንዳለው የክብር ዙፋን ነው።

13 እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የእስራኤል ተስፋ ነህ፤ አንተን የሚተዉ ሁሉ ያፍራሉ፤ የሕይወት ውሃ ምንጭ የሆንከውን አንተን እግዚአብሔርን ስለ ተዉ በትቢያ ላይ እንደ ተጻፈ ስም ይደመሰሳሉ።


ኤርምያስ እግዚአብሔር እንዲታደገው መለመኑ

14 እግዚአብሔር ሆይ፥ ፈውሰኝ፤ እኔም እፈወሳለሁ፤ ታደገኝ፤ እኔም በሰላም እኖራለሁ፤ ዘወትርም አንተን አመሰግናለሁ።

15 ሕዝቡ “ኤርምያስ ሆይ! እግዚአብሔር ተናገረ ያልከውን ነግረኸን ነበር፤ ታዲያ ለምን አልተፈጸመም” ብለው ይጠይቁኛል።

16 ነገር ግን እግዚአብሔር ሆይ! በእነርሱ ላይ መቅሠፍትን እንድታመጣ ያሳሰብኩህ ጊዜ የለም፤ የመከራ ዘመን እንዲገጥማቸውም አልተመኘሁም፤ እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ይህንና የተናገርኩትን ሁሉ ታውቃለህ።

17 አንተ በመከራ ጊዜ መሸሸጊያዬ ስለ ሆንክ አስደንጋጭ አትሁንብኝ፤

18 እግዚአብሔር ሆይ! በሚያሳድዱኝ ሁሉ ላይ ኀፍረትን አምጣባቸው፤ እኔን ግን አታሳፍረኝ፤ እነርሱ እንዲሸበሩ አድርግ፤ እኔን ግን አታስደንግጠኝ፤ ተሰባብረው እስኪደቁ ድረስ ደጋግመህ አጥፋቸው።


ሰንበትን ስለማክበር

19 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የይሁዳ ንጉሥ ከከተማይቱ በሚወጣበትና በሚገባበት ወደ ሕዝቡ ቅጽር በር እንዲሁም በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት ወደ ሌሎቹም ቅጽር በሮች ሄደህ ቁም፤

20 እኔ የምነግርህንም ቃል እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘የይሁዳ ነገሥታትና ሕዝብ! እንዲሁም በእነዚህ ቅጽር በሮች የምትገቡ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ!

21 ሕይወታችሁን ለማዳን እኔ የምሰጣችሁን ማስጠንቀቂያ ጠብቁ፤ ስለዚህ በሰንበት ቀን ምንም ዐይነት ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም ቅጽር በሮች አትግቡ።

22 የቀድሞ አባቶቻችሁን እንዳዘዝኳቸው ሰንበትን የተቀደሰ ቀን አድርጋችሁ አክብሩ እንጂ በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ ከቤታችሁ አትውጡ፤ በሰንበት ቀን ምንም ሥራ አትሥሩ።

23 የቀድሞ አባቶቻችሁ ቃሌን አላዳመጡም፤ ትእዛዜንም አልፈጸሙም፤ ይልቁንም እልኸኞች በመሆን ለእኔ መታዘዝንና ከእኔ መማርን እምቢ አሉ።

24 “‘እንግዲህ የሚያዳምጡኝ ከሆኑ እነዚህ ሕዝብ ትእዛዜን እንዲጠብቁ ንገራቸው፤ በሰንበት ቀን ምንም ዐይነት ሸክም ይዘው በከተማይቱ በሮች አይግቡ፤ ሰንበትን የተቀደሰ ቀን አድርገው ያክብሩ እንጂ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አይሥሩ።

25 በዳዊት ዙፋን ላይ የተቀመጡ ነገሥታት ከባለ ሥልጣኖቻቸው ጋር በኢየሩሳሌም በሮች ይገባሉ፤ እነርሱም ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ጋር በአንድነት ሆነው በፈረሶችና በሠረገሎች ላይ ይቀመጣሉ፤ የኢየሩሳሌም ከተማ ሁልጊዜ በሕዝብ የተሞላች ትሆናለች።

26 ከይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ዙሪያ ከሚገኙ መንደሮች ሕዝቡ በአንድነት ይሰበሰባሉ፤ ከብንያም ክፍል፥ ከኰረብቶች ግርጌ፥ ከተራሮችና ከይሁዳ ደቡብ ይመጣሉ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላውንም መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና ዕጣን፥ የምስጋናውንም መሥዋዕት ጭምር ወደ ቤተ መቅደሴ ያመጣሉ።

27 ነገር ግን ለእኔ መታዘዝና ሰንበትንም የተቀደሰ ቀን አድርገው ማክበር ይገባቸዋል፤ በዚህ ዕለት በኢየሩሳሌም የቅጽር በሮች ምንም ዐይነት ሸክም ይዘው መግባት የለባቸውም፤ ትእዛዜን ባለመቀበል ይህን ቢያደርጉ ግን የኢየሩሳሌም ቅጽር በሮች በእሳት እንዲጋዩ አደርጋለሁ፤ የኢየሩሳሌም ቤተ መንግሥቶችም በእሳት ይነዳሉ፤ እሳቱንም ሊያጠፋ የሚችል የለም።’ ”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos